ናይጄሪያዊው አዴሞላ ሉክማን አስደናቂ ሀት-ትሪክ በመሥራት አታላንታ የአውሮፓ ሊግ ባለድል እንዲሆን አስችሏል።
የጣሊያኑ ክለብ አታላንታ ከ61 ዓመታት በኋላ ዋንጫ ሲያነሳ ባየር ሌቨርኩሰን የውድድር ዓመቱን ያለምንም ሽንፈት ለማጠናቀቅ የነበረው ሕልም ተቀጭቷል።
ደብሊን በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታው የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ደምቀው ታይተዋል።
አታላንታ ለአውሮፓ ሊግ ፍፃሜ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን የጀርመኑ ክለብ ሌቨርኩሰን ደግሞ ሶስተኛው ነው።
በአሠልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የሚመራው ባየር ሌቨርኩሰን ባለፉት 51 ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን የውድድር ዘመኑን ያለምንም ሽንፈት ለማጠናቀቅ የቀረው ሁለት ጨዋታ ብቻ ነበር።
ነገር ግን ናይጄሪያዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች ሉክማን ይህ እንዲሆን አልፈቀደም።
የመጀመሪያውን ጎል በ12ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር፤ ሁለተኛውና የጨዋታው ድንቅ የተባለውን ጎል በ26 ደቂቃ አስቆጥሯል። በሁለተኛው አጋማሽ በ75ኛው ደቂቃ ሶስተኛ ጎል በማከል የሌቨርኩሰንን ቅስም ሰብሯል።
ጎል ቢቆጠርባቸው እንኳ የጎል ዕዳቸውን አካክሰው ማሸነፍ አሊያም አቻ መውጣት ባሕላቸው የነበረው የሌቨርኩሰን ተጫዋቾች ረቡዕ ምሽት ያንን ማድረግ አልቻሉም።
የአታላንታው አሠልጣኝ ጂያን ፒዬሮ ጋስፔሪኒ ተጭነው በመጫወት ሌቨርኩሰን እንደልብ እንዳይንሸራሸር በማድረግ ታክቲካዊ የበላይነታቸውን አስመስክረዋል።
አታላንታ የአውሮፓ ሊግ ዋንጫን ከማንሳታቸውም በላይ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ጋስፔሪኒ በአውሮፓውያኑ 2016 አሠልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላ አታላንታ የአውሮፓ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ቢችሉም ዋንጫ ሲያነሱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ጋስፔሪኒ በኮፓ ኢታሊያ ሶስት ጊዜ ለፍፃሜ ደርሰው ሶስቱንም ተሸንፈዋል። ባለፈው ሳምንት በኮፓ ኢታሊያ ፍፃሜ በጁቬንቱስ መረታታቸው ይታወሳል።
ምንም እንኳ ሌቨርኩሰን የአውሮፓ ሊግን ሊያነሱ ጫፍ ደርሰው ቢመለሱም ያሳለፉት የውድድር ዘመን አስደናቂ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
የዣቪ አሎንሶ ቡድን አንድ ጨዋታ ሳይሸነፍ የጀመርን ቡንደስሊጋን በማንሳት የመጀመሪያው ክለብ ነው። ነገር ግን ከ361 ቀናት በኋላ የመጀሪያውን ሽንፈት ቀምሰዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡- (BBC)