የትግራይ ኃይሎች በአላማጣ ከተማ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መስፈራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ Leave a comment

የትግራይ ኃይሎች በአላማጣ ከተማ መታየታቸውን እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ መስፈራቸውን ነዋሪዎች እና በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ገለጹ።

በትግራይ ክልል በኩል የተሾሙት የከተማዋ ከንቲባ በበኩላቸው ክሱ “ፈጽሞ ሐሰት ነው፤ ከአካባቢው የወጣ እንጂ የገባ መደበኛ ሠራዊት የለም” ሲሉ አስተባብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ካለፈው ሳምንት ሰኞ ወዲህ የትግራይ ኃይሎች እንቅስቃሴ በከተማዋ እንደሚታይ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ነዋሪ ታጣቂዎቹ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሰፈሩ ገልጸዋል።

“ኮከብ ጽባሕ ትምህርት ቤት፣ ምሥራቅ ትምህርት ቤት እና ከሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀርባ ባሉ ሦስት ትምህርት ቤቶች ላይ የቡድን መሣሪያ ጭምር ይዘው ነው የገቡት” ብለዋል።

አክለውም “ኋላ ላይ ግን የመከላከያ ሠራዊት ሁሉንም አጠቃለው መብራት የሚባለው ትምህርት ቤት አድርገዋቸዋል” በማለት አሁን ስላለው ሁኔታ ገልጸዋል።

ነዋሪው ጨምረውም “በአየር ማረፊያ አዲስ ዓለም የሚባል ትምህርት ቤት ትምህርት ቆሞ የህወሓት ታጣቂዎች እየኖሩበት ነው” ብለዋል።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪም የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ ከሳምንት በፊት ጀምሮ መታያት እንደጀመረ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሦስተኛ ነዋሪ ደግሞ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ አካባቢው በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር ከመግባቱ በፊት በከተማዋ አመራር የነበሩ ግለሰቦች በከተማዋ መታየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ከዚህ በፊት ከተማዋ በትግራይ ክልል ሥር እየተዳደረች ሳለ በአመራር ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች እየታዩ ነው ያሉት” ብለዋል።

አክለውም “ሌሎች የጦር መሣሪያ ይዘው የከተማው አቅራቢያ ሆነው እንደመሸጉም ይወራል” ሲሉ የሰሙትን ተናግረዋል።

ነዋሪው ለቢቢሲ “ከከተማው አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚገኝ እና ከዚህ ቀደም የፖሊስ ጣቢያ በነበረ አካባቢ ኬላ ዘርግተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ወደ አጎራባች [ወደ ባላና አፋር] በሚወስደው አካባቢ ኬላ ዘርግተው መታወቂያ እያዩ ነው” ሲሉም እኚሁ ነዋሪ አክለዋል።

አያይዘውም “በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ወደ ቆቦ መስመርም ገብተው ወጥተዋል እየተባለ ነው” ብለዋል።

በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በከተማዋ ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ ታጣቂዎች ሰፍረው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ስድስቱ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች ላይ፣ ከአላማጣ ከተማ ውጪ ኮረምን ጨምሮ ከሚያዝያ 7 እና 8 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከነትጥቃቸው ገብተዋል። ዝርፊያም እያካሄዱ ነው” ሲሉ ከሰዋል።

አቶ ኃይሉ አክለውም “አላማጣ ከተማ ዳር ላይ ያሉ ቦታዎች እየገቡ ነበር። አሁን ወደ መሃል ለመግባት ሞክረዋል። ከሕዝብ ተቃውሞ ገጠማቸው። መከላከያም እንዲመልሳቸው ተደርጎ አሁን ምሥራቅ እና ሹሜ በርሄ ትምህርት ቤቶች ላይ የተወሰኑ ኃይሎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ በከተማው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቅሰው “አላማጣ ከተማ በመግባት ትምህርት ቤቶች ላይ እንዲከማቹ የተደረገው ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ ነው” ብለዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከጥቂት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ‘የህወሓት ታጣቂዎች’ ሲል የገለጻቸው ኃይሎች “በከተማዋ ላይ የወረራ ጥቃት በመክፈት ነዋሪዎችን እየገደለ፣ ንብረታቸውን እየዘረፈ እና እያፈናቀለ ይገኛል” ሲል ከሷል።

ቢቢሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገራቸው በትግራይ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት አወዛጋቢ ከሆኑ ቦታዎች የትግራይ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ መውጣቱን ገልጸው፤ አንደ አዲስ የገባ ሠራዊት አለመኖሩን ተናግረዋል።

“ገቡ የተባለው ወጡ ለማለት ከሆነ አላውቅም። ሆነ ተብሎ ሰውን ለማደናገር ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር በትግራይ መንግሥት በሚዲያ የተደገፈ ቀረጻ ተደርጎ አከራካሪ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ ያለ የትግራይ ኃይል እንዲወጣ ተደርጓል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም “በስምምነቱ መሠረት ግጭቱ ከመፈጠሩ በፊት የአካባቢ ሚሊሻ ተብሎ ታጣቂ የነበረው ወደ ነበረበት ቦታ መመለስ አለበት ተብሎ በግልጽ ተነግሯል” ብለዋል።

አቶ ዝናቡ፣ “ከጦርነቱ በፊት የአካባቢያቸውን ሰላም ያስከብራሉ ተብለው የነበሩ የአካባቢው ሚሊሻዎች እንዲገቡ በተባለው መሠረት እንዲገቡ ሙከራ ነው የተደረገው። ካምፕ ላይ ነው የሰፈሩት” በማለትም ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

ካምፕ ላይ ለምን ሰፈሩ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “እስክንጠይቅ ወይም እስክንረዳ ድረስ አትገቡም ብለው ስላልፈቀዱልን ነው። አንድ ቦታ ላይ ለቁጥጥር እንዲመቻቸው ነው እንጂ መሆኒ ተፈናቃይ ሆኖ ይኖር የነበረ በከተማው ቤቱ፣ ንብረቱ፣ ልጆቹ ባሉበት ሁለተኛ ካምፕ ውስጥ መግባት አይገባውም ነበር። ስምምነቱም እሱን አይልም” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፣ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ሲባል በአላማጣ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኙ ገርጃሌ እና በቅሎ ማነቂያ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።

አብን በበኩሉ አቶ ጌታቸው ታጣቂዎች ከአካባቢው መውጣታቸውን የገለጹት “በከተማዋ ሕዝብ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ለማወጅ ነው” ብሏል።

አቶ ዝናቡ በአላማጣ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት ገርጃሌ እና በቅሎ ማነቂያ አካባቢዎች የነበረው ኃይል “ሆነ ተብሎ የገባ ሳይሆን ሚያዝያ 5 የፕሪቶርያው ስምምነት ይከበር ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ስናደርግ ሕዝቡን ሊያጠቃ የመጣውን ኃይል ለመከላከል ነው እንጂ ሊዋጋ አይደለም። ውጊያም አልነበረም” ብለዋል።

በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው ታጣቂዎቹ ከአካባቢዎቹ እንዳልወጡ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“እንኳን ሊወጡ ተጨማሪ ኃይሎች ገብተው ወደማያውቁባቸው ቦታዎች እየገቡ ነው” ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪም ከአካባቢው ታጣቂዎች አለመውጣታቸውን ገልጸው፣ ከአካባቢዎቹ በርካታ ነዋሪዎች በስጋት መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል።

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ሥር የነበሩት እነዚህ አካባቢዎች ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ገልጿል።

አካባቢዎቹ ያለ አስተዳዳሪ ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ የቆዩ ሲሆን፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችም እንደተቋረጡ ናቸው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want