አዲሱ የበረኞች የ8 ሰከንድ ሕግ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል? የትኞቹ ግብ ጠባቂዎችስ ሰዓት ያባክናሉ? Leave a comment

በአዲሱ ሕግ መሠረት ግብ ጠባቂዎች ኳስ በእጃው ይዘው እስኪለቁ ስምንት ሰከንድ ብቻ ይሰጣቸዋል። ይህ ሕግ ከመጪው ክረምት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው በረኞች ሰዓት ለመግደል የሚደረገውን ሙከራ ለመቀነስ በሚል ነው።

ሕጉ በሙከራ ደረጃ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን እና በማልታ ተግባራዊ ሆኖ ስኬታማነቱ ተረጋግጧል። ይህም የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበራት ቦርድ ሕጉ ከ2025/26 መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቋል።

ሕጉ እንዴት ይተገበራል?

ሕጉ ከሰኔ 1 ጀምሮ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ ውድድሮች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።

ክረምት ላይ እንደሚደረግ በሚጠበቀው የክለቦች የዓለም ዋንጫ ላይም ሕጉ ሥራ ላይ ይውላል።

ምን ዓይነት ቅጣት ይኖረዋል?

ግብ ጠባቂዎች በእጃቸው ላይ ከስምንት ሰከንድ በላይ ኳስ ይዘው ከቆዩ ተቃራኒው ቡድን የማዕዘን ምት እንዲሰጠው ይደረጋል።

ዳኞች በምን መልኩ ይተገብሩታል?

በረኞች ኳስ ይዘው 5 ሰከንድ ሲሞላቸው ኳሷን እንዲለቁ በዳኞች ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። በመቀጠልም እጃቸውን ከፍ በማድርግ እንዲታይ አድርገው እያሳዩ ይቆጥራሉ።

ይህ ሕግ ከዚህ ቀደም አልነበረምን?

ይህ ሕግ ቀደም ሲልም የነበረ ሲሆን፣ የሚተገበረው ግን አልፎ አልፎ ብቻ ነበር።

አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕግ መሠረት ግብ ጠባቂዎች ከስድስት ሰከንድ በላይ ኳስ በእጃቸው ይዘው ከቆዩ ለተቃራኒው ቡድን ሁለተኛ ቅጣት ምት እንዲሰጥ ያዛል።

በሙከራ ወቅት ምን ውጤት ተገኘ?

በሙከራ ወቅት ሕጉ በጥብቅ እንዲተገበር መደረጉን ያስታወቀው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ቦርድ፤ በመቶዎች በሚቆጠሩ ጨዋታዎች ላይ ላይ ተተግብሮ አራት ጊዜ ብቻ ግብ ጠባቂዎች ከስምንት ሰከንድ በላይ ኳስ በእጃቸው በመያዛቸው እንዲቀጡ ተደርጓል ብሏል።

“ጥሩ ሕግ ማለት ሁሉም ለመተግበር የሚፈልገው እና ያለው ችግር በሙሉ የሚቀረፍበት ነው” ሲሉ የቦርዱ ቴክኒካል ዳይሬክተር እና የቀድሞው የፕሪሚየር ሊግ ዳኛ ዴቪድ ኤላሪ ለዘ ታይምስ ተናግረዋል።

“ጨዋታው እንዲፈጥን ካደረገ አዎንታዊ ውጤት ነው ማለት ነው” ብለዋል።

ከአዲሱ ሕግ ምን ይጠበቃል?

የክለቦች የዓለም ዋንጫ ላይ ማንቸስተር ሲቲ እና ቼልሲ ተሳታፊ ይሆናሉ። የሁለቱ ክለቦች ግብ ጠባቂ የሆኑት ኤደርሰን፣ ስቴፈን ኦርቴጋ፣ ሮበርት ሳንቼዝ ወይም ፊሊፕ የርገንስን ሕጉን እንዴት ተግባራዊ ያደርጉታል የሚለው በጉጉት ይጠበቃል።

በቀጣዩ የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ በርካታ ማዕዘን ምቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የቆመ ኳስ ከአሠልጣኞች ከፍተኛ ትኩረት የሚያገኝበት ጊዜም ይሆናል።

አዲስ ሕግ ሲወጣ መጀመሪያ ላይ የሚጎዱ መኖራቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ተጋጣሚ ቡድን ጨዋታ በፍጥነት እንዳያስጀምር የሚያደርጉ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ እንደሚሰጣቸው በሚገልጸው አዲስ ሕግ ምክንያት በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ መጀመሪያ ላይ ዴክላን ራይስ እና ሊዮናርድ ትሮሳርድ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መበረራቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች በረኞች ኳስ ሲይዙ በምጸት መቁጠር ይጀምራሉ።

ተጫዋቾችም በጉዳዩ ዙሪያ ጣልቃ መግባታቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። አንድ ቡድን ግብ ለማስቆጠር በሚጥርበት ወቅት የተቃራኒ ቡድን ግብ ጠባቂ ኳስ በእጁ ሲይዝ ዳኛው መቁጠር እንዲጀምር ከተጫዋቾች ግፊት ይደረግበታል። ተጨዋቾቹ በራሳቸውም መቁጠር ሊጀምሩ ይችላሉ።

የትኞቹ ግብ ጠባቂዎች ሰዓት ያባክናሉ?

በእግር ኳሱ ዓለም ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ሰዓት ለመግደል በሚል ኳስ ይዘው ስለሚቆዩበት የጊዜ መጠን መረጃ የለም። አልፎ አልፎ ኳስ የሚመለከቱ ሰዎች ጭምር ግብ ጠባቂዎች ኳስ ይዘው በጣም በዘገየ መልኩ ወደ መሬት ሲወድቁ ይመለከታሉ።

ቀድሞው ዳኛ ኤላሪ መስከረም 2023 ማንቸስተር ዩናይትድ በብራይትን 3 ለ 1 የተሸነፈበትን ጨዋታ በምሳሌነት ያነሳሉ። ጄሰን ስቲል የብራይትን ግብን በመጠበቅ ላይ ነበር።

በጨዋታው ስቲል በአማካይ ኳሷን በእጁ ላይ ያቆየው ለ14.8 ሰከንዶች ሲሆን፣ የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ግን በአማካይ ለ4.8 ሰከንዶች ብቻ ኳስ እጁ ላይ አቆይቷል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop