ስለ ክትባት ያልተረጋገጡ የሴራ ትንተናዎችን የሚያሠራጩት ተጽእኖ ፈጣሪ ፓስተር Leave a comment

ታዋቂው ፓስተር ክሪስ ኦያኪሂሎሜ ወደ ካሜራው በቀጥታ እያዩ “ክትባቶች ስለመሥራታቸው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ተገኝቶ አያውቅም” ሲሉ ይናገራሉ።

ፓስተሩ በቤተ-ክርስቲያን ለተሰባሰቡ እና በዩቲዩብ በሚሠራጨው ስብከታቸው ላይ ሁሉም ሰው ስለክትባት ውሸትነት ይነገራዋል ይላሉ።

የ60 ዓመቱ ፓስተር ክሪስ በአፍሪካ እጅግ ዝነኛ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ የሃይማኖት ሰባኪያን መካከል አንዱ ናቸው።

ቢቢሲ እኒህ ፓስተር በ2023 እና 2024 መካከል ያደረጉትን ስብከቶች ከመረመረ በኋላ ፓስተሩ በተለይ ለአፍሪካ አገራት እየቀረበ ያለው የወባ በሽታ ክትባትን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ ለተከታዮቻቸው እያሠራጩ እንደሆነ ደርሶበታል።

የወባ በሽታ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ገዳይ ነው። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በዓለም በበሽታው ከሚሞቱ ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት መገኛቸው አፍሪካ ናት። ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎች ናቸው።

ፓስተር ክሪስ ክትባቶችን በተመለከተ ከሚያሰራጩት የተሳሳት መረጃ በተጨማሪ የሚመሩት ድርጅት ክትባትን የተመለከተ የ20 ደቂቃ ርዝመት ያላቸው ቢያንስ 5 ዘጋቢ ፊልሞችን (ዶክመንተሪ) ሠርቶ አሠራጭቷል።

“የሕዝብ ቁጥርን የመቀነስ ሴራ”

የጤና ሳይንስ ተመራማሪዎች በአፍሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል እውቅና የተሰጠው የወባ ክትባት በሽታውን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ።

ይሁን እንጂ የእኚህ ተደማጭ ፓስተር ዘመቻ የወባ ክትባት በሚፈለገው ደረጃ ሰዎች ጋር እንዳይደርስ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ስለ ክትባቶች ያልተረጋገጠ የትንተና ሴራ የሚያሰራጩ አካላት እንደሚሉት ሁሉ ፓስተሩም ሰዎች ክትባት እንዲወስዱ የሚደረጉት የዓለም የሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ስለሚፈለግ ነው ይላሉ።

ፓስተር ክሪስ በአንድ መድረክ ላይ “የወባ በሽታ ጭራሽ ለአፍሪካውያን ችግር ሆኖ አያውቅም” ሲሉም ተደምጠዋል።

“እንደዚህ ዓይነት ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ስለ ክትባት ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨታቸው ቀድሞ በነበረ ጥርጣሬ እና ስጋት ላይ ተደማምሮ በሕዝብ ጤና ላይ ከባድ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የወባ ክትባትን በአፍሪካ በይፋ ማሠራጨት ሲጀምር የፓስተር ክሪስ የሴራ ትንተና በክትባቱ አቅርቦት እና አጠቃቀም ላይ ችግር ሆኖ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ፓስተር ክሪስ ክትባትን በተመለከተ በሚሰጡት አስተያየት ከቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ይህ የሃይማኖት መሪ በናይጄሪያዋ ትልቋ ከተማ ሌጎስ “ክራይስት ኤምባሲ” የተሰኘ ቤተ-ክርስቲያንን እአአ በ1990ዎች ከመሠረቱ በኋላ በመላው ዓለም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል።

ፓስተሩ እአአ 2011 ላይ ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በማፍራት ከናይጄሪያውያን ባለጸጎች መካከል ተካተው ፎርብስ ላይ ወጥተው ነበር።

ፎርብስ ከፓስተሩ የገቢ ምንጮች መካከል የጋዜጣ እና መጽሔት ህትመት፣ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ሆቴሎች እና የመኖሪያ ቤቶች ልማት እንደሚገኙበት ገልጾ ነበር።

‘ላቭዎርልድ’ የተባለው የፓስተሩ ኩባንያ ከተጠቀሱት የንግድ ዘርፎች በተጨማሪ የጸሑፍ መልዕክት መለዋወጫን ጨምሮ ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችን ያበለጽጋል።

በፓስተር ክሪስ ቤተ-ክርስቲያን በየሳምንቱ አገልግሎት ተሳታፊ የሆነችው የ25 ዓመቷ ዊኒፍሬድ ኢከሂአኖሲን “በፍጹም ክትባት ለመውሰድ ፍቃደኛ አይደለሁም” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“የእግዚአብሔር ሰው ነግሮናል። እኔም በግሌ አጣርቻለሁ” ትላለች።

በኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አዳ ኡሜንዋሊሪ የጤና መሠረተ ልማት እና የጤና አገልግሎት እጅግ ደካማ በሆነባት አፍሪካ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ተከታዮቻቸው ጤናቸውን በተመለከት በሚወስዱት ውሳኔ ላይ ጉልህ ተጽእኖ አላቸው ይላሉ።

“ፓስተር ክሪስ እያራመዱ ያሉት አጀንዳ ከሃይማኖት ጨርሶ የማይገናኝ ከመሆኑም በላይ፤ እጅግ አደገኛ ስለሆነ ስጋቱ መታወቅ አለበት” ያሉት ደግሞ የፓስተር ክሪስ ቤተ-ክርስቲያን ለ10 ዓመታት ያህል አባል ሆነው የቆዩት ጁሊየስ ኦጉንሮ ናቸው።

በፓስተር ክሪስ አስተምህሮ ውስጥ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሱ አንድ ሰው አሉ። እኒህም ከዓለማችን ባለጸጎች መካከል አንዱ የሆኑት ቢል ጌትስ ናቸው።

ቢል ጌትስ ክትባቶች ላይ ለሚደረግ ምርምር እና ሥርጭት ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። በዚህም ምክንያት ክትባቶችን በተመለከተ የሴራ ትንተና በሚነዙ ሰዎች ዘንድ የቢል ጌትስ ስም በተደጋጋሚ ይነሳል።

ፓስተር ክሪስ ቢል ጌትስ እአአ 2010 በአንድ መድረክ ላይ ያደረጉትን ንግግር ቆርጠው ለተከታዮቻቸው በተደጋጋሚ ያስደምጣሉ።

በዚህ በተቆረጠ ቪዲዮ ላይ ቢል ጌትስ እንዲህ ሲሉ ይሰማሉ “. . . ዛሬ ላይ ዓለማችን 6.8 ቢሊዮን ሕዝብ አላት። ይህ ቁጥር ወደ 9 ቢሊዮን እየሄደ ነው። በክትባትን፣ በጤና እንክብካቤ፣ በሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላይ ጥሩ ብንሠራ 10 ወይም 15 በመቶ መቀነስ እንችላለን” ይላሉ።

ይህ የቢል ጌትስ ንግግር ከአውድ ውጪ ተወስዶ በክትባት እና በጤና ሥርዓት የሕዝብ ቁጥርን የመቀነስ ውጥን እንዳላቸው ተደርጎ ይገለጻል።

ይሁን እንጂ ቢል ጌትስ ደጋግመው እንደገለጹት ሐሳባቸው፤ ሰዎች የተሻለ የጤና ሥርዓት የሚያገኙ ከሆነ ያነሰ ልጆችን የመውለድ ፍላጎት ስለሚኖራቸው የሕዝብ ቁጥር ይቀንሳል የሚል ነው።

ፓስተር ክሪስ ከዚህ በተጨማሪም በኮሎምቢያ የሚገኘው የዓለም የወባ በሽታ መቆጣጠሪያ ፕሮግራም ማዕከል ንብረትነቱ የጌትስ ፋውንዴሽን መሆኑን በመጥቀስ፤ ማዕከሉ የዘረ መል ማሻሻያ የተደረገባቸው የወባ ትንኞችን አራብቶ የሕዝብ ቁጥር የመቀነስ ዕቅድ አለው ሲሉ ይናገራሉ።

ፓሰተር ክሪስ ካሉት በተቃራኒው ‘የወባ ትንኝ ፋብሪካው’ ባለቤትነቱ የአውስራሊያው ሞናሽ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ትንኞቹ የሚራቡትም የወባ ትንኞች የወባ በሽታ የማስተላለፍ አቅማቸውን እንዲቀንስ በማድረግ ነው።

ከወባ ክትባት በተጨማሪ ፓስተር ክሪስ ከዚህ ቀደም ፀረ ቴታነስ መርፌ፣ የፖሊዮ ክትባት እና የሕጻናት ክትባትን በተመለከተ ያልተረጋገጡ በርካታ የሴራ ትንተናዎችን ሲያሠራጩ ቆይተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የፓስተር ክሪስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዩናይትድ ኪንግደም የብሮድካስት ተቆጣጣሪ አካል (ኦፍኮም) የ125ሺህ ፓዎንድ ቅጣት ተላልፎበት ነበር።

ኦፍኮም ቅጣቱን የጣልኩት የቴሌቪዥን ጣቢያው ኮቪድ-19 እና ክትባቱን “የተመለከተ አሳሳች እና ጎጂ የሆነ መረጃ” ስላሠራጨ ነው ብሎ ነበር።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop