አንድ ፈረንሳያዊ በተሰረቀበት ክሬዲት ካርድ (የባንክ ካርድ) በተገዛ ሎተሪ ከፍተኛ ሽልማት አሸናፊ በመሆኑ ክሬዲት ካርዱን የሰረቁት ሌቦች የሎተሪ ትኬቱን ይዘው ከቀረቡ ሽልማቱን እኩል ለመካፈል ፈቃደኛ መሆኑን አስታወቀ።
በተሰረቀው ክሬዲት ካርድ ፈጣን ሎተሪ የቆረጡት ሌቦች ዕድለኛ ሆነው ከፍተኛ የተባለውን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽልማት አሸናፊ ቢሆኑም፣ ትኬቱ የተገዛበት ክሬዲት ካርድ ባለቤት እነሱ ባለመሆናቸው ሽልማቱን መውሰድ አይችሉም።
እራሱን ዣን ዴቪድ በማለት ያስተዋወቀው የክሬዲት ካርዱ ባለቤት ለአንድ ሬዲዮ ጣቢያ እንደተናገረው በእሱ እና በሌቦቹ መካከል ስምምነት ተደርሶ የሎተሪ ሽልማቱን ገንዘብ መቀበል ካልቻሉ ከቀናት በኋላ ዕጣው አሸናፊ እንደሌለው ተቆጥሮ ተመላሽ ይሆናል።
“ካለእኔ ክሬዲት ካርድ [ሌቦቹ] አሸናፊውን ሎተሪ አይገዙም፣ ካለ እነሱ ደግሞ እኔ ሎተሪውን ልቆርጥ አልችልም። ስለዚህ ሽልማቱን ከእነሱ ጋር ለመካፈል ዝግጁ መሆኔን ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ” ብሏል ግለሰቡ።
እስካሁን ድረስ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽልማት የሚያስገኘውን የሎተሪ ሽልማት ያሸነፈውን ትኬት የያዘ ሰው ሽልማቱን ለመረከብ ወደ ፈረንሳይ ብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት አለመቅረቡ ታውቋል።
ዣን ዴቪድ ክሬዲት ካርዱን የያዘው ቦርሳው ከመኪናው ውስጥ የተሰረቀበት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። ይህንንም ለባንኩ ሲያሳውቅ በክሬዲት ካርዱ በአቅራቢያው ከሚገኝ ሱቅ ወደ 50 ዶላር ወጪ ተደርጎ ግዢ መፈጸሙ ተነግሮታል።
ከዚያም ወደ ሱቁ በመሄድ ሌቦቹ ሌሎች እቃዎቹን ትተዋቸው ሄደው እንደሆነ በጠየቀበት ጊዜ የሱቁ ገንዘብ ተቀባይ ሁለት ጎዳና ላይ የሚኖሩ የሚመስሉ ሰዎች በክሬዲት ካርዱ ሲጋራ እና በርካታ የፈጣን ሎተሪ ትኬቶች ገዝተው መሄዳቸው ተነግሮታል።
ሁለቱ ሌቦች በተጨማሪም ከገዟቸው የፈጣን ሎተሪ ትኬቶች መካከል በአንዱ የግማሽ ሚሊዮን ዶላር ዕጣ አሸናፊ መሆናቸውን እና ወደ ሎተሪ ተቋሙ ሄደው ሽልማታቸውን እንደሚወስዱ እንደነገሯት የሂሳብ ባለሙያዋ ተናግራለች።
ከዚህ በኋላ ወደ ፖሊስ በመሄድ ያጋጠመውን ለአካባቢው ፖሊስ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ ፖሊስም በበኩሉ ለሎተሪ ድርጅቱ ክስተቱን በማሳወቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በሎተሪ ድርጅቱ አሠራር መሠረት አንድ የፈጣን ሎተሪ አሸናፊ የገንዘብ ሽልማቱን ትኬቱን ከገዛበት እስከ 30 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ቀርቦ ካልወሰደ አሸናፊነቱ ውድቅ ይሆናል።
በዚህም የተነሳ በሌቦቹ እና በክሬዲት ካርዱ ባለቤት መካከል ስምምነት ተደርሶ አሸናፊውን የሎተሪ ትኬት ይዘው በመቅረብ ገንዘቡን ለመረከብ ያላቸው ቀነ ገደብ እያለቀ ነው።
ነገር ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ቢደረስ ትኬቱን የያዙት ሁለቱ ሰዎች በሌብነት በፖሊስ መያዛቸው አይቀርም፤ በዚህም ሳቢያ ትኬቱን እንደያዙ ተደብቀው ሊቀሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
የክሬዲት ካርዱ ባለቤት ጠበቃም በሁለቱ መካከል ስምምነት ተደርሶ ሌቦቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ሐሳብ አቅርቧል።
“በዚህ ሁኔታ ደንበኛዬ ክሬዲት ካርዱ በመሰረቁ በጣም ደስተኛ ነው፤ ስለዚህም በሌቦቹ ላይ ምንም ዓይነት ክስ አይመሠርትም። በተጨማሪም ይህ ገንዘብ ሁለቱ ሰዎች አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ነው” ስምምነት እንዲደረስ ጠይቋል።
ሌቦቹ “ከጠበቃዬ ጋር በመገናኘት ገንዘቡን እንድናገኝ ካላደረጉ አሸናፊው የሎተሪ ትኬት ዋጋ አይኖረውም። ስለዚህም ጉዳዩን በስምምነት በመፍታት ሽልማቱን ለምን ግማሽ ግማሽ አንካፈለውም?” ሲል ፍላጎቱን ገልጿል።
ክሬዲት ካርዱ የተሰረቀበት ዣን ከሌቦቹ ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ የሎተሪ ሽልማቱን እኩል በመካፈል የሚያገኘውን ከ250 ሺህ ዶላር በላይ የሚሆነውን ገንዘብ ያለበትን የባንክ ብድር ለመከፈል እንደሚያውለው ተናግሯል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)