“ሥራዬ ቲክቶክ ላይ የሚለጠፉ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ቪድዮዎችን ማፅዳት ነበር”……. Leave a comment

በቅርቡ ቢቢሲ እጅግ አሰቃቂ የሚባለውን የማኅበራዊ ሚድያ የጨለማ ዓለም ለመዳሰስ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል።

ይህ ዓለም እጅግ ዘግናኝ እና አሰቃቂ የሚባሉ ጭንቀት የሚለቁ እንዲሁም ሕጋዊ ያልሆኑ ምሥሎች የሚለጠፉበት ነው።

ሰዎች ሲታረዱ፣ በጅምላ ሲገደሉ፣ ሕፃናት ስቃይ ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና የጥላቻ ንግግሮች . . . ማኅበራዊ ሚድያው ላይ የማይለጠፍ የለም። እነዚህን ይዘቶች ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከመድረሳቸው በፊት የሚቆጣጠሩ ሰዎች አሉ።

የእነዚህ ይዘት ተቆጣጣሪዎች (ኮንቴንት ሞደሬተርስ) ሥራ እነዚህ አሰቃቂ የሚባሉ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን ተመልክቶ አስፈላጊ ከሆነ ማጥፋት ነው። እነዚህ ቪዲዮዎች ሰዎች ‘ሪፖርት’ ያደረጓቸው አሊያም በቴክኖሎጂ አማካይነት የተጣሩ ናቸው።

በይነ መረብ ላይ የሚለጠፉ አንዳንድ ይዘቶች ለተጠቃሚዎች የሚመከሩ አይደሉም። ይህን ተለትሎ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጎጂ የሚባሉ ይዘቶችን እንዲቆጣጠሩ ጫና እተደረገባቸው ይገኛል።

ምንም እንኳ ቴክኖሎጂው ብዙ መዋዕለ ነዋይ ቢፈስበትም በራሱ መሰል ይዘቶችን አጣርቶ ማስወገድ አይችልም። ይህ ማለት ሥራው የሚሠራው በሰዎች ነው ማለት ነው።

ሞደሬተሮች ብዙውን ጊዜ የሚቀጠሩት በሦስተኛ ወገን ነው። ለምሳሌ ፌስቡክ ራሱ ሳይሆን ይዘት የሚቆጣጠሩ ሰዎችን የሚቀጥረው ሥራውን ለሌላ ወገን በኮንትራት ሰጥቶ ነው የሚያሠራው።

እንደ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ወክለው በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የይዘት ቁጥጥር የሚሠሩ ድርጅቶች አሉ።

በኬንያ ያሉ የይዘት ቁጥጥር ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ቀጥረው ያሠራሉ።

ቢቢሲ ያናገራቸው አብዛኞቹ ‘ኮንቴንት ሞደሬተሮች’ ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች ይህን ኢንዱስትሪ እየለቀቁ ይወጣሉ።

የአብዛኞቹ ታሪክ አሳዛኝ የሚባል ነው። የአንዳንዶቹ ታሪክ ለሚዲያ ለማቅረብ ከባድ ነው።

“ለምሳሌ ስልክሽ ላይ ቲክቶክ ብትከፍቺ የተለያዩ ቪዲዮዎች ታያለሽ። ሰዎች ሲደንሱ የሚያሳዩ ደስታ የሚታይባቸው ቪዲዮዎች” ይላል ናይሮቢ ላለ ድርጅት ይዘት ተቆጣጣሪ ሆኖ ይሠራ የነበረው ሞጄዝ።

“ነገር ግን ከጀርባ እኔ ቁጭ ብዬ በመቶዎች የሚቆጠሩ እጅግ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ምሥሎችን እያጣራሁ ማፅዳት ነበር ሥራዬ” ይላል።

ይህ የኮንቴንት ሞደሬሽን ሥራ የአእምሮ ጤናቸው ላይ ያደረሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስመልክቶ አሠሪዎቻቸውን የከሰሱ በርካታ የቀድሞ ሠራተኞች አሉ።

ፎክስግሎቭ የተሰኘው የሕግ አማካሪ ቡድን የእነዚህን ሠራተኞች ክስ እየተመለከተ እገዛ ይሰጣል። የድርጅቱ ኃላፊ ማርታ ዳርክ “ቤቴ ቁጭ ብዬ ማኅበራዊ ሚዲያ ስዳስስ የታረደ ሰው እንዳያይ የሚያደርጉኝ እነዚህ ኮንቴንት ሞደሬተሮች ናቸው” ይላሉ።

የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ በአውሮፓውያኑ 2020 በሥራቸው ምክንያት የአእምሮ ጤና መታወክ ላጋጠማቸው ሠራተኞች 52 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መክፈሉ አይዘነጋም።

ክሱን ያቀረበችው የይዘት ቁጥጥር ሥራ ትሠራ የነበረችው ሴሌና ስኮላ ስትሆን ሰዎች ሕይወታቸው ሲጠፋ እየተመለከተች የአእምሮ ጤናዋ እንደታወከ ትናገራለች።

ቢቢሲ ያናገራቸው አብዛኞቹ የቀድሞ የይዘት ተቆጣጣሪዎች “ሥነ-ልቦናዊ ቁስለት” ገጥሞናል ይላሉ። አንዳንዶች እንቅልፍ ያስቸግራቸዋል፤ የተቀሩት ደግሞ የምግብ ፍላጎታቸው ተዳክሟል።

አንድ ሰው ሕፃናት ሲያለቅሱ ሲሰማ እጅግ ከባድ ድንጋጤ ውስጥ እንደሚገባ ይናገራል። ሌላ ግለሰብ ደግሞ ሕፃናት ሲሰቃዩ የሚያሳዩ ብዙ ምሥሎች በመመልከቱ ከሚስቱ እና ከልጆቹ ጋር ያለው ግንኙነት እንደተቀዛቀዘ ይገልጻል።

ሞጄዝ

የቻትጂፒቲ ፈጣሪ የሆነው ኦፕንኤአይ የተባለው ድርጅት የቀድሞ ሠራተኛ የሆኑት ዴቭ ዊልነር (ስማቸው የተቀየረ) ሰው ሠራሽ አስተውሎት በመጠቀም ጎጂ የሚባሉ ይዘቶችን አጣርቶ ማስወገድ የሚችል ቴክኖሎጂ አበልፅገናል ይላል። ቴክኖሎጂው ስኬታማነቱ 90 በመቶ መሆኑንም ይናገራል።

ነገር ግን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፉ ዘግናኝ እና አሰቃቂ የሚባሉ ይዘቶችን ለመቆጣጠር ትክክለኛው መንገድ ነው አይደለም የሚሉ ጥቂት አይደሉም።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንዱስትሪውን ማገዝ ቢችልም የመናገር ነፃነትን ሊገድብ ይችላል፤ አልፎም የሰው ልጅ የሚታዘባቸውን ለቅሞ ሊያገኝ አይችልም የሚል ትችት ይቀርብበታል።

ቢቢሲ የይዘት ቁጥጥር የሚያሠሩ ግዙፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ድርጅቶችን ምላሽ ለማግኘት ሙከራ አድርጓል።

የቲክቶክ ቃል አቀባይ ኩባንያው ይዘት ቁጥጥር ከባድ ሥራ መሆኑን ይረዳል፤ ለሠራተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ይተጋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ቃል አቀባዩ አክለው ኩባንያው የሠራተኞቹን የአእምሮ ጤና ለመጠበቅ አስፈላጊውን እንደሚያደርግ አሳውቀዋል።

የኢንስታግራም እና ፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ በበኩሉ የይዘት ቁጥጥር የሚሠሩለት ድርጅቶች በሙሉ 24 ሰዓት ሙሉ በሠለጠኑ ባለሙያዎች እገዛ እንዲያደርጉ እንደሚጠየቁ አሳውቋል።

ሜታ አክሎም ይዘት ተቆጣጣሪዎች አሰቃቂ የሚባሉ ምሥሎችን ማየት ካልፈለጉ ለይቶ የሚያደበዝዝ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚችሉም ገልጿል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop