አሜሪካ ውስጥ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቀረት ትራምፕ ያሳለፉትን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ? Leave a comment

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕጋዊ ሰነድ ከሌላቸው ቤተሰቦች በአሜሪካ ለሚወለዱ ሰዎች በቀጥታ የሚሰጠውን ዜግነት ለማስቀረት የሚያስችለውን ውሳኔ አሳልፈዋል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በጀመረው በአዲሱ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ቀን ከፈረሟቸው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች መካከል አሜሪካ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የሚያስቀረው አንዱ ነው። ሆኖም ዝርዝሩ ግልጽ አይደለም።

14ኛው የተሻሻለው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ደግሞ በአሜሪካ ምድር የተወለደ ማንኛውም ሰው የአሜሪካ ዜግነትን እንደሚያገኝ ይደነግጋል።

በመሆኑም ትራምፕ ይህንን ለማስቀረት ቃል ቢገቡም ውሳኔያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጋዊ መሰናክሎች እንደሚገጥሟቸው እሙን ነው።

የአሜሪካውያን ሲቪል ነጻነቶች ኅብረት እና ሌሎች ቡድኖች የትራምፕን ትዕዛዝ ተከትሎ በአስተዳደራቸው ላይ ክስ ያቀረቡትም ወዲያውኑ ነው።

በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ምንድን ነው?

14ኛው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ‘በመወለድ የሚገኝ ዜግነት መርኆዎችን ያብራራል።

“በአሜሪካ የተወለደ አሊያም የዜግነት መብት የተሰጠው ማንኛውም ሰው የአሜሪካ እና የሚኖርበት ግዛት ዜጋ ነው” ይላል።

ፖሊሲው ሕገወጥ ስደትን እና ‘የወሊድ ቱሪዝም’ የሚባለውን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች በአሜሪካ ምድር ለመውለድ ሲሉ ድንበር አቋርጠው እንዲገቡ ያበረታታል በሚል በኢምግሬሽን ተሟጋቾች ይነቀፋል።

ይህ የዜግነት መብት እንዴት ተጀመረ?

14ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የፀደቀው የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ 1868 ነበር።

ቀደም ብሎ በ1865 የተደረገው 13ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የባሪያ ንግድን ያስወገደ ሲሆን፣ 14ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ደግሞ ነጻ የወጡ እና በአሜሪካ የተወለዱ ‘የቀድሞ ባሪያዎችን’ የዜግነት ጥያቄ መልሷል።

ሕጉ ከመጽደቁ በፊት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በ1857 የድሬድ ስኮት [አፍሪካ አሜሪካዊ] እና ሳንፎርድ [የሕንዳውያን ጎሳ ወኪል የነበረ] ግለሰቦች መዝገብን ጨምሮ በቀረቡ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አፍሪካ አሜሪካውያን የአሜሪካ ዜጋ ሊሆኑ እንደማይችሉ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

ከዚያም በ1898 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተመለከተው የ’ዎንግ ኪም አርክ እና አሜሪካ’ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት በመወለድ የሚገኝ ዜግነት የስደተኞች ልጆች ላይም ተግባራዊ እንዲሆን ፈቅዷል።

ዎንግ ከቻይናውያን ስደተኞች በአሜሪካ የተወለደ የ24 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ከቻይና ጉብኝቱ በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሶ እንዳይገባ ተከልክሎ ነበር።

ዎንግ በአሜሪካ በመወለዱ የወላጆቹ የስደት ሁኔታ የተሻሻለው14ኛው ሕገ መንግሥት በእርሱ ላይ ተግባራዊ ከመሆን እንደማያግደው ስኬታማ በሆነ መልኩ ተከራክሮ ነበር።

በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የኢምግሬሽን ታሪክ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ኢሪካ ሊ “የወላጆች ዘር ወይም የስደት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በዩናይትድ ስቴትስ የተወለደ ማንኛውም ሰው ዜግነታቸው የሚሰጣቸውን ሁሉንም መብቶች የማግኘት መብት እንዳላቸው የዎንግ እና አሜሪካ ጉዳይ አረጋግጧል” ሲሉ ጽፈዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እንደገና መርምሮት አያውቅም።

ትራምፕ ይህንን ሊቀለብሱት ይችላሉ?

በርካታ የሕግ ምሁራን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ማስቆም እንደማይችሉ ይስማማሉ።

የሕገ መንግሥት ባለሙያ እና በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ሳይክሪሽና ፕራካሽ “ትራምፕ በርካታ ሰዎችን የሚያበሳጭ ድርጊት ነው እየፈፀሙ ያሉት። ሆኖም ይህ ሊወሰን የሚችለው በፍርድ ቤት ነው” ብለዋል።

“በመሆኑም ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው ፍቃድ ብቻ ብድግ ብለው የሚወስኑት ጉዳይ አይደለም።”

ፕሮፌሰር ፕራካሽ እንዳሉት ፕሬዚደንቱ እንደ የአሜሪካ ኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ሥራ አስፈፃሚ ወኪሎች ያሉ የፌደራል ተቋማት ሠራተኞች ዜግነትን በጠባብ መልኩ እንዲተረጉሙት ማዘዝ ቢችሉም ዜግነቱን ከሚከለከል ሰው የሕግ ፈተና ሊያስነሳባቸው ይችላል።

ይህም በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ የተራዘመ ክርክር ሊያመራ ይችላል።

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከተደረገ ግን በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ሊሻር ይችላል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሃሳቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔቱ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅበታል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሦስተኛ በሚሆኑት የአሜሪካ ግዛቶች ሊጸድቅ ይገባል።

ውሳኔው ምን ያህል ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ያደርሳል?

እንደ ፒው ጥናት ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2016 በአሜሪካ ከሚኖሩና ዜግነት ከሌላቸው ስደተኛ ወላጆች 250 ሺህ ሕፃናት ተወልደዋል።

ይህ ቁጥር በ2007 ከነበረው በ36 በመቶ ቀንሷል።

መቀመጫው ዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው በአሜሪካ ፖለቲካ እና ፖሊሲ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያካሂደው የጥናት ተቋም – ፒው በ2022 ባወጣው መረጃም ሰነድ ከሌላቸው ስደተኛ ወላጆች የተወለዱ 1.2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዜጎች እንዳሉ ጠቅሷል።

እነዚህ ልጆችም ልጆች ስላሏቸው በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ማስቆም በአገሪቷ ያለውን የሕገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር በ2050 ወደ 4.7 ሚሊዮን እንደሚያደርሰው የስደት ፖሊሲ ተቋም አመልክቷል።

ትራምፕ የኤንቢሲ ፕሮግራም ከሆነው ‘ሚት ዘ ፕረስ’ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ሕገ ወጥ ስደተኛ ልጆች ምንም እንኳን በአሜሪካ ቢወለዱም ከወላጆቻቸው ጋር ወደመጡበት መመለስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ታኅሣሥ ወር ላይ በሰጡት በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ “ቤተሰብን መለያየት አልፈልግም፤ በመሆኑም ቤተሰብን ላለመለያየት ያለው ብቸኛው አማራጭ አንድ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፤ እናም ሁሉንም ወደ መጡበት መላክ አለብን” ብለዋል።

በመወለድ ዜግነት የሚሰጡ አገራት የትኞቹ ናቸው?

ካናዳ እና ሜክሲኮን ጨምሮ ከ30 በላይ የዓለም አገራት ያለምንም ገደብ ‘ራይት ኦፍ ዘ ሶይል’ የሚባለውን በተወለዱበት ቦታ የሚገኝ ዜግነትን ይሰጣሉ።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ያሉ ሌሎች አገራት ደግሞ ወላጆቻቸው ዜጋ አሊያም ቋሚ ኗሪ ለሆኑ ልጆች ዜግነትን ይሰጣሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop