በሰሜን ሸዋ ዞን በትምህርት ቤት በደረሰ የድሮን ጥቃት መምህራንን ጨምሮ አምስት ሠዎች ቆሰሉ Leave a comment

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ ጉሎ በተባለ ትምህርት ቤት እሁድ ግንቦት 4፤ 2016 ዓ.ም. በደረሰ የድሮን ጥቃት የወላጅ መምህራን ህብረት (ወመህ) ስብሰባ ላይ የነበሩ ሠላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞችና የተጎጂ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከቀወት ወረዳ ዋና መቀመጫ ሸዋ ሮቢት በግምት 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የጉሎ (ጎጥ) አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቀኑ 7፡30 ገደማ ደርሷል በተባለው የድሮን ጥቃት አራት ሠዎች ሲገደሉ አምስት ሠዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱ የደረሰው መምህራንና የአካባቢው ማሕበረሰብ የወላጅ መምህራን ህብረት (ወመህ) ስብሰባ ላይ በነበሩበት ቅጽበት መሆኑን የተናገሩ አንድ የስብሰባው ተካፋይ፤ በጥቃቱ እሳቸውም ጭንቅላታቸው ላይ እንደቆሰሉ ገልጸዋል።

“ሩቢላ [አውሮፕላን] ነው የመሰለን፤ [ድሮኑ] አንድ ሁለት ሦስቴ ዞሮናል” ሲሉ ጥቃት አድራሹ ድሮን መሆኑን አለማወቃቸውን የተናገሩት የዐይን እማኙ፤ “ተቀምጠን ስንወያይ ከየት እንደመጣ አላወቅነውም። እላያችን ላይ ሲያርፍ ብቻ ነው ያወቅነው” ሲሉ ስለ ጥቃቱ ገልጸዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ የት/ቤቱ ዙሪያ ላይ የነበሩ ሠላማዊ ሠዎች እንደሆኑ እማኙ ተናግረዋል።

“ሁለቱ ከእኛ ጋር አብረው እየተሳተፉ ነበር። እነኛ ግን የቀን ሰራተኞች [አርሶ አደሮች] ናቸው። ከትምህርት ቤቱ አጥር ውጭ ነው ቁጭ ያሉት። ከአጥሩ ዘሎ ነው ሁለቱን የመታቸው” ሲሉ ስለ ጥቃቱ ተናግረዋል።

በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩና የአንዱ ሟች የቅርብ ቤተሰብ የሆኑ ግለሰብ፤ እርሳቸው ፈንጠር ብለው በመቆማቸው በፍንዳታው ግፊት መውደቃቸውን ገልጸው፤ ጥቃቱ ዱብዕዳ እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በጊዜው ሰማይና ምድር ነው ያለፈብኝ። አይቼም ሰምቼም አላውቅም። የምንጠረጥርበት ቦታ [አስጊ ቦታ] ላይ ቢሆን እናስብበታለን። ምንም በሌለበት ቦታ ላይ ነው እንደዚህ የተሰራነው” ሲሉ ጥቃቱንና ሁኔታውን ገልጸዋል።

ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ሟች በግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ የ30 ዓመት ወጣት እንደነበረ ቤተሰቡ ተናግረዋል።

ከትምህርት ቤቱ አጠገብ ያለን የመስኖ ውሃ ለመጠቀም ወደ ትምህርት ቤቱ መጥቶ እያለ ጥቃቱ እንደተፈጸመ የተናገሩ ሲሆን፤ “ተስፋ አስቆራጭ” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

“ልጁ ታታሪና የዋህ ነው፤ ምንም የማያውቅ” ሲሉ ሟቹን ገልጸውታል።

ስርዓተ ቀብሩ የጥቃቱ ቀን እሁድ ዕለት 10 ሰዓት አካባቢ እግዚአብሄር አብ በተባለ ቤተ-ክርስቲያን እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

በጥቃቱ የመምህራን ሕይወት ባይጠፋም ሦስት መምህራን (አንድ ወንድ ሁለት ሴት መምህራን) እንደቆሰሉ ሌላ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው ወደ አካባቢው በፍጥነት እንዳመሩ የተናገሩ አንድ የዐይን እማኝ እንደደረሱ አስከሬን ማየታቸውን ጠቅሰው፤ የአራት ሠዎች ሕይወት ማለፉንና በርካታ ሠዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

“የሞቱት ሠዎች ገበሬዎች ናቸው። እዛው ከትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ሙዝ፣ አትክልትና መስኖ ልማቶች ላይ የሚሰሩ ናቸው። እንዲሁም እዛው ትምህርት ቤቱ ውስጥ የምትሰራ አንዲት መምህር ቆስላለች። ሁለት ገበሬዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለዋል።

የዐይን እማኙ በስፍራው ከደረሰው አካባቢው ማሕበረሰብ ጋር ቁስለኞችን እንዳነሱ ገልጸው፤ ጉዳት የደረሰባቸው ሠዎች ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

“መምህሯ ሆስፒታል ገብታ ነበር። ሪፈር ብለው ልከዋታል። . . . የእሷ ከበድ ያለ ጉዳት ነው። እስካሁን ሞታለች የሚል [ነገር] አልሰማሁም። ሌላው ከባድ ጉዳት ያለው አንድ አርሶ አደር እዚሁ [ተሬ ቀበሌ] እየታከመ ነው። አንደኛው አርሶ አደር ቀለል ያለ ጉዳት ነው። ብዙም ለስጋት የሚጥለው እንዳልሆነ ሰምቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከቁስለኞቹ ውስጥ በ70ዎቹ አጋማሽ ይገኛሉ የተባሉ የትምህርት ቤቱ “አጋዥ” የነበሩ ሽማግሌ እንደሚገኙበት አንድ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

በሸዋ ሮቢት ዙሪያ የፋኖ ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ ለቢቢሲ የተናገሩት አንድ የዐይን እማኝ፤ ጥቃቱ ሲደርስ ግን በአካባቢው እንዳልነበሩ እና ከመንግሥት ኃይሎችም ጋር የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበር ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው በፋኖና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እንደነበሩ ያስታወሱት የዐይን እማኙ፤ “በቅርብ ጊዜ [ግን] በአካባቢው [ጉሎ] ፋኖ ሲንቀሳቀስ አይተን አናውቅም” ብለዋል።

በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች እንዳልነበሩ ያረጋገጡት ሌላ እማኝ፤ ጥቃቱ ለምን ሠላማዊ ሠዎች ላይ እንደተፈጸመ “ጥያቄ ሆኖብኛል” ብለዋል።

“ይሄ [ትምህርት ቤቱ] የመንግሥት መዋቅር ነው። መሰረተ ልማት ነው። እንዴት የመሰረተ ልማት ኃላፊዎችን ሊመታን ቻለ? ብዬ ጥያቄ ነው የሆነብኝ” በማለት ትምህርት ቤቱ ኢላማ መሆኑ እንዳልገባቸው ገልጸዋል።

“የ8ተኛ ክፍል አራት መማሪያ ክፍል ነበር፤ በመስታወት በዲዛይን የተሰራ። እሱን ፍርስርስ አድርጎታል። ከ1ኛ እስከ 7ተኛ ያለው [መማሪያ ክፍል] ቆርቆሮውን ሁሉ ብጭቅጭቅ ነው ያደረገው። የተጣለው አንድ ጥይት ነው። አንድ ጥይት ነው ወይ የመታው ብሎ ውሳኔ ለመስጠት እንኳን ይከብዳል። ከአካባቢው ዙሪያው መስኖ ስለሆነ ማንጎ አለው፤ ዋንዛ ዛፍ አለው፤ ሙዝ አለው፤ ሸንኮራ አለው። ይሄን ሁሉ ውድምድም ነው ያደረገው” ሲሉ ጥቃቱ ንብረት ላይ ስላደረሰው ጉዳት ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ ማስተማር ካቆመ አንድ ወር ገደማ በመሆኑና ጥቃቱ የደረሰው እሁድ በመሆኑ ጉዳቱ ከባድ እንዳይሆን ማድረጉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

አካባቢው በስጋት እንደተወጠረ የተናገሩት አንድ እማኝ፤ በነዋሪው ዘንድ ዳግም ጥቃት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ተናግረዋል።

“አካባቢው ስጋት ላይ ነው። እንደዚሁ አይነት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ስጋት ስላለ እንደ በፊቱ መስመር ላይ ወጣቶቹ ውር ውር [አይንቀሳቀሱም] አይሉም። [ድሮን] ይጥላል የሚል እሳቤ ስላላቸው አሁን ዋናው ቀበሌው ላይ [ተሬ] መሰብሰብ ሁኔታ የለም። እና ስጋት ስላለ ከክስተቱ በኋላ የመሰብሰብ ሁኔታ የለም” ሱሉ አሁናዊ አካባቢውን ሁኔታ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኀይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባለው ግጭት በተለያዩ ቦታዎች የድሮን ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፤ ጥቃቶቹ የሠላማዊ ሠዎችን ሕይወት መቅጠፋቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ባለፈው ታህሳስ ወር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በድሮን ጥቃቶች ንጹሃን እየተገደሉ ነው መባሉን አስተባብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የድሮን ጥቃት የሚፈጽመው የፋኖ ታጣቂዎች “ስብስብ ዒላማ” ላይ መሆኑን በመጥቀስ “ሕዝብ ላይ ድሮን አይጣልም፤ አይተኮስም። መንደር ላይ እንኳ አይተኮስም። የጠላት ስብስብ ሲገኝ ግን ይተኮሳል” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop