“ብልጽግናዎች ይዘውን እንዲጠፉ አንፈቅድም፤ አገራችን ሕዝባችን ነው፤ ዝም አንላቸውም” – ጃዋር መሐመድ……. Leave a comment

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ፖለቲከኞች መካከል ጃዋር መሃመድ አንዱ ነው። ለዓመታት ያህል በኦሮሚያ የነበሩ ትግሎችን እንዲሁም ተቃውሞዎችን ከጀርባም ሆነ ከፊት ሆኖ በማስተባበር እና በመምራት ግንባር ቀደም ነው።

ሰላማዊ ትግልን እንደ ስልት የያዘው ጃዋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞን በመምራት ስሙ ይጠቀሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ስርዓቱን በቅርብ ርቀት በሰላ ሲተች ቆይቶ ነበር።

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያን ተከትሎ በተነሳው ግርግር ሳቢያ ከተገደለ ፖሊስ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበት የነበረው ጃዋር በእስር ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ አሳልፏል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራሩ ጃዋር ከትውልድ አንስቶ በፖለቲካ ህይወቱ የተጓዘበትን ህይወቱ ላይ የሚያጠነጥን ‘አልጸጸትም’ የተሰኘውን መጽሐፍ ታህሳስ 10/ 2017 ዓ.ም በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ያስመርቃል።

ጃዋር መሃመድ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስለሚኖረው ሚና፣ አገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ጃዋር፡– ዐቢይ ከመጀመርያውም መስመር ላይ አልነበረም። . . . [መጀመርያ አካባቢ] እኛ ከህወሓቶች ጋር እንደራደር ነበር፤ ስልጣን እንደሚለቁ፤ ማዕከላዊ ስልጣን እንደሚለቁ፣ ስምምነት ላይ ከደረስን በኋላ፣ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ማን ይሁን? የሚለው ሲመጣ የዐቢይ ስም በመምጣቱ አነጋግሬው ነበር።ያኔ ለእኔ ግልጽ ነበር።

ኢትዮጵያ ከኢህአዴግ አንድ ፓርቲ አገዛዝ፣ ወደ መድብለ ፓርቲ፣ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሄድ፣ መሻገር ነበረባት፤ ወደ ግጭት የማያደርስ ያለው ብቸኛ አማራጭ እርሱ ብቻ ነበር።

ገና ስልጣን ሳይይዝ፣ገና ስሙም ሳይታወቅ፣ለእኔ ከእርሱ ጋር በነበረኝ ውይይት የዲሞክራሲ ስርዓት የመገንባት ፍላጎት እንደሌለው ግልጽ ነበር።አምባገነናዊ ስርዓትን ከአንድ ፓርቲ ወደ አንድ ግለሰብ የማሻገር ህልም እንዳለው ለእኔ ግልጽ ነበር። ለዚያ ነው የተቃወምኩት።

በወቅቱ ግን ሰዉ የሚያየው ነገር የለውጥ ስሜቱ ወያኔ [ህወሓት] ብቻ ትጥፋ እንጂ ማንም ይምጣ የሚለው ስሜት በጣም ጠንካራ ስለነበር እኔ ሰዉን ማሳመን አልቻልኩም። መጀመርያ ኦህዴዶችን፣ ቀጥሎ ሕዝቡን ማሳመን አልቻልኩም። በዚያ ምክንያት አቆምኩ እንጂ ለእኔ በጣም ግልጽ ነበር

ከዚያ በኋላ የመጀመርያው አንድ ዓመት ሲደረግ የነበረውን ሳየው ነበር። ተወያይተን ይህንን ሽግግር እንምራ የሚለው ሲመጣ እኔ አሻግራችኋለሁ ማለት፤ የጋራ ፍኖተ ካርታ ይምጣ ሲባል አያስፈልገንም የሚል ምላሽ ተሰማ።በጎ በጎው በሚታይበት ወቅት ራሱ በውስጥ በውስጡ ወደ ዲሞክራሲ የሚያሸጋግረው ኃዲድ ተስቶ ነበር። መጨረሻ ላይ የለየለት ወደ ምርጫ ሲገባ፣ ተፎካካሪ ይሆናሉ

ተብለው የሚታሰቡ ኃይሎችን ወደ መምታት ሲገባ ነው ሰዉ የነቃው እንጂ ከጅምሩም ዐቢይ ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲ የማሻገር ፍላጎት ፈጽሞ ኖሮት አያውቅም።

ቢቢሲ፦በአገሪቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጦርነቶች እንደቀጠሉ ናቸው፤ በትግራይ ክልልም ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም። . . . አሁንም ወደ ዲሞክራሲ የመመለስ፣ አገሪቱን ወደ መስመር የመመለስ እድል አለ ብለህ ታምናለህ?

ጃዋር፦ ቢጠብም እድል አለ። ግን አሁን እነ ዐቢይ በያዙት አመለካከት እና ትምክህተኛነት ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስ የሚችሉ አይመስለኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያን አይረዷትም። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበትን (Multi ethnic) የሆነን አገር፣ አሁን ባለው ዓለም ተጨባጭ ሁኔታ እና ኢትዮጵያ ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አይረዱም። ለመረዳትም ፍላጎት የላቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የብልጽግና ደሴት የሚባል ተፈጥሯል። ዐቢይ እና እርሱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ብቻ የሚንሸራሸሩበት፣ ሌላውን ሕዝብ ፈጽሞ ያገለለ፣ የሌላውን ሕዝብ አኗኗር የማይረዳ።

በቅርቡ [አዲስ አበባ] ሄጄ የሆነ ነገር ፌስቡክ ላይ ጽፌ ነበር። ‘ሕዘቡ ጠውልጓል እነርሱ ደንዝዘዋል’ የሚል፤ እውነቴን ነበር። ሕዝቡን ተዘዋውሬ አየሁት። ከተማ ውስጥ ቀንም ማታም እየዞርኩ ሕዝቡን አየው ነበር። ከዚያ ደግሞ ቱባ ቱባ ሚኒስትሮችን አገኘኋቸው።

ስለ ኢኮኖሚ ስታወራ፣ ‘ኢኮኖሚውማ እንደዚህ አድጎ አያውቅም’ ይሉሀል. . . በየቤቱ ማር እና ወተት በቧንቧ የሚፈስ ነው የሚያስመስሉት።

ስለ ጦርነት ስታወራ አማራ ክልል. . እነሱ እኮ ተከፋፍለዋል፤ እየጠፉ ነው። ኦሮሚያ ክልል ምንም ችግር የለም። ትግራይ የራሳቸው ጉዳይ. . . ያምኑታል ደግሞ [ጠቅላይ ሚኒስትሩን]። . . . የራሳቸውን ውሸት ያምኑታል። እነርሱ በያዙት አመለካከት ወደ መስመር መመለስ አንችልም። ነገር ግን ዝም ብለን እንመለከታለን? ዝም ብለን ደግሞ አንመለከትም። አገራችን ነው ሕዝባችን ነው። የለፋንበት ነው፤ እድሜያችንን ያጠፋንበት ነው። We are not going let them take us down [ብልጽግናዎች ይዘውን እንዲጠፉ አንፈቅድላቸውም]። ራሳቸው ብቻ ሳይሆን አገር ይዘው ሊወድቁ ነው። እኛ ኢትዮጵያን ሕዝቦቿ ወደ መንገድ መመለስ እንችላለን? አዎ መመለስ እንችላለን። እነሱን ግን ይመልሱናል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ ባለፉት ስድስት ዓመታት አገሪቷን ከከተተበት መከራ ወደባሰበት ነው ይዘውን እየሄዱ ያሉት።

ጃዋር፦በእስር ቤት ወቅት እኔ ብቻ እስር ቤት መሆኔ አይደለም ትልቁ ነገር። ባለፈውም እንዳልኩት እኔ ትቻት የታሰርኩት ኢትዮጵያ እና እኔ ከእስር ቤት ወጥቼ ያገኘኋት ኢትዮጵያ የተለያዩ ነበሩ።

እስር ቤት ከመግባቴ በፊት የችግር ዳመናው፣ የጦርነት ዳመናው የተሰበሰበ ነበር። ከእስር ቤት ስወጣ እሳት በየቦታው ተቀጣጥሎ ነበር። ስለዚህ እንደ አንድ ተሰሚነት እንዳለው እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ምን ባደርግ ነው አገር እና ሕዝብ ማዳን የምችለው? ብዬ አሰብኩ። ወጥቼ ወደ አክቲቭዝም እና ወደ ትችት ብመለስ በእሳቱ ላይ ሌላ ቤንዚን መጨመር ሆኖ ታየኝ። ስለዚህ ያንን ተወት ላድርገው እና ያለኝን ተሰሚነት፣ ያለኝን ትስስር፣ መስተጋብር በማማከር፣ በመገሰጽ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡም እንዲረባረብ፣ መስራት ላይ አተኮርኩ። ከእስር ከወጣሁም በኋላ ሕዝቡንም ወደ ዲያስፖራው ሄጄ ስለ ሠላም ስናገር ከፍተኛ ተቃውሞ ይደርስብኝ ነበር። ያንን ማድረግ የምችለው እኔ ብቻ ነበርኩ።

ከትግሉ ጋር ተያይዞ ያለኝ የፖለቲካ ካፒታል ነበር።ያንን የፖለቲካ ካፒታል ውጪ አገር ሄጄ በመመንዘር፣ በወቅቱ ሕዝቡ በተለያየ ወገን ያለውን ጦር በመደገፍ በጣም ተከፋፍሎ ስለነበር፣የጦርነት ገበያ እንዲጠብ እና የሠላም ገበያ እንዲሰፋ፣ መንግሥትም ሆነ ጫካ ያሉት አማፂያን ጫና ተደርጎባቸው ወደ ሠላም ይመጣሉ በሚል ነበር ያንን ስሰራ የነበረው።

መጀመርያ ለሕዝቡ ስለ ሠላም በመናገር፣ ከዚያ ደግሞ ዲፕሎማቶቸን በመቀጠል ደግሞ የአገሪቱን ባለሥልጣናት የአማፂ አመራሮችን በማግኘት የተቻለኝን ሳደርግ ነበር። ብዙ ሞከርኩ። ግን እያየሁት የመጣሁት ነገር፣ ጊዜ ለመግዣ እንጂ አገሪቱን ወደ አጠቃላይ ሠላም፣ ሥር ነቀል ሠላማዊ ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነቱም ፍላጎትም እንደሌለ፣ እንዳውም ነገሮች ረገብ ሲሉ ወደ ነበረበት ሲመለሱ ስላየሁ ይህ ነገር በዚሁ ከቀጠለ እየተባባሰ ነው የሚሄደው፤ ዝም ማለቱ እና መምከሩ፣ መለማመጡ፣ መለመኑ ብዙም አላስኬደም። . . . እኔ በዚያ መቀጠሉ ዋጋ ስለሌለው ነው።

ጃዋር፦ ወደ ቀደመው መመለስ አይቻልም። ወደፊት ብቻ ነው መሄድ የሚቻለው።(ሳቅ)

ቢቢሲ፡- ይህንን ያነሳሁት ቀጣዩ ምርጫ ብዙም ሩቅ አይደለም በሚል ነው። አንተ ደግሞ በኦፌኮ ውስጥ አባል እና አመራር ነህ፤ በቀጣይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ሚና ይኖርሃል ለማለት ነው?

ጃዋር- ቀልጣፋ ሚና ይኖረኛል። እኔ አሁን መናገር እና መጻፍ የጀመርኩት እነዚህ ልጆች[የብልጽግና ሰዎች] በጣም አደገኛ ነገር ውስጥ ነው የገቡት። Total ignorance and arrogance (እልም ያለ ድንቁርና እና እብሪተኝነት)።

ቢቢሲ- የብልጽግና ሰዎች ማለትህ ነው?

ጃዋር-የብልጽግና ሰዎች ዐቢይ እና በአካባቢው ያሉ ሰዎች Total ignorance and arrogance[እልም ያለ ድንቁርና እና እብሪተኝነት] ውስጥ ናቸው። ይህ ነው የማይባል ጥጋብ ውስጥ ገብተዋል።

ጥጋብ ደግሞ ጆሯቸውንም አእምሯቸውን ደፍኖታል። ይሄ ለእነሱም ለአገርም አደጋ አለው። ስለዚህ እኔ የምፈልገው እንድንነጋገር ነው። ልንነጋገር ይገባል።

በተለይ አሁን ምን እያደረጉ መሰለህ እኛን እና ትግራይን ሲመቱ የአማራውን የፖለቲካ ‘ካምፕ’ ነው የተጠቀሙት። አሁን ደግሞ አማራ ጋር ሲጋጩ ኦሮሞ ውስጥ ተወሽቀው፤ ኦሮሞን ፊት ለፊት እየያዙ በኦሮሞነት ስም አማራን ለመምታት ይፈልጋሉ።

ይኼ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ አደጋ ነው የሚዳርጋት። የኦሮሞ ሕዝብ ይህንን አይፈልግም። የኦሮሞ ሕዝብ ትናንት ከአማራው ውስጥ በወጡ ገዢ መደቦች ሲጨቆን ታግሏል። ከትግራይም በወጡ ሲጨቆን ታግሏል። የታገለው ግን አንድ አምባገነን ሥልጣን ላይ ወጥቶ በእርሱ ስም ትግራይን እንዲመታ፣ አማራን አንዲመታ አይደለም።

እኛ ከአማራ ጋር፣ ከተጋሩ ጋር፣ ከሶማሌ ጋር ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በውይይት፣ በክርክር በመፍታት ለእኛም ለሁሉም የምትሆነንን ኢትዮጵያን መመስረት ነው።

ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ኢትዮጵያን መመስረት ነው። እንጂ አሁን እንደ እኔ አይነት ተሰሚነት ያለን ሰዎች ዝም ካልን የኦሮሞን ስሜት በመኮርኮር ከአማራ ጋር በሚያደርጉት ጦርነት ለመጠቀም የሚያደርጉትን ማንዣበብ ስላየሁ ይኼ መክሸፍ አለበት በሚል ነው የሄድኩበት [እየሰራሁ ያለሁት]።

ጃዋር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ምርጫ ቅንጦት ነው። አንድ ተረት አለ። ጭንቅላት ካለ ነው ጥምጣም የምትጠመጥምበት። ጭንቅላቱ ከሌለ ግን ምኑ ላይ ትጠመጥመዋለህ? ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው መንግሥት የሚቆጣጠረው ቦታ ሲኖር ነው።

ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ መንግሥት ባህር ዳር እና የተወሰኑ ጥቂት ቦታዎች እንጂ ክልሉ በቁጥጥሩ ስር አይደለም። በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ከተወሰኑ ዋና ዋና ከተሞች ውጪ ሌላው የአማፂያን መፈንጫ ነው። ኢትዮጵያ ካላት 547 የፓርላማ የምርጫ መቀመጫዎች ውስጥስንቱ ቦታ ውስጥ ነው ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው? ኢትዮጵያ ካላት 547 የፓርላማ ወንበሮች ውስጥ ቢያንስ በ2/3ኛው በትንሹ ምርጫ ካልተካሄደ ያ ምርጫ ተቀባይነት አይኖረውም።

ስለዚህ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ስለ ምርጫ ማውራት ዋጋ የለውም። መጀመርያ አገራችንን ወደ ሠላም መመለስ መቻል አለብን። አንጻራዊ ሰላም ከመጣ ስለ ምርጫ ማውራት እንችላለን። አንጻራዊ ሠላም መጥቶ የምርጫ እድል ከመጣ የመጀመርያው ረድፍ ላይ እሰለፋለሁ።

ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ስለ ምርጫ የምናወራው እኛ ነበርን። አገር ነበረን። ስርዓት ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ስለ ምርጫ ማውራት ሕዝብን ማዘናጋት ስለሚሆን ነው። ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ላይ ጫና ተደርጎ፣ ምክንያቱም የሰላም ድርድር እና ንግግር እንዳይመጣ ዋነኛ ጋሬጣ የሆነው መንግሥት ነው።

ጃዋር፡- መንግሥት የችርቻሮ ሠላም ነው የሚፈልገው። ይህንን አማፂ በዚህ ጋር በገንዘብ በሌላ ነገር ደልሎ ለማምጣት። ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ወይም ትግራይ ክልል የዛሬ አምስት ስድስት ዓመት እኮ አማፂ አልነበረም። ምንድን ነው ወደ አመጽ የመራው? ጎንደር ውስጥ ወለጋ ውስጥ አማፂ ሳይመጣ እኮ ልብ የሸፈተው አዲስ አበባ፣ ፊንፊኔ ላይ ነው።

የፖለቲካ አለመስማማት፣ የነበረውን የፖለቲካ ልዩነት በጠረጴዛ ዙርያ ለመፍታት ፍላጎት ከማጣት እና የፖለቲካ ምህዳሩን በመዝጋት የግለሰብ አምባገነናዊ ስርዓት ለመመስረት ዐቢይ በመወሰኑ ነው። በአገሪቱ እምብርት ዋና ከተማ ላይ ሊፈታ የሚገባው ልዩነት ነው ወደ ጫካ ለመግባት ምክንያት የሆነው።

እኛ እያልን ያለነው አጠቃላይ ሠላም፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ‘ሴትልመንት’ [ፖለቲካዊ እልባት]፤ ወደ ጦርነት ያስገቡን የፖለቲካ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙርያ በድርድር እና በንግግር መፈታት አለባቸው ነው። እነርሱ ይህንን አይፈልጉም። በዚህ ጋር ቄሱን ሼኩን ልከው፣ በዚህ ጋ ነጋዴውን ገንዘብ አስይዘው ልከው ሊያመጡ ነው የሚፈልጉት። ይመጣሉ የተወሰኑ ወታደሮች። እኛም እኮ ሞክረናል ከአባ ገዳዎች ጋር ሆነን ከግማሽ በላይ የሆኑ የኦነግ ጦርን ይዘን መጥተናል። የፖለቲካ ምህዳሩ ጠብቦ በመቀጠሉ እና ዋና የግጭቱ መንስዔ የሆነውን ጉዳይ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከዚያ ወዲህ እጥፍ ተስፋፍተው ዛሬ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ መንግሥት ካለው ጦር በላይ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ነው ያለው።

ስለዚህ እኛ ሰላም እያልን ያለነው የምላስ ሰላም ሳይሆን ስር ነቀል የፖለቲካ ልዩነቶችን ከየጫካው ከጠመንጃ አፈ ሙዝ ወደ ጠረጴዛ ላይ የሚያመጣ ሰላም ነው እያልን ያለነው።

ጃዋር – ተድበስብሰዋል። መድበስበስ ብቻ ሳይሆን ከእነዚያ ጥያቄዎች የባሱ ሆነዋል። ያኔ እኮ የሚነሱ ጥያቄዎች የእኩልነት፣ የቋንቋ፣ የከተማ ምናምን ዛሬ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያንን የሚጠይቅ የለም። ዛሬ ጥያቄው የሕልውና ሆነ። ሕዝብ በቀዬው አርሶ መግባት አልቻለም። በሺዎች ሚሊሻዎችን እያሰለጠነ፣ ሚሊሻው ደሞዝ የለውም፣ ሰዉን ይዘርፋል። ጫካ ያለውም ሰውን ይዘርፋል።መንግሥትን ወክሎ ስርዓት ለማስከበር የሚላከው ሠዉን ይገላል። ሠዉን ይዘርፋል። ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዘብ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ አንተ የምትላቸውን እኛ ስናነሳቸው የነበሩትን ጥያቄዎች አይደለም የሚያነሳው።

መሰረታዊ ወጥቶ የመግባት እና ያለመግባት ጥያቄ ነው እያነሳ ያለው። ብዙዎቹ ወጣቶች በኦሮሚያ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ድሪባ ኩምሳ፣ ጃል መሮ ጋር የገቡት፣ በአማራ እነ እስክንድር ነጋ ጋር ሌሎቹ ጋር የተቀላቀሉት የፖለቲካ ጥያቄያቸውን ‘አርቲኩሌት’ [ስላንጸባረቁ] ስላደረጉ አይደለም። አንደኛ የፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋት መፈናፈኛ አሳጣቸው። ሁለተኛ ወደ ቀያቸው ሲገቡ የሚደረገው አፈና፣ ግድያ፣ እርግጫ፣ መኖርያ ከለከላቸው። የግል ሕይወታቸውንም ለመታደግ፣ የፖለቲካ ጥያቄያቸውንም ለማራመድ የግድ መግባት ነበረባቸው። . . . ስለዚህ የፖለቲካ ጥያቄው ተድበስብሶ የሕልውና ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄውን ሸፈነው፤ አፈነው ማለት ነው።

ጃዋር፦የአገር መበተን ነው። ምክንያቱም ያኔ እኛ ስንታገል አገረ መንግሥት ነበር። እኛ አገረ መንግሥቱን እየጎነተልንም እየቦቀስንም አፈናው እንዲቀንስ፣ ለዜጎች እና የቡድኖችን መብት እንዲሰጥ ነበር የምንጠይቀው። ግንዱ ስለነበር ነው። አሁን ግንዱ ምስጥ በልቶት እያለቀ ነው።

የአገር መፍረስ አደጋው በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ ነው። . . . ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚሉ ሰዎች በየዕለቱ እያፈረሷት ነው። አገር ከፈረሰ፣ ምናልባትም እድሜዬ እየሄደ ነው መሰለኝ እና የአገር መፍረስ ያሳስበኛል።

መጽሐፌም ውስጥ ብዙም ጊዜ ደጋግሜ እንደምናገረው፣ ከ2007 እስከ 2012 ድረስ በነበረው ጊዜ የቄሮን እንቅስቃሴ ስትራቴጂ ሳወጣ የስርዓት ፍንቀላ ‘ሪጂም ቼንጅ’ ነበር ሳስብ የነበረው።

ይኼ እያለ ከእኔ ጋር ሲማሩ የነበሩ፣ እኔም ሳስተምራቸው የነበሩ ልጆች ‘የአረብ ስፕሪንግ’ [የአረብ አመጽን] አስነሱ። ከዚያ በፊት የነበረው አስተሳሰብ ምንድን ነው በሕዝባዊ ዓመጽ አምባገነናዊ ስርዓትን ትገረስሳለህ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትገነባለህ ነበር። ሦስተኛ አማራጭ እንደበር አላየንም። የስቴት ኮላፕስ [የአገር መፍረስ]። የሊቢያ መፍረስ፣ የየመን መፍረስ፣ የሶሪያ መፍረስን ሳይ መለስ ብዬ ኢህአዴግን ካፈረስን የአገር መፍረስ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጫና ፈጥረን ከኢህአዴግ ውስጥ ለዘብተኛ የሆነ ለውጥ የሚፈልጉ ኃይሎች ወደ ሥልጣን ይምጡ ወደሚል ሄድን። ከዚያ ጊዜ የተጠናወተኝ ፍራቻ ለ’ስቴት’ የመሳሳት ጉዳይ አሁን ደግሞ እያየሁት መጣሁ። እና አሁን እንቅልፍ የሚነሳኝ አንዴ ስቴት ከፈረሰ፣ አምባገነናዊ የሆነን መንግሥት ማስተካከል ትችላለህ፤ ኢኮኖሚው የተበላሸን ስቴት ሰውዬውን [መሪውን] አንስተህ ልታስተካክል ትችላለህ። አገር ከፈረሰ መልሶ መገንባት በጣም ከባድ ነው። . . . እንደ ኢትዮጵያ ውስብሰብ የሆነ እና ብዙ የውጪ ኃይሎች ፍላጎት ያሉበት አገር አንዴ ከተበተነ. . . አገር መፍረስ ስል ግን ሰው መጠንቀቅ አለበት። ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሚያ አይቀርም፣ አማራ አይቀርም፣ ትግራይ አይቀርም። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ከፈረሰ ብትንትን ነው። . . . ከጣርያ ላይ እንደለቀቀከው ጀበና ነው የሚሆነው።

 ጃዋር- የአገራዊ ውይይት ጉዳይ ገና ለውጡ ሲመጣ ሦስት ጉዳዮችን ነው ‘ፕሮፖዝ [ያቀረብነው] ያደረግነው። አንደኛው አገራዊ ውይይት ነው። የብሔራዊ እርቅ እና የማንነት እና የድንበር ጉዳዮችን ከዚያ የሚወጡ ብለን ነው ያስቀመጥነው። Part of our transition plan [እንደ መሸጋገሪያ ዕቅድ]። የብሔራዊ ውይይቱን ትተው የብሔራዊ እርቅ እና የማንነት እና የድንበር ኮሚሽንን ለጊዜው አቋቁመው ለሦስት ዓመት ከቆዩ በኋላ ፈረሰ። ‘ናሽናል ዲያሎግ’ [ብሔራዊ ምክክር] በአንድ አገር ውስጥ በሁለት ምክንያት ነው የሚደረገው። አንዱ ጦርነትን ለማስቀረት። የፖለቲካ ልዩነቶች በጣም ተጋግለው ሲወጠሩ ያንን ውጥረት ለማርገብ እና ወደ ጦርነት እንዳያመሩ ለማድረግ።

ቅድመ ጦርነት የመከላከል መንገድ ሊሆን ይችላል። አንዱ ደግሞ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ጦርነት ሲቆም ወደ ጦርነት ያስገቡ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወደ ሌላ ጦርነት እንዳያመሩ በጦርነት ጊዜ የተፈጸሙ በደሎች እና ስህተቶች እንዲታከሙ፣ ቁስል እንዲሽር የሚደረግበት ድህረ ጦርነት ‘ናሽናል ዲያሎግ’ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ሲጀመር በጦርነት መካከል ነው የተመሰረተው፥ ትግራይ ጦርነት እየተካሄደ ነበር። ኦሮሚያም ውስጥ እየተካሄደ ነበር። እስር ቤት እያለሁም ጠይቄያለሁ። ከወጣሁም በኋላ ለ’ናሽናል ዲያሎግ’ የተመረጡት ሰዎች መጥተው ጠየቁኝ። የእኔ ምክረ ሀሳብ ምን ነበር? ሀሳቡ በጣም ጥሩ ነው።

ከስድስት ዓመት በፊት፣ 2018 ላይ ማድረግ ነበረብን። እሺ ከመቅረት መዘግየት ይሻላል።ብሔራዊ ዲያሎግ (ምክክር) ሊሰራ የሚችለው መነሻው ወሳኝ ነው። ሊወያዩ የሚወስኑ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች አወያዮቹን መረጣ ላይ፣ የመወያያ ሕጉ ላይ ግብዓታቸውን ሊካተት እና ሊስማሙበት ይገባል። ስለዚህ አትሩጡበት አትቸኩሉበት።

አንድ እርሱ ነው። ሁለተኛ ቅድም እንዳልኩት ‘ናሽናል ዲያሎግ’ [ብሔራዊ ምክክር] ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ጦርነት ካለቀ በኋላ ሲሆን ነው። ስለዚህ ጦርነት እንዲቆም፣ የትግራይ ጦርነት እንዲቆም፣ የኦሮሚያ ጦርነት አንዲቆም፣ እነዚያ የሚዋጉ ሰዎች ወደ መድረክ እንዲመጡ ስሩበት እኛም አንደግፋለን የሚል ነው። ያ ሳይሰራ ቀጠሉበት። የአማራ ክልል ጦርነት ተጨመረበት ማለት ነው። ዛሬ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ናሽናል ዲያሎግ’ ሊካሄድ አይችልም፤ ዐቢይ መስታወት እያየ እንደማውራት ማለት ነው።

ጃዋር፡-ያለቀለት ጉዳይ ኦኮ ነው። ፕሮፌሰር መረራ እንደሚለው ‘ዴድ ኦን አራይቫል’። ከጅምሩ የተበላሸ ነገር ስለሆነ አሁን ባለው ሁኔታ በዋናነት ምንድን ነው የሚሆነው ስርዓቱ ፕሬዝዳንታዊ ይሁን በማለት ዐቢይን ፕሬዝዳንት ከማድረግ ያለፈ ውጤት ሊኖረው አይችልም።

ጃዋር፡- ቅድም እንዳልኩህ ነው። ‘Mataa jirutti sabbata marani’ ባለ ጭንቅላት ላይ ጥምጣም የሚጠመጠመው። ለእኔ ትልቁ ነገር እስቲ አገር ይኑረን።

አገር የለንም የምንልበት ደረጃ ላይ እየገባን ነው። . . . አገር ይመለስና የጠቅላይ ሚኒስትርነትም የገበሬነት ችግር የለውም። ችግር የፈጠረው አንዱ ምንድን ነው? አገር ለመምራት የሚያስፈልገው እውቀት፣ ብስለት፣ ብልሀት፣ ምንድን ነው ብሎ ራስን ሳያዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን፣ ሚኒስቴር ለመሆን ብቻ የሚደረግ ያለ ዕቅድ የአገሪቱን ውስብስብነት፣ የዓለምን ውስብሰብነት ሳይረዱ የሚደረግ ነገር አደጋ አለው። ስለዚህ ለእኔ ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁን? የሚለው ሁለተኛ ደረጃ ነው።

እኔ አሁን አምፁ እያልኩ አይደልም ያለሁት። መነጋገር አለብን ነው የምለው። አገር ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብታለች። ኢኮኖሚያችን ዳሽቋል። ሕዝቡ ኢትዮጵያ ድሮም ደሀ ነች አሁን ባለው ደረጃ ግን ሕዝቡ ተቸግሮ አያውቅም። . . . ይህ ደግሞ ምን ውጤት ነው። አንዱ የጦርነት ውጤት ነው፥ ከጦርነት የተረፈውን ገንዘብ ቅንጡ ሪዞርቶች እና ቤተመንግሥት ላይ ውሏል ።

የፈጣሪ ያለህ. . . ኢትዮጵያ ለምንድን ነው አዲስ ቤተ መንግሥት የሚያስፈልጋት? የኢትዮጵያ ሕዘብ ችግር ሪዞርት ነው?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር በቂ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ማዳበርያ አለማግኘት ነው። የኢትዮጵያ ሕዘብ ችግር ገበሬው ተረጋግቶ ማረስ የሚችልበት ሠላም አለመኖር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር የመንገድ ትራንስፖርት በሰፊው አለመኖር ነው። . . . . ስለዚህ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ምንድን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የቅድሚያ መዛባት አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያንን ማስተካከል የግድ ነው።

ጃዋር፦በጣም ነው ያጣችው። ኢትዮጵያ ሴኩሪቲን [ደህንነትን] ለሌሎች አገሮች የምታዳርስ አገር ነበረች። ያን የምታደርገው ጠንካራ ጦር ስለነበራት ብቻ አይደለም። በአገር ውስጥ መረጋጋት ስለነበር ነው። የአገር ውስጥ ጦርነቱ የአገሪቱን አቅም በጣም አዳክሞታል። ለጎረቤቶቿ ጸጥታን ሳይሆን ብጥብጥን የምታከፋፍል ሆናለች። ያ አንሶ ከጎረቤቶቻችን ጋር አላስፈላጊ ግብግብ ውስጥ ገብተናል። አገራዊ ራዕይ፣ አገራዊ ፕሮጀክት የለም። . . . ከኤርትራ ጋር፣ ከሶማሊያ ጋር ልዩ ግንኙነት ነው ያለን። ከሁለቱ አገራት ጋር ያለን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከሌሎች ጋር የሚነጻጸር አይደለም። በጣም የተወሳሰበ ነው። ለሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ መሀከል ነች ። የእኛ ሚና መሆን የነበረበት ከእነዚህ አገራት ጋር የነበረንን ታሪካዊ ቁርሾ በመጠገን በማዳን የበለጠ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ግንኙነት ማጠናከር ነው።

. . . ከሶማሊያ ጋር ሴንሲቲቭ [ሰሱ] የሆኑ ታሪካዊ ሁኔታዎች አሉ። በመጀመርያው የዐቢይ አምስት ዓመት የነበረን ግንኙነት ጥሩ ነበር። ከሶማሊያ ጋር የነበረንን ግንኙነት አረጋግተነው ነበር። ግን ከማረጋጋት ባለፈ ሊኖረን የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና የሴኩሪቲ [የደህንነት] ግንኙነት ስርዓት አላስያዝነውም። አልተነጋገርንበትም፤ አልተጻፈም። . . . ስለዚህ አገራዊ ከመሆን ወረደ እና ግለሰባዊ ሆነ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል። አዎ! ለንግድ ብቻ ሳይሆን የባሕር ኃይልም ያስፈልገናል። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኖር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም አስፈላጊ ነው። ሰፊ ሕዝብ ያላት፣ ትልቅ ወታደር ያላት፣ ሰፊ የቆዳ ስፋት እና ሰፊ ኢኮኖሚ ያላት አገር ናት ኢትዮጵያ። የሕንድ ውቅያኖስም ሆነ የቀይ ባሕር በተለያዩ ከሩቅ በሚመጡ ኃይሎት ተጋላጭ ሆኗል። ብዙ ኃይሎች እየመጡ ነው። ሶማሊያ በራሷ የዚህን አካባቢ ጥቅም ልታስከብር አትችልም። ኤርትራም አትችልም።

ከኢትዮጵያ ጋር ቢተባበሩ ግን፣ ኢትዮጵያ እቀማለሁ በሚለው ፉከራ ሳይሆን፣ ለሶማሊያም፣ ለኤርትራም ለጂቡቲም ሊሆን በምትችለው ቀጠናዊ ትስስር ላይ ማዕከል ያደረገ የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል። . . . ከዚህ ይልቅ ግን ከዚህ በፊት የሰለቸንን ዓይነት በፉከራ መሄዱ አደጋ ውስጥ ከትቶናል። . . . . ድንገት ከሶማሌላንድ ጋር ተስማምተናል ተባለ። ገና ለመስማማት እኮ ነው የተስማማነው። ኢትዮጵያ ወደብ አገኘች ተብሎ ሕዝብን ለማሞኘት። እና ሕዝብ ሴንሴቲቭ [ስስ] ነው። ወደብ ይፈልጋል። ያንን የሕዝቡን ፍላጎት ‘ሚስ ዩዝ’ [ያለ አግባብ ነው የተጠቀሙበት]ነው ያደረጉት። አዋረዱን። ከገቡበት በኋላ እንኳ ተደራድረው ሌላ መንገድ ከማምጣት ይልቅ ወደ ሚታየው ነገር ውስጥ ገባን። በዓለም ላይ ቻይና እና አሜሪካ፣ ምስራቁ እና ምዕራቡ ተስማማብን። ረባሽ አገር አስባሉን። . . . በአካባቢው የችግር መንስዔ ሆነን እየታየን ነው።

በአካባቢው ያሉ አገራት አሁን አዲስ አበባ ካለው መንግሥት ጋር አንዳቸውም ጤነኛ ግንኙነት የላቸውም። . . . እዚህ አካባቢ አንደሚንቀሳቀስ እና ጉዳዩን በንቃት አንደሚከታተል ‘አይ ፊል ፔይን’ [ሕመም ይሰማኛል]። ስለ አገራችን እና ስለ አገራችን አመራር የሚነገረውን ስትሰማው እንደ አንድ ዜጋ ሕመም ይሰማኛል። በአገሬ መኩራት ነው የምፈልገው። በአመራሮቼ ልኮራ ነው የምፈልገው።

ኢትዮጵያ የሚመጥናት አመራር ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያን እመራለሁ ብሎ ስልጣን የያዘ ኃይል ለዚያች አገር እና ሕዝብ የሚመጥን አመራር መስጠት አለበት። ካልቻለ ግን አልቻልኩም ብሎ መልቀቅ መቻል አለበት አንጂ አገርንም ራስንም በዚህ ደረጃ ማዋረድ በጣም የሚያሳዝን ነው።

ቢቢሲ፦ በአሁኑ ወቅት ኑሮህን ኬንያው ውስጥ ነው ያደረግከው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የደህንነት ስጋት አለብህ?

ጃዋር- ለስጋት ብቻ አይደለም። አንደኛ ለስራዬ እዚህ ይሻለኛል። ሁለተኛ ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ወደ እሬቻ ሲሄድ ጠባቂዎቼን አዋክበው በሙሉ አሰሯቸው።

ከዚያ ከብዙ ሰዎች ጋር፣ ከፓርቲ ሰዎችም ጋር ስንወያይ በወቅቱ የነበረኝም አቋም ምንድን ነው፣ ምንም ቢሆን በእኔ ምክንያት አሁን ባለው እሳት ላይ ችግር መፈጠር የለበትም የሚል ነበር።

ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እኔን ተተናኩለው ነገሮችን ማባባስ የሚፈልጉ ስላሉ የሚሻለው ምንድን ነው ብለን ወደ ናይሮቢ መጣሁ። ግን ሁሌ እዚህ አልኖርም። አውሮፓ ነው የምሰራው። አውሮፓ ብዙ ጊዜ እመላለሳለሁ። ግን ናይሮቢ ውብ ስፍራ ነች። አያስቀናም! (ፈገግታ)

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop