በሕንድ ሚስቱን ደፍሮ ለሞት ዳርጓል በሚል የተከሰሰው ግለሰብ በነጻ መለቀቁ ቁጣን ቀሰቀሰ……. Leave a comment

አንድ የሕንድ ፍርድ ቤት ከሚስቱ ጋር በግዳጅ “ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት” መፈጸሙ ጥፋት አይደለም በሚል ያስተላለፈው ውሳኔ ትልቅ ቁጣን ቀሰቀሰ።

የመብት ተሟጋቾችም ለባለትዳር ሴቶች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ አወዛጋቢ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በትዳር ውስጥ የሚፈጸምን መድፈር በሕንድ ዳግም ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሕንድ ማዕከላዊ ግዛት ቻቲስጋርህ የሚገኝ የከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2019 ባለቤቱን በመድፈር እንዲሁም ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት በመፈጸም፣ ከደፈራት ጥቂት ሰዓታት በኋላም የባለቤቱ ሕይወት በማለፉ ጥፋተኛ የተባለውን የ40 ዓመት ወንድ ከእስር ነፃ አውጥቶታል።

የስር ፍርድ ቤት ግለሰቡን “በቤት ውስጥ ጥቃት ነገር ግን ከነፍስ ማጥፋት ጋር ባልተያያዘ” ጥፋተኛ ብሎት ነበር።

በወቅቱ በቀረበበት በእያንዳንዱ ክስ “የ10 ዓመት ጽኑ እስራት” የተፈረደበት ሲሆን፣ ሁሉም ቅጣቶች በአንድ ላይ እንዲፈጸሙ ተደርገዋል።

ሰኞ ዕለት ግን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ናሬንድራ ኩማር ቪያስ፣ ሕንድ በትዳር ውስጥ መደፈርን ስለማትቀበል ባልየው ስምምነት የሌለው ወሲብ በመፈጸም ወይም በማንኛውም ስምምነት ላይ ያልተመሰረተ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወንጀል ጥፋተኛ እንደሆነ ሊቆጠር አይችልም በማለት በነጻ አሰናበተውታል።

በፍርድ ውሳኔው የተቆጡ የመብት ተሟጋቾች፣ ጠበቆች እና ተቆርቋሪዎች በሕንድ በትዳር ውስጥ መደፈርን ወንጀል ተደርጎ እንዲቆጠር ዳግም ጠይቀዋል።

የሕግ ባለሙያ እና የሥርዓተ-ፆታ መብት ተሟጋች ሱክሪቲ ቻውሃን “ይህ ሰው ነጻ ተብሎ ሲሰናበት ማየት ተቀባይነት የለውም። ይህ ፍርድ በሕጋዊ መንገድ ትክክል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከሥነ ምግባር አኳያ አስጸያፊ ነው” ብለዋል።

“አንድን ሰው ከእንዲህ ዓይነት ወንጀል፣ ወንጀል አይደለም በማለት፣ ነጻ የሚያደርገው ውሳኔ፣ በሕግ ስርአታችን ውስጥ በጣም ጨለማው ወቅት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በእጅጉ አስቆጥቶናል፤ ይህ በፍጥነት መለወጥ እና መለወጥ አለበት።”

በቻትስጋርህ የሕግ ጠበቃ የሆኑት ፕሪያንካ ሹክላ እንዲህ ያለው ፍርድ “ባል ስለሆንክ መብት አለህ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እና ማንኛውንም ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ነፍስ አጥፍተህ እንኳን ነጻ ልትወጣ ትችላለህ የሚል መልዕክት አለው” ብለዋል።

ፍርድ ቤት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሲያስተላልፍ አዲስ አለመሆኑን በመጥቀስ ሁልጊዜም ቁጣ እንደሚኖር አክለዋል።

“በዚህ ጊዜ ቁጣው የከፋ ነው፤ ምክንያቱም ወንጀሉ በጣም አሰቃቂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ተጎጂዋ ሞታለች።”

እንደ አቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ከሆነ ወንጀሉ የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በታህሳስ 11 ቀን 2017 ምሽት ላይ ሲሆን በሹፌርነት ይሰራ የነበረው ባል “ከትዳር አጋሩ ፍላጎት ውጪ፣ ከእርሷ ጋር ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽሟል… ብዙ ስቃይም አድርሶባታል።”

ወደ ስራው ከሄደ በኋላ ከእህቱ እና ከሌላ ዘመድ ጋር በመሆን ወደ ሆስፒታል ብትሄድም ሕይወቷ አልፏል።

ሟች በወቅቱ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል “ባለቤቷ ጉልበት የተቀላቀለበት የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸሙ ምክንያት” መታመሟን ተናግራለች።

የሕግ ባለሙያዎች ይህ የሟች ቃል በፍርድ ቤት ክርክር ወቅት ክብደት የሚሰጠው ነው ያሉ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያዎች በሌሎች ማስረጃዎች ካልተቃረኑት በስተቀር ለአጠቃላይ ፍርድ በቂ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

እ.ኤ.አ. በ 2019 ግለሰቡ የጥፋተኝነት ፍርድ በተላለፈበት ወቅት፣ የመጀመሪያው ፍርድ ቤት ከሟች የተወሰደውን ቃል እንዲሁም ሆስፒታል ያቀረበውን የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከግንዛቤ አስገብቷል።

በወቅቱ የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ የግለሰቧ ሞት መንስኤ “የሆድ እቃ መቆጣት እና የፊንጢጣ ቀዳዳ መበሳት” መሆኑን አሳይቷል።

ዳኛ ቪያስ ግን ጉዳዩን በተለየ መንገድ አይተውታል።

ሟች የሰጠችውን ቃል “እውነተኝነት” ጥርጣሬ ውስጥ የከተቱት ዳኛው፣ አንዳንድ ምስክሮች ቃላቸውን መቀየራቸውን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕንድ በትዳር ውስጥ መድፈር ወንጀል አለመሆኑን ተናግረዋል።

የስር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ “በጣም አልፎ አልፎ የሚገጥም ጉዳይ ነው” የሚሉት ሹክላ “ምናልባት ሴትየዋ ስለሞተች” ነው ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ነገር ግን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን አስደንጋጭ የሚያደርገው ከዳኛው አንድ እንኳን ርህራሄ የተሞላበት አስተያየት አለመስጠቱ መሆኑን ይገልጻሉ።

የጥቃቱን ዓይነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዳኛው ጉዳዩን በቀላሉ ውድቅ ማድረግ አልነበረባቸውም ብለው ለሚያምኑ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስደንጋጭ ሆኗል።

ሕንድ በትዳር ውስጥ መደፈር ወንጀል ካልሆነባቸው የዓለማችን 30 አገራት ውስጥ አንዷ ናት።

ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን እና ሳዑዲ አረቢያ እንዲሁ በትዳር ውስጥ የሚፈጸም መድፈር ወንጀል አይደለም።

በሕንድ በትዳር ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተስፋፍተዋል።

መንግሥት በቅርቡ ባደረገው ጥናት 32 በመቶ ያገቡ ሴቶች በባሎቻቸው አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

82% የሚሆኑት ደግሞ በባሎቻቸው ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ለሹክላ ይህ የችግሩን ትክክለኛ መጠን አያሳይም፤ ምክንያታቸው ደግሞ አብዛኞቹ ሴቶች ጥቃት በተለይም ጾታዊ ጥቃት ደርሶብኛል ለማለት ስለሚያፍሩ ሪፖርት አያደርጉም የሚል ነው።

“በእኔ ልምድ ሴቶች ቅሬታ ሲያቀርቡ አይታመኑም፤ ሁሉም ሰው ውሸት መሆን አለበት ይላል። እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች በቁም ነገር የሚወሰዱበት አንዲት ሴት ስትሞት ወይም ጥቃቱ አሰቃቂ ሲሆን ነው” ይላሉ።

ቻውሃን ሕጉ እስካልተለወጠ ድረስ ምንም ነገር እንደማይለወጥ ያምናሉ።

“በትዳር ውስጥ መደፈርን ወንጀል ልናደርገው ይገባል። ሚስት ከእንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ ክስተት በኋላ ፍትህ የማታገኝ ከሆነ አገር አቀፍ ዘመቻ ማድረግ ግድ ይላል።”

መንግሥት እና የወንዶች መብት ተቆርቋሪዎች “በወንድ እና ሴት መካከል የሚደረግ ክርክር” አድርገው ለማቅረብ እንደሚሞክሩም ጨምረው ተናግረዋል።

“ነገር ግን በትዳር ውስጥ መደፈርን ወንጀል የማድረግ ጥያቄ ከወንዶች በተቃራኒ የቆመ ሳይሆን የሴቶችን ደህንነት እና ምቾት ለመጠበቅ ነው፤ የሴቶችን ደህንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ አይደለም?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop