በህጻናት መደፈር መንሰራፋት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለባት ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር…… Leave a comment

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴራሊዮን በመድፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶች መንሰራፋት የተነሳ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀች ጥቂት ዓመታትን አስቆጠረች።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቁርጠኛ የተባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።

አዋጁ ከታወጀ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ቢቢሲ አፍሪካ አይ የወሲብ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ሰዎች ፍትህ አግኝተው እንደሆነ በዚህ ዘገባ መርምሯል።

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጹሁፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል።

ከሴራሊዮን መዲና ፍሪታውን በስተምስራቅ በምትገኘው ማኬኒ ከተማ አንዲት ወጣት እናት ከሶስት ዓመት ልጇ ጋር ከቤቷ ደጃፍ ተቀምጣለች።

ለደህንነቷ ሲባል ስሟን አኒታ እያልን የምንጠራት እናት በህይወቷ ብዙ ውጣ ውረድ ብታይም ነሐሴ 2015 ዓ.ም የተከሰተውን አስከፊ ነገር ግን የሚስተካከል በህይወቷ የለም።

በዚያን ወቅት የሁለት ዓመት ዕድሜ የነበራትን ጨቅላ ልጇ ከተጠቀለለችበት ጨርቅ ደም እየተንጠባጠበ ነበር ያገኘቻት።

“ለአንዲት ሴት ተቀጥሬ እሰራ ነበር እናም አንድ ቅዳሜ ጥዋት ወደ ገበያ እንድሄድ ላከችኝ” ስትል ልጇን ከአሰሪዋ እና ከግለሰቧ 22 ዓመት ልጅ ጋር ትታት እንደወጣች ታስረዳለች።

“ልጄን ጣፋጭ እና ብስኩት ሊገዛላት ልወስዳት ነው አለ። ለካ ሃሰት ነበር” ትላለች።

እናት ስትመለስ ልጇ እንደጠፋች ተረዳች። ጨቅላዋን ከተወሰነ የፍለጋ ጊዜ በኋላ ቢያገኙዋትም የ22 ዓመቷ እናት ታዳጊዋ ደም እየፈሰሳት መሆኑን አየች።

ጨቅላዋን ወደ ሆስፒታል ወሰዷት። መደፈሯ በህክምና ባለሙያዎች የተረጋገጠ ሲሆን ብልቷም በሁለት ዙር በቀዶ ህክምና መሰፋት ነበረበት።

“ገና ልጄ እንደመጣች መመርመር ሲጀምሩም ያዩት ነገር አስደንግጧቸው “አምላኬ ሆይ። ይህ ሰው በዚህች ጨቅላ ላይ የፈጸመባት ነገር” አሉ። ልጄን ሲያክም የነበረው ዶክተር እንኳን ራሱ አለቀሰ” ትላለች።

አኒታ ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰደችው። ነገር ግን ደፋሪው ግለሰብ ደብዛው ጠፋ። ፖሊስ በአንድ ዓመት ውስጥ እንኳን ሊያገኘው አልቻለም።

“ፕሬዚዳንቱ ህጻናትን የሚደፍሩ ግለሰቦች ተይዘው ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ህግ አጽድቀዋል” የምትለው እናት ነገር ግን በልጇ ባየችው ነገር ተፈጻሚ አለመሆኑን አይታለች።

በአገሪቷ የሚፈጸሙ መድፈሮችን ለመግታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማዳ ባዮ የጣሉትን ጠበቅ ያለ እስራትን ያካተተውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትጠቅሳለች።

ለዚህ አዋጅ መነሻ የሆነው ከስድስት ዓመታት በፊት የተነሳው ተቃውሞ ነው። በመዲናዋ ፍሪታውን በርካታ ሰዎች “ከሴት ልጆቻችን ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚል ጽሁፍ ያለበት ነጭ ቲሸርቶቻቸውን ለብሰው የሚል ትልቅ ተቃውሞ አስነሱ።

በወቅቱም የአምስት ዓመት ህጻን በመደፈሯ ምክንያት ከወገቧ በታች ሽባ መሆኗን ተከትሎ የአገሪቱን ህዝብ አስደነገጠ። በወቅቱም በነበረው አኃዝ ወሲባዊ ጥቃቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ የጨመሩበት ሲሆን ከነዚህም አንድ ሶስተኛው ህጻናት እንደነበሩ ተገልጿል። የሁኔታውን አሰቃቂነት ያዩት ሴራሊዮናውያን በቃን ብለው ለተቃውሞ ወጡ።

ከየካቲት 2019 ጀምሮ ለአራት ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ የተንሰራፋውን የወሲብ ጥቃቶችን ለመግታት የመንግሥትን ሃብትን እንዲያዛውሩ የፈቀደላቸው ነው።

አገሪቷ ህጓን አሻሽላ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ጠንከር ያለ ቅጣትን አመጣች።

በዚህም መሰረት ለመድፈር ወንጀል እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ቅጣት በተለይም ህጻናት ላይ የደረሰ ጥቃት ከሆነ የእድሜ ልክ እስራት ቅጣት ይገኝበታል። ወሲባዊ ጥቃቶችን በአፋጣኝ ሁኔታ ለመዳኘት የሚያስችሉ ሞዴል ፍርድ ቤቶች በፍሪታውን ተመሰረቱ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ መጠነኛ መሻሻል ያለ ይመስላል። ከፖሊስ በተገኘው መረጃ መሰረት ሪፖርት የተደረጉ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና መደፈሮች በ17 በመቶ ገደማ ማለትም በአውሮፓውያኑ ከ12 ሺህ በላይ ከነበረው በ2023 ወደ 10 ሺህ ወርዷል።

ሆኖም የግንዛቤ ማስጨበጫዎች እና አዳዲስ መዋቅሮችን መፍጠር አንድ ጉዳይ ቢሆንም ነገር ግን ልክ እንደ አኒታ ያሉ ሴቶች ለልጆቻቸው ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው።

ሬይንቦው ኢንሺየቲቭ የተሰኘው ተቋም የወሲባዊ ጥቃቶች ሰለባዎች ከሆኑ ሰዎች ጋር የሚሰራ ብሔራዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

ተቋሙ እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2022 ከመጡ 2 ሺህ 705 ጉዳዮች መካከል ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት 5 በመቶ ብቻ ናቸው።

ለዚህም ደግሞ ዋነኛው ችግር ደግሞ ህግ አስከባሪዎች ያለባቸው የአቅም እጥረት ነው።

አኒታ የልጇን መደፈር ሪፖርት ያደረገችበት ማኬኒ ፖሊስ ጣቢያ የቤተሰብ ድጋፍ ክፍል የሚመሩት አቡ ባካር ካኔ በየሳምንቱ አራት የተደፈሩ ህጻናት ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ያስረዳሉ።

የጸጥታ አስከባሪዎቻቸው በዋነኝነት የገጠማቸው ትልቁ ፈተና በአካል ሄዶ ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝ የትራንስፖርት እጥረት ነው።

በግዛቲቱ ያሉ ሰባቱን የፖሊስ ጣቢያዎችን የማስተባበር ኃላፊነቱ በእሳቸው ላይ የተጫነ ሲሆን ሁሉም አንድም ተሸከርካሪ የላቸውም።

“ተጠርጣሪዎች የት እንዳሉ የምናውቅባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በተሽከርካሪ እጥረት የተነሳ ሄደን መያዝ እንችልም” ይላሉ አስተባባሪው።

በዚህም የተነሳ “ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ጊዜ ማድረግ ፈታኝ ነው” ይላሉ።

እንደ በርካታ ሴራሊዮናውያን እሳቸውም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው እርምጃ መደነቃቸው አልቀረም።

“እኛ በቂ ጥሩ ህጎች እና ፖሊሲዎች አሉን። ነገር ግን አወቃቀሩ እና የሰው ኃይል አቅም በሴራሊዮን ውስጥ ያሉ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለመፍታት ተግዳሮቶችን ደቅኗል” ይላሉ።

የመድፈር ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ቢያዙ እንኳን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ አሁንም ቢሆን ትግል ነው።

በአገሪቱ የመድፈር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲታይ ሰነዶቹን መፈረም የሚችሉት አንድ ሰው ብቻ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብቻ ናቸው። መጀመሪያ ሲታቀድ ሂደቱን ለማፋጠን እና በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ታስቦ የነበረ ቢሆን የተለየ እክል መፍጠሩ አልቀረም።

“በአሁኑ ወቅት ማንኛውም የህግ ባለሙያዎች ከጾታዊ ጥቃቶች ጋር የተያዙ ወንጀሎች ክስ ላይ መፈረም አይችሉም” ሲሉ በመንግሥት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ጠበቃ ጆሴፍ ኤኬ ሴሳይ ያስረዳሉ።

“የ2019 ማሻሻያ የወሲብባዊ ጥቃቶች ክሶች ላይ መፈረም የሚችሉት የጠቅላይ አቃቤ ህግ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል። ስለዚህ የተለያዩ ክሶችን ወደ ፍርድ ቤቶች ለማምጣት ፈታኝ አድርጎታል” ይላሉ።

የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ቼርኖር ባህ ሂደቱ ፍጹም እንዳልሆነ አምነው ነገር ግን “ያለንን እድገት እያሻሻልን የምንቀጥልበት ሂደት ነው” ይላሉ።

የመድፈር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ፍትህ በማግኘት ረገድ ደረጃ ብዙም አልተቀየረም የሚሉ ሰዎችን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትሩ “አንዳንድ ማህበረሰቦች እንዲህ አይነት ስሜት እንዳላቸው” ገልጸዋል። ነገር ግን ምንም መሻሻል አልታየም የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

“ያስቀመጥናቸው የስርዓት ማሻሻያዎች፣ አዳዲስ ህጎች እና እርምጃዎች አሉ። ይህም ከዓመታት በፊት እንደነበረው ተስፋ አስቆራጭ ጊዜ ውስጥ አይደለም የሚለው ስሜት እንዲፈጠር አድርገዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።

አኒታ ጨቅላ ልጇ ከተደፈረች አንድ ዓመት ሊጠጋው ነው። የልጇን ደፋሪ በተመለከተ ምንም አዲስ መረጃ ከፖሊስ ማግኘት ስላልቻለች የተጠርጣሪውን ፎቶ ፌስቡክ ላይ ለመለጠፍ ተገዳለች።

“ግለሰቡን ፈልገው ፈልገው እንዲያገኙልኝ እየጠየቅኩ ነው። በስቃይ ላይ ነው ያለሁት። በኔ ልጅ ላይ የደረሰው ነገር በሌላ ልጅ ላይ እንዲደርስ አልፈልግም” ስትል እያለፈችበት ያለውን መከራ ለቢሲ ገልጻለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ(BBC)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want