በአንድ ሳምንት ውስጥ የብር የመግዛት አቅም ከ57 በመቶ በላይ ተዳከመ……. Leave a comment

የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ57.93 በመቶ ተዳከመ።

ከአንድ ሳምንት በፊት አርብ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም 57.48 ብር ነበረው አንድ የአሜሪካን ዶላር የመግዣ ዋጋ አርብ ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም. ረፋድ ከ90 በላይ የኢትዮጵያ ብር አሻቅቧል።

ብሔራዊ ባንክ አዲሱን ፖሊሲ ይፋ ባደረገ ማግስት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር አንጻር ያለው የመግዛት አቅም በ30 በመቶ ተዳክሞ ነበር። የብር የመግዛት አቅም ባለፉት አምስት ቀናት በየቀኑ እየተዳከመ መጥቷል።

የግል ባንኮች አርብ ዕለት ረፋድ ይፋ ባደረጉት የውጭ ምንዛሪ ተመን መሠረት አንድ የአሜሪካን ዶላር ባለፉት ቀናት ከ33 ብር በላይ ጨምሮ ከ90 ብር በላይ እየተመነዘረ ነው።

የዶላር የመሸጫ ዋጋ በባንኮች መካከል ልዩነት አሳይቷል። ዝቅተኛው የመሸጫ ዋጋ የተመነው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን ይኸውም 85.6 ብር ነው። ዳሽን ባንክ ደግሞ ከፍተኛ የሆነውን 98.05 ብር የመሸጫ ዋጋ ይፋ አድርጓል።

ግራፍ

ከአዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያ መውጣት በኋላ ባንኮች የምንዛሪ ተመናቸውን በቀን ሁለት ጊዜ እስከ መከለስ ደርሰው ነበር። ንግድ ባንክ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. ለሁለት ጊዜ ያህል የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ አድርጓል።

ይህን ፈጣን የሆነ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተችተውታል። ዐቢይ ሐሙስ ዕለት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመመለከተ ከመንግሥት ኃላፊዎች እና ከባንክ ፕሬዝዳንቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ “[ባንኮችን] አሁን የሄዳችሁበት ያለው የዋጋ መጠን ትክክልኛ እርምጃ አይመስለንም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ ያልነው በጥቁር ገበያው እና በዋናው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ጉልህ መሆን የለበትም ነው እንጂ፤ እናንተ [ባንኮች] ሰባ ስትገቡ እነሱ [ጥቁር ገበያው] 130 ከገቡ ምን ለውጥ አለው ተሠራው ሥራ በቂ አይደለም፤ ይሄ ንግግር ይፈልጋል፤ የጥቁር ገበያን የሚቀይር አካሄድ መከተል አለብን” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አካል ነው።

ባለፈው ሰኞ ተግባራዊ መደረግ ለጀመረው ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ የሚውል 3.5 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ወዳጅ አገራት “በድጋፍ” እና በሌሎች አማራጮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቆ ነበር።

መንግሥት ያስተዋወቀው የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ተዋንያን እንዲወሰን ክፍት ማድረጉ ብር ትክክለኛው የመግዛት አቅሙ ላይ እንዲደርስ በማድረግ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ያደርጋል የሚል ዕምነት አለው።

ሌሎች ደግሞ ይህ የብርን የመግዛት አቅምን በፍጥነት የሚያዳክመው ውሳኔ በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በማባባስ ሸማቹን ማኅበረሰብ ለበለጠ ችግር ይዳርገዋል ሲሉ ይተቻሉ።

ይህን እርምጃ ለመደገፍም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ድጋፍ የሚውል በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ለማቅረብ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop