ሰሞኑን በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው “ተቃውሞ” መነሻው ምንድን ነው? Leave a comment

የዩኒቨርስቲዎች የምግብ በጀት ማስተካከያ በተደረገ በቀናት ውስጥ የሦስት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚቀርብላቸው ምግብ “ጥራት እና መጠን” ቀንሷል በማለት ተቃውሞ አነሱ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ትምሕርት ሚኒስቴር በምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት “የተማሪዎች ዕለታዊ የምግብ በጀት” ላይ ማሻሻያ መደረጉን ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

በዚህም 22 ብር የነበረው የአንድ ተማሪ ዕለታዊ የምግብ በጀት ወደ 100 ብር ከፍ እንዲል ተወስኗል።

ከታኅሳስ ወር ጀምሮ “በወጥነት” በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ገቢራዊ ይሆናል የተባለው አዲሱ የምግብ በጀት ከተመኑ ጋር ‘የተጣጣመ ሜኑ [የምግብ ዝርዝር]’ እንደተዘጋጀለትም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

አዲሱ የምግብ ሜኑ “ዝቅተኛ መስፈርትን መሰረት በማድግ” እንደተዘጋጀ የገለፀው ትምሕርት ሚኒስቴር፤ ዩኒቨርስቲዎቹ የአካባቢያቸውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስት ማስገባት ጭማሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማል።

ይሁን እንጂ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሦስት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሚቀርብላቸው ምግብ ጥራት ተቃውሞ አሰምተዋል።

በአዲሱ የምግብ ዝርዝር ቅር የተሰኙ የደባርቅ፣ ደብረ ብርሃን እና መቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በመመገቢያ አዳራሾች ተቃውሞ ሲያሰሙ ንብረት ውድመትን ጨምሮ በፀጥታ ኃይሎች እስር እና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተቃውሞው በተጀመረበት ደባርቅ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታኅሳስ 10/2017 ዓ.ም. ተማሪዎች ምሳ ሰዓት ላይ የቀረበላቸው “መጠን እና ጥራት” ቀንሶ በማግኘታቸው የመመገቢያ አዳራሽ (ካፌ) ውስጥ ግርግር መፍጠራቸውን አንድ ምንጭ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት ከመመገቢያ አዳራሹ ወጥተው ወደ አስተዳደር ህንፃ እያቀኑ እያለ “አድማ ብተና” የተባሉ የፀጥታ ኃይሎች ተቃውሞውን ለመበተን መሳሪያ “ወደ ላይ” እየተኮሱ እንደነበር ገልጸዋል።

ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ በፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እና እስርም እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን እና መቀለ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችም ተቃውሞ ማሰማታቸውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሕብረት ለቢቢሲ ገልጿል።

ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለመቀለብ በመንግሥት ከተመደበላቸው 22 ብር በተጨማሪ ከ100 ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ምግብ ያቀርቡ እንደነበር ሕብረቱ አስታውሷል።

“በ22 ብር ብቻ አልነበረም እየተቀለበ የነበረው” የሚሉት የሕብረቱ ፕሬዝዳንት ሃየሎም ስዩም፤ ዩኒቨርስቲዎች አዲሱ የምግብ በጀት ማሻሻያን ተከትለው ድጎማቸውን በማንሳት በ100 ብር ምግብ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

“[ጭማሪው] የት ሄደ? የት ገባ?” በሚል በተማሪዎች እና በዩኒቨርስቲዎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

“22 ብር እያለ ቀለቡ የተሻለ ነበር። አሁን 100 ብር ከሆነ በኋላ ደግሞ ቀንሷል የሚል [ነው]” ሲሉ የተማሪዎችን ጥያቄ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ለመቀለብ የሚደጉሙትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ “ቀንሰዋል” ብለዋል።

ተማሪዎች በዋናነት የምግብ በጀት ማስተካከያ ሲደረግ የሚቀርብላቸው የምግብ ጥራት በፊት ከጠበቁት በታች ቀንሶ ማግኘታቸው ለተቃውሞው መነሻ ሆኗል።

አንድ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተለምዶ ‘ዜርፎር’ የሚባለው ስጋ ወጥ መቅረብ ማቆሙን ጠቁሞ፤ በአዲሱ የምግብ ዝርዝር የተካተቱ ቂንጬ የመሰሉ ምግቦች እንደማይቀርቡ ተናግሯል።

“[ምግቡ] ጥራት የለውም ብዛትም የለውም” የሚለው ተማሪው፤ “ርቦን ነው የምንውለው። . . . በሳምንት አምስት ቀን ቁርስ አንድ ዳቦ በሻይ ነው የሚሰጠን። ፍርፍሩ ደግሞ በጣም ጥራት የሌለው ፍርፍር ነው። ስጎ የለውም። ጣዕሙ በጣም ኮምጣጣ የሆነ ፍርፍር ነው” በማለት ለተጨማሪ የምግብ ወጪ እተዳረግን ነው ብሏል።

“አራት እጥፍ ስለተጨመረ ከነበረው ምግብ መስተካከል አለበት ነው [በተማሪዎች] እየተባለ ያለው” የሚሉት የተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ “ምንም የተጨመረ ነገር የለም። የተጨመረው የወጪ መጋራት ነው” ብለዋል።

“ምግቡ ሳይስተካከል [ተመርቀን] ስንወጣ በ100 ብር ወጪ መጋራት ልንከፍል ነው። ስናሰላው ከ100 ሺህ ብር በላይ ሊሆን ይችላል” በማለት በምግብ በጀት ማስተካከያው ተማሪው ተጠቃሚ ሳይሆን ባለ እዳ እየሆነ ነው ብሏል።

የወጪ መጋራት ክፍያ የአንድ ተማሪ ዕለታዊ የምግብ ፍጆታ በ22 ብር ታስቦ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለመንግሥት እንዲከፍሉ ይደረጋል።

“ለተማሪ ጥቅም የለውም። ምክንያቱም የወጪ መጋራት ብቻ ነው እየጨመረ ያለው። 150 ብር እየተቀለበ የነበረ ተማሪ 22 ብር ብቻ የወጪ መጋራት ነው እየከፈለ የነበረው። አሁን በአራት ዓመት ለምግብ ብቻ 120 ሺህ ይከፍላል ማለት ነው” በማለት የተማሪዎቹን ተቃውሞ አብራርተዋል።

ተማሪዎቹ የምግብ በጀት መጨመሩን እንጂ “ምን ተጨመረ? ለምን ተጨመረ? እንዴት ተጨመረ? በቀጣይ እንዴት ይሆናል? የሚለውን ተማሪው የያዘው ነገር የለም” ሲሉም በበጀቱ አተገባበር ዙሪያ ተማሪዎች ዝርዝር መረጃ ስላልነበራቸው አለመግባባት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሕብረት የምግብ በጀት ማስተካከያው ውይይት ላይ እንደተሳተፈ እና ዩኒቨርስቲዎች የሚያደርጉት የምግብ በጀት ድጎማ እንዳይነሳ ጠይቆ እንደነበር ገልፀዋል።

ሕብረቱ በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ፕሬዝዳንቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከትምሕርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ውጤትን መሰረት አድርጎ በጀት እንደሚመድብ ያሳወቀ ሲሆን፤ ከ47ቱም ዩኒቨርስቲዎች ጋር “ቁልፍ የአፈፃፀም ውል” መፈራረሙን ገልጿል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop