በቅርቡ የተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት የትርጉም ጥያቄ ቀረበበት…… Leave a comment

በቅርቡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥትን እና የክልሉን ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት ያሻሻሉት አዋጆች “ያልነበሩ፣ ያልተደነገጉ እንዲባሉ” እና “ተፈጻሚ እንዳይሆኑ” የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ቀረበባቸው።

የትርጉም ጥያቄውን ለአገሪቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረቡት ከተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተመረጡ ሦስት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ናቸው።

አባላቱ የክልሉ ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት በአብላጫ ድምጽ ያጸደቃቸው እነዚህ ሁለት አዋጆች “ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ያልነበሩ፣ ያለተደነገጉ እንዲባሉ” እና “ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ተብለው” እንዲወሰኑ ዳኝነት ጠይቀዋል።

ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ዳኝነት የተጠየቀባቸው አዋጆች የመጀመሪያው “የየእርከኑ ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት መወሰኛ” የወጣው አዋጅ እና የክልሉን ሕገ መንግሥት እንደገና ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ነው።

የዛሬ ሁለት ሳምንት የጸደቀው “የየእርከኑ ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት መወሰኛ” አዋጅ 99 የነበረውን የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ ብዛት ወደ 165 አሳድጎታል።

ይህ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ለውጥ በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ላይም ተንጸባርቋል።

“ጠቅላላ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ከአንድ መቶ አይበልጥም” የሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ተሰርዟል። በምትኩ “ጠቅላላ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ165 መብለጥ የለበትም” የሚል አዲስ ንዑስ አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቷል።

ማሻሻያው በአንድ ምርጫ ክልል የሚመረጡ ተወካዮች ብዛትም ከ5 እስከ 11 የሚደርሱ እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በነበረው ሕግ ከአንድ ምርጫ ክልል የሚመረጡ የክልል ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት ከ4 እስከ 6 ነበር።

የተሻሻለው 165 የክልል ምክር ቤት መቀመጫ “የሕዝብ ብዛትን ያላማከለ” መሆኑን የጠቀሱት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጠያቂዎቹ፤ “ነባር ምርጫ ክልሎች የፈረሱበት እና አዳዲስ ምርጫ ክልሎች የተቋቋሙበት ሂደት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ” መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም “አድሏዊ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥልጣን እና ተግባርን የተጋፋ ነው” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የቀረበው አቤቱታ “ክልሉ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ፈጥኖ መግባቱ አገራዊ ምክክሩን ዓላማ የሚጋፋ ጭምር” መሆኑን ያትታል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ ሁለት አዳዲስ የክልሉ አዋጆች በአራት ምክንያቶች የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥባቸው ጠይቀዋል።

የመጀመሪያው ምክንያት የየእርከኑ ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት መወሰኛ አዋጅ ነባር ምርጫ ክልሎችን አፍርሶ አዲስ ምርጫ ክልል ማካለሉ ነው።

የክልሉ ምክር ቤት “ሥልጣን ሳይኖረው ቀደም ሲል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቋቋሙትን” ሦስት የምርጫ ክልሎች አፍርሶ አምስት አዲስ ምርጫ ክልሎችን ማቋቋሙን አቤቱታ አቅራቢዎቹ አመልክተዋል።

አዲስ የተቋቋሙት የምርጫ ክልሎች አብራሞ፣ ኡራ፣ ኡንዱሉ፣ አሶሳ ከተማ ወረዳ አንድ እና አሶሳ ከተማ ወረዳ ሁለት ናቸው።

“ለአስተዳደር ተብሎ የተቋቋሙት እነዚህ አምስት ወረዳዎች እንደ ምርጫ ክልል ተቆጥረው 31 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ተሰጥቷቸዋል” ሲል ማመልከቻው ያትታል።

“የምርጫ ክልል አከላለልን በተመለከተ ክልሎች ሥልጣን የላቸውም። ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን የክልል ምክር ቤት የመቀመጫ ጥቅል ብዛትን መወሰን እና የአካባቢ ምርጫን የሚመለከት ነው” ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ “የክልሉ ምክር ቤት ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መርኅ ጥሷል” ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቁጥር ማሻሻያ “የሕዝብ ብዛትን መሠረት ያላደረገ ነው” የሚለው ሁለተኛው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲጠየቅ ምክንያት የሆነ ጉዳይ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምክር ቤት መቀመጫ ወንበሮችን “በሕዝብ[ብዛት ሳይሆን በወረዳ ቁጥር አከፋፍሏል” ያለው አቤታታው፤ ይህ “ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን መተላለፍ” እንደሆነ ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም “እያንዳንዱ ወረዳ ያለውን የሕዝብ ብዛት ወደ ወንበር መቀየር ሲገባ አነስተኛ ቁጥር ላለው ወረዳ በርካታ መቀመጫ፤ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ወረዳዎች ደግሞ አነስተኛ መቀመጫ ተሰጥቷል” ሲል ተችቷል።

በኢትዮጵያ እንዲሁም በክልሉ ሕገ መንግሥት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት አባላት ቁጥር የሕዝብ ብዛትን መሠረት ያደረገ ነው።

ሦስተኛው ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ካለው የሕግ ማውጣት ሥልጣን ወሰን ጋር የተያያዘ ነው።

“የክልሉ ምክር ቤት ባልተሰጠው ሥልጣን የጠቅላላ እና የአካባቢ ምርጫን አቀላቅሎ አዋጅ አውጥቷል” ሲል ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የቀረበው ማመልከቻ ያትታል።

የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲጠየቅ ምክንያት የሆነው አራተኛው እና የመጨረሻው ምክንያት ከወረዳ ምክር ቤቶች የሥልጣን ጊዜ ጋር የተያያዘ ነው።

በአቤቱታው መሠረት የክልሉን ሕገ መንግሥት የተወሰኑ ክፍሎች ለማሻሻል በሁሉም የወረዳ ምክር ቤቶች በሁለት ሦስተኛ ድምጽ እና በክልሉ ምክር ቤት ደግሞ በአብላጫ ድምጽ መጽደቅ አለበት።

ነገር ግን አሁን ያሉት እና በ2005 ዓ.ም. የተመረጡት የወረዳ ምክር ቤቶች የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን ስላጠናቀቁ የሁሉም ወረዳ ምክር ቤቶች የሥልጣን ጊዜ አብቅቷል።

“የአካባቢ ምርጫ ተካሂዶ የወረዳ ምክር ቤቶች ስላልተመረጡ አሁን ያሉት ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም። ተሰብስበው ሕጋዊ ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም” ሲል አቤቱታው አብራርቷል።

ይህን ተከትሎ የክልሉ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ “ሕጋዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን በሌለው አካል የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ ኢ ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አስረድተዋል።

የክልሉ ሕገ መንግሥት ከምክር ቤት አባላት ቁጥር በተጨማሪ የክልሉን ዓርማ ላይ ለውጥ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ በሕገ መንግሥት “በርታ” በሚል የጠቀሰውን ብሔረሰብ ስያሜ “ቤኒሻንጉል” በሚል ቀይሮታል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የ”በርታ” ብሔረሰብ ስያሜ ወደ “ቤኒሻንጉል መቀየሩ” ይታወሳል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop