ሁሉም ነዋሪዎች የመዘንጋት ችግር ያለባቸው መንደር Leave a comment

ፈረንሳይ አንዲት መንደር አቋቁማለች- የመዘንጋት ችግር ያለባቸው ነዋሪዎች ብቻ የሚኖሩባት።

ላንዳይስ አልዛይመር ትሰኛለች።

በዚህች በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በምትገኘው መንደር የሚኖሩ ነዋሪዎች ሁሉም የመዘንጋት ችግር አልዛይመር የተሰኘው ህመም አለባቸው።

በመንደሯ ውስጥ በዋናው አደባባይ የሚገኘው ሱቅ መሰረታዊ የሚባሉ ጨቀጦችን ይዟል።

ለምሳሌ ፈረንሳይ የምታተወቅበት ባጌት የተሰኙት የዳቦ አይነቶች። ይህንን መደብር ለየት የሚያደርገው ገንዘብ አይቀበልም ። ነዋሪዎቹ የገንዘብ ቦርሳቸውንም ሆነ ገንዘብ ይዘው እንደሆነ ማስታወስ አይጠበቅባቸውም።

ቀድሞ አርሶ አደር የነበሩት ፍራንሲስ እለታዊ ጋዜጣቸውን እየወሰዱ በነበረበት ወቅት ነበር ቢቢሲ ያገኛቸው።

የመንደሯ ዋነኛ ማዕከል በሆነችውም ሬስቶራንት ቡና እንጠጣ የሚል ሃሳብ ቢቢሲ አቀረበላቸው።

የመርሳት (የመዘንጋት) ችግር እንዳለባቸው የህክምና ባለሙያው ሲነግራቸው ምን ተሰማቸው? ቢቢሲ ለፍራንሲስ የጠየቃቸው የመጀመሪያ ጥያቄ ነው።

ራሳቸውን እየነቀነቁም የነበረውን ሁኔታም ለማስታወስ እየሞከሩም “በጣም ፈታኝ ነበር” የሚል ምላሽ ሰጡ።

ፍራንሲስ የመዘንጋት ችግር የነበረባቸውን አባታቸውን ትግል ቢያዩም ምንም ፍራቻ አይሰማቸውም።

“ሞትን አልፈራም። ምክንያቱም አንድ ቀን መሞታችን አይቀርም” ይላሉ።

“በሽታው ቢኖርም እስካለሁ ድረስ መኖሬን እቀጥላለሁ”

“ምንም እንኳን ህይወት ተመሳሳይ ባትሆንም እየኖርኩ ነው”

“እጅ ከሰጠን በቃ አከተመ ማለት ነው። ስለዚህ በተቻለ መጠን፣ በምትችለውም መንገድ ያለህን ኑሮ ትኖራለህ” ይላሉ

ወደ መገበያያ መደብር እና ሬስቶራንት ከመሄድ በተጨማሪ የመንደሯ ነዋሪዎች ቲያትር ቤት ሄደው ቲያትሮችን እንዲመለከቱም ይበረታታሉ።

የተለያዩ ቡድኖችንም በመቀላቀል ህይወታቸውን ማስቀጠል እንደሚችሉም ይነገራቸዋል።

ቢቢሲ በዚህች መንደር ያገኛቸው ባለትዳሮቹ ፊሊፕ እና ቪቪያን የመርሳት ችግር እንዳለባቸው በምርመራ ቢረጋገጥም የተለመደውን ህይወታቸውን ለማስቀጠል እየሞከሩ ይገኛሉ።

“በእግራችን ረጅም መንገድ እንሄዳለን፣ እንራመዳለን” ይላሉ ፊሊፕ መንገዳቸውን እየተመለከቱ።

ቢቢሲም ደስተኛ ናችሁ? የሚል ጥያቄ ሲጠይቃቸውም እሳቸውም ፊታቸው ወዲያውኑ ራሳቸውን አዙረው ደመቅ ባለ ፈገግታ “አዎ በእውነት! ደስተኛ ነን” አሉ በማያጠራጥር ድምጸት።

ጥንዶቹ ያዘዙትን ቡና ጨርሰው ሞቅ ያለ ልብሳቸውን ደረብ አድርገው በእግራቸው ወደ መንደሯ ፓርክ አመሩ።

የጊዜ ዑደት በዚህች መንደር የተለዬ ነው ይላል የቢቢሲ መንደር አስጎብኚ።

እንደሌላው የከተሜ ኑሮ ቀኑ ለተለያዩ ጉዳዮች አልተከፋፈለም።

ለቀጠሮ፣ ገበያ ለመውጣት ወይም ምግብ ለማብሰል እና ለማጽዳት የተቀመጡ ሰዓቶች የሉም።

በተቻለ መጠን የመንደሯ ነዋሪዎች ህይወትን በተረጋጋ እና እና ነጻነት በተሞላበት መንገድ እንዲኖሩ ለማድረግም ነው የሚሞከረው።

የመንደሯ ሁኔታ በቅርበት ክትትል የሚደረግበት ሲሆን፣ ፕሮፌሰር ሄሌኔ አሚዬቫ እንደሚሉት በበሽታው ሂደትም ላይ ለየት ያለ ተጽእኖ እያመጣ እንደሆነም የእስካሁኑ ውጤቶች ያሳያሉ።

“የመዘንጋት ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ህክምና ተቋማት ወይም ማዕከላት ሲገቡ የምናየው ጉዳይ በተፋጠነ ሁኔታ የግንዛቤ ሁኔታቸው ያሽቆለቁላል። በዚህች መንደር ውስጥ ግን ይህንን አልተመለከትንም” ይላሉ።

“የበሽታው ሂደት ቀስ ባለ ሁኔታ እንደሚሄድ ተገንዝበናል” ሲሉም ያስረዳሉ።

“እንደነዚህ አይነት መንደር ማቋቋም በክሊኒክ በሚደረጉ የህክምና ውጤቶችን አቅጣጫ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ለማመን ምክንያቶች አሉን” ብለዋል።

በተጨማሪም የመርሳት ችግር ያለባቸው ቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት እና ጭንቀት ላይ የጣላቸውም ቤተሰቦች እንዲህ አይነት መንደር እፎይታ ሰጥቷቸዋል።

የ89 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን እና የመርሳት ችግር ያለባቸውን እናቷን ልትጎበኝ የመጣችው ዶሚኒክ “የአዕምሮ ሰላሜን አግኝቻለሁ። ምክንያቱም ደህንነቷ ተጠብቆ አዕምሮዋም ሰላም የሚሆንበት ስፍራ ላይ እየኖረች ስለሆነ ነው” ትላለች።

የእናቷ መኝታ ክፍልም ግድግዳ ላይ የቤተሰብ ፎቶዎች እና ስዕሎች ተሰቅለዋል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም እናቲቱ ሲጠቀሙበት በነበሩ የቤተሰብ እቃዎች ተሞልቷል። በመስኮቱም በኩል የአትክልት ስፍራው ተንጣልሏል።

እሳቸውን ለመጎብኘት የተቀመጠ ሰዓት የለም። ሰዎች በፈለጉበት ሰዓት መጥተው ይጎበኟቸዋል። ሲፈልጉም ይሄዳሉ። ዶሚኒክ እና እህቶቿ እናታቸው እንዲህ አይነት እጅግ በጣም ጥሩ እንክብካቤ ይገጥማቸዋል ብለው ፍጹም እንዳልጠበቁ ታስረዳለች።

“ትቼያት ስሄድ እፎይታ ይሰማኛል። ስመጣም ልክ የቀድሞ ቤት እንደምጎበኛት ነው የሚሰማኝ። ከእናቴ ጋር በቤታችን ነን” ስትልም ስለ መንደሯ ትናገራለች።

መንደሯ በቪላ ቤቶች የተከፋፈለ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ቪላም ወደ ስምንት የሚጠጉ ነዋሪዎች አሉ። በቪላውም ውስጥ የሚኖሩት ነዋሪዎች የጋራ ማዕድ ቤት፣ ሳሎን እና የመመገቢያ ክፍሎችንም ይጋራሉ።

የመንደሩ ነዋሪዎች የተወሰነ መዋጮ ቢያወጡም አጠቃላይ ወጪውም በክልሉ የፈረንሳይ መንግሥት ነው የሚሸፈነው።

መንደሪቷንም ለማቋቋም መንግሥት 22 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶበታል።

መንደሯ በአውሮፓውያኑ 2020 ስትቋቋም በዓይነቷ ሁለተኛዋ ስትሆን ብቸኛዋም የምርምር ፕሮጀክት አካል ናት።

በዓለም ላይ እንደዚህች ያሉ የአዕምሮ መዘንጋት ችግር ላለባቸው የተቋቋሙ መንደሮች ቁጥር ከአስራ ሁለት ያነሱ እንደሆኑ ይታሰባል።

በመንደሪቷ ባለው የውበት ሳሎን ጸጉራቸውን ታጥበው እያደረቁ የነበሩት የ65 ዓመቷ ፓትሪሺያ ላንዳይስ አልዛይመር መንደር በህይወት ላይ ሁለተኛ የመኖር ዕድል እንደሰጣቸው ይናገራሉ።

“እዚህ ከመምጣቴ በፊት ቤት ነበርኩ። ነገር ግን እየሰለቸኝ ነበር” ይላሉ።

“ምግብ የምታበስልልኝ ሴት ነበረች። ሁሌም ይደክመኝ ነበር። ጥሩ ስሜትም አይሰማኝም። የመርሳት ችግር ቀላል እንዳልሆነም ስለተረዳሁ ፈርቼም ነበር” ይላሉ።

“በምችለው መርዳት የምችልበት ስፍራም መኖር እፈልግም ነበር”

“በሌሎች የእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ይባላል። ነገር ግን ህምመተኞቹ ምንም አያደርጉም”

“በዚህች መንደር ግን፣ ትክክለኛ ህይወትን ነው የምንኖረው። ትክክለኛ ስል እንደቀደመ ህይወታችን” ይላሉ

አብዛኛውን ጊዜ የመዘንጋት ችግር መገለልን ያመጣል።

በዚህች መንደር ግን ያ ሁሉ የለም ጠንካራ የማህበረሰብ ቁርኝት ያለበት ነው።

ሰዎች እርስ በርስ ይጠያየቃሉ። በተለያዩ እንቅስቃሴዎችም በመሳተፍ አብሮነታቸውን ያጎለብታሉ።

የማህበረሰብ ትስስሩ ጠንካራ መሆን ደስተኛ እና ጤናማ ኑሮ ለመኖር መሰረታዊ ሁኔታ እንደሆነ የሚናገሩት ተመራማሪዎች በተለይም የመዘንጋት ችግር ላለባቸው ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነው ይላሉ።

በመንደሪቷ 120 የሚጠጉ ነዋሪዎች ሲኖሩ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የእንክብካቤ ሰጪ ባለሙያዎች አሉ። የበጎ ፈቃደኞች ቁጥር ከነዋሪዎቹም ሆነ ከባለሙያዎች ይበልጣል።

የመዘንጋት (የመርሳት ችግር) ጭካኔው እየከፋ መሄዱ እና መድኃኒት አለመኖሩ ነው።

ነገር ግን በዚህች መንደር ያሉ ነዋሪዎች ህመማቸው እየከፋ ሲሄድ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ይሰጣቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በብዙ ስፍራዎች ክረምቱ ከቤት አላስወጣ ቢልም በዚህች መንደር ያለው ህይወት ግን ሞቅ ያለ እና መጠያየቅ የሞላበት ነው።

*በዚህ ታሪክ ውስጥ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አንዳንዶች ሙሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ በጠየቁት መስረት ሙሉ ስማቸው አልተካተተም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want