ተማሪዎች ከውጭ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ጋር የተያያዘ ክፍያ መፈጸም ይፈልጋሉ። ውጭ ዘመድ ከሌላቸው እንዴት ይከፍላሉ?
ባሕር ማዶ ጉዞ ሲታሰብ የሆቴል አደራ (Hotel Reservation) ክፍያ ያስፈልጋል። ክፍያው ያለ ካርድ እንዴት ይፈጸም?
ዶላርን በካርድ መጫን -አዲሱ ስልት
ብዙ ሰዎች ለውጭ ጉዞ ዶላር ሲፈልጉ ከንግድ ባንክ ይልቅ ወደ ብሔራዊ ቴአተር የሚያቀኑት ወደው አይደለም። የሚሹትን ከባንክ ስለማያገኙ ነው።
በጥቁር ገበያ ለዚያውም በእጥፍ ተመን የዶላር ግዥ ከፈጸሙ በኋላም ደግሞ ሌላ ራስ ምታት አለ። ገንዘቡን ይዞ ከአገር መውጣት ያሳስራል።
የገዛ ብርን ከስክሶ የገዙትን ዶላር ይዞ ከአገር መውጣት፣ ቅርስ ሰርቆ ከአገር ለመሸሽ የመሞከር ያህል ከባድ ጥፋት እየሆነ ነው።
“የውጭ ምንዛሬው ምን ያህል በስስት እንደሚሰጥ የምትረዳው ከተሰጠ በኋላ ፓስፖርት ላይ ማኅተም መመታቱን ስትመለከት ነው” ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ በግል ባንክ ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ መኰንን።
ይህ ዓመታትን ያስቆጠረ ፈተና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰነ መልክ እየያዘ የመጣ ይመስላል። ”ካርዳዊ መልክ”
ቢያንስ ውጭ አገር ጉዞ ላለባቸውና በበይነ መረብ ግብይት መፈጸም ለሚሹ፣ ባንኮች አዲስ አማራጭ ማቅረብ ጀምረዋል።
ይህም ተጓዥ ደንበኞችን በጥሬ ገንዘብ (ካሽ) ሳይሆን በካርድ የማስተናገድ ስልት ነው።
“እኛም እፎይ ብለናል፤ ደንበኞቻችንም ከሞላ ጎደል ደስተኞች ናቸው” ይላሉ አቶ ካሳዬ እሸቱ። አቶ ካሳዬ የዳሽን ባንክ የዲጂታል ቢዝነስ ባንኪንግ መምሪያ ዳይሬክተር ናቸው።
ዳሽን ባንክ ከወራት በፊት ነው ይህን አዲስ አሠራር ያስተዋወቀው። ሌሎች ባንኮችም በራሳቸው መንገድ እየሄዱበት ነው።
ነገሩ አዲስም ነው፤ አዲስም አይደለም። በአንድ ዓረፍተ ነገር ሲጠቃለል ‘ዶላርን በካርድ’ የመስጠት አማራጭ ነው።
አንድ ደንበኛ ወደ ውጭ ጉዞ እንዳለው የሚያረጋግጡ መረጃዎችን ሲያቀርብ ባንኩ መጀመርያ መረጃዎቹን ይመረምራል። የደንበኝነት ዘመኑንና የሒሳብ ታሪኩን ግምት ውስጥ በማስገባት የዶላር ጥያቄውን በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ይሞክራል።
ቢቢሲ እንደተረዳው ዳሽን ባንክ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ያስተዋወቀው ይህ የዓለም አቀፍ የበይነ መረብ መገበያያ የዶላር ካርድ ሁለት መልክ አለው።
አንዱ የላስቲክ ካርድ ነው። ሌላው ደግሞ ምናባዊ (Virtual card) ነው።
ሁለቱም ግን ‘ፕሪፔይድ’ ወይም የቅድመ ክፍያ ካርዶች ናቸው። ሁለቱም በውጭ ምንዛሬ ለሚፈጸም የበይነ መረብ ዓለም አቀፍ ክፍያዎች የሚያገለግሉ ናቸው።
በተለይ ምናባዊውን ካርድ በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ዳሽን የመጀመርያው ነኝ ይላል።
ዶላር ያለው ሰው አይደለም በዚህ የሚስተናገደው። አገልግሎቱን ልዩ የሚያደርገውም ይኸው ነው።
ደንበኞች በኢትዮጵያ ብር የቁጠባ ሒሳብ ይከፍታሉ። የጉዞ መረጃ ሲያቀርቡ ብሩ ዶላር ሆኖ ካርድ ላይ ተጭኖ ይሰጣቸዋል።
“ልዩነቱ ዶላር በእጅ ሳይሆን በእነዚህ ካርዶች ጭነን ነው የምንሰጣቸው” ይላሉ አቶ ካሳዬ።
የሁለቱን ካርዶች መጠነኛ ልዩነት ቆየት ብለን እንመለከታለን።
ለጊዜው ከዚህ አሠራር በፊት የነበሩ መንገዶችን በአጭሩ እንመልከት።
“ዶላር የሚያገኙት በዶላር የሚከፈላቸው ብቻ ነበሩ”
አቶ መልካሙ ታደሰ በአንድ የግል ባንክ የዲጂታል ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ናቸው። ለቢቢሲ የሚሰጡት ማብራሪያ የሚሠሩበትን ባንክ አይወክልም።
አቶ መልካሙ ”በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ካርዶች ሥራ ላይ ማዋል የቅርብ ታሪክ ነው” ይላሉ።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የግል ባንኮች ኢንተርናሽናል ካርድ ማተም አይችሉም ነበር።
“ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ማሻሻያ የግል ባንኮች ይህ ተፈቅዶላቸዋል።”
ይህ ማሻሻያ የተደረገው በ2018 ዓ/ም ነበር።
መጀመርያ ለንግድ ባንክ ብቻ ውስን በሆነ መንገድ ይሞከር ተባለ። ልምዱ ታየ። እዳውና ምንዳው፣ ተስፋውና ፈተናው ተገመገመ። ከሁለት ዓመት በኋላ ለሌሎች ባንኮች ተፈቀደ።
”ከዚያ በፊት ግን በዶላር የሚሠራ ካርድ በኢትዮጵያ አልነበረም። መመሪያውም ይከለክል ነበር።”
ከንግድ ባንክ በኋላ ሌሎች የግል ባንኮች ወደ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሬ ካርድ የገቡት በ2020 ዓ/ም ነው።
አሁን ባለው አሠራር ማንኛውም ባንክ በዚህ ዶላርን ዲጂታላይዜሽን በማድረጉ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሕጉ ያበረታታል።
አቶ መልካሙ እንደሚሉት አሁንም ባለው አሠራር ቢሆን ካርዱ በሌሎች አገራት እንዳለው ዓይነት ”መልከ ብዙና ዘርፈ ብዙ” አይደለም።
ከዚያ ይልቅ ‘የጉዞ ካርድ’ ነው ማለት ይቀላል ሲሉ ልዩነቱን ለማስረዳት ይሞክራሉ።
‘ለምሳሌ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ያለ ሰው ካርዱን አገር ውስጥም ሌላ አገርም ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲጓዝ ይጠቀምበታል። (ሽንኩርት ሲገዛም- የአየር ትኬት ሲገዛም)። እኛ አገር ግን አንድ ደንበኛ ውጭ አገር ሄዶ እንዳይቸገር ለማድረግ ብቻ ነው በዋናነት አገልግሎቱ የቀረበው።”
ካርዱን ለማግኘት ደንበኛው ይጓዛል ወይ? ትኬት አለው ወይ? ቪዛስ ተመቶለታል? ተብሎ የሚጠየቀውም ለዚሁ ነው።
ስለዚህ ካርዱ ራሱ ‘ትራቭል ካርድ’ ቢባል ይቀላል።
ውጭ አገር የማይሄድ ሰው ካርዱን ማግኘት ይችላል?
በኢትዮጵያ የዶላር ሒሳብ እንዲኖራቸው የተፈቀደላቸው ለዚህ የተቀመጠውን ጥብቅ መስፈርት የሚያሟሉት ብቻ ናቸው።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ሆነው የውጭ ድርጅት ውስጥ እየሠሩ በዶላር የሚከፈላቸው፤ ለምሳሌ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ወ.ዘ.ተ.።
‘’አንድ ላኪ (Exporter) ‘ሪቴንሽን አካውንት’ ሊኖረው ይችላል። ደንበኛው ባንኩ ከፈቀደለት በዶላር ሒሳብ ያስቀመጠውን ዶላር በካርድ ተቀይሮ ሊሰጠውና ሊገለገልበት ይችላል።”
ይህ ግን ከሚሊዮን ደንበኞች እጅግ ጥቂቶች የሚያገኙት ዕድል ነው።
በውጭ ምንዛሬ የሚከፈላቸው ደግሞ ‘ዴቢት ካርድ’ ላይ ገንዘባቸው ተጭኖላቸው ውጭ ሲሄዱ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የነዚህ ደንበኞችም ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
የተቀረው የባንክ ደንበኛ ግን ዶላር ቢሻ መንገዱ ሁሉ ዝግ ነው።
አሁን ባለው አሠራር ኢንተርናሽናል ካርዱ ከጉዞ ጋር ለተያያዘ አገልግሎት የሚውል ነው።
ይህ ማለት ግን ከጉዞ ጋ ባልተያያዘ ካርዱን መጠቀም አይቻልም ማለት ነው?
ለምሳሌ አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በበይነ መረብ ግዢ ለመፈጸም ቢፈልግ ይከለከላል?
አቶ መልካሙ እንደሚሉት አንድ ሰው የውጭ ምንዛሬው በካርዱ ከተጫነለት በኋላ የትም ሆኖ ሊጠቀምበት የሚከለክለው ነገር የለም።
ነገር ግን አንዳንድ ባንኮች አገልግሎቱን ሊገድቡት ይችላሉ ሲሉ ለቢቢሲ ያስረዳሉ።
ለምሳሌ አንዳንድ ባንኮች ለደንበኛ በካርድ ጭነው የሰጡትን ዶላር ኤቲኤም እና ‘ፖስ ማሽን’ ላይ ብቻ እንዲጠቀም ሊያደርጉ ይችላሉ።
አንዳንዶቹ ደግሞ ለማንኛውም ትራንዛክሽን እንዲጠቀም ሊፈቅዱ ይችላሉ። ይህ እንደ ባንኮቹ አሠራር የሚወሰን ይሆናል።
አገር ቤት የበረራ ትኬት ቅርንጫፍ ቢሮ የሌላቸው አየር መንገዶች አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በጭራሽ የሚዳሰስ ቢሮም የላቸውም። ትኬት የሚሸጡት በበይነ መረብ ነው። ከጥሬ ገንዘብ ክፍያ ጋር ፍቺ ከፈጸሙ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ያለ ዜጋ እንዴት ይክፈል?
የተመሰከረለት የሒሳብ አዋቂ ለመሆን የትምህርትና የፈተና ክፍያ በበይነ መረብ ነው የሚካሄደው። የባንክ ሠራተኞች ሳይቀሩ በዚህ ይቸገራሉ።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚያንገላታት ኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች ከአገር ሲወጡ ራስ ምታት የሚሆንባቸው የዶላር ጉዳይ ነው።
በተለምዶ ክቡ ባንክ የሚባለው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በ2ኛው ወለል የዶላር ጠያቂዎችን ሰልፍ በየዕለቱ ማየት ብርቅ አይደለም። ለዓመታት ሰልፉ እየረዘመ እንጂ እያጠረ አልሄደም።
ለውጭ አገር አፋጣኝ ሕክምና 30ሺ ዶላር የጠየቀ ታማሚ፣ ለዚያውም በሐኪሞች ቦርድ የተፈረመበትን ደብዳቤ አቅርቦ፣ ከጠየቀው ገንዘብ አንድ እጅን እንኳ አያገኝም።
ባንኮች የዶላር ጥያቄ የሚያቀርቡላቸው ደንበኞችን ዓይን ይሸሻሉ። ጨክነው ከሰጡም ቆንጥረው ነው።
ታዲያ ዜጎች እነዚህን በይነ መረባዊ ክፍያዎች (International Online Payments) እንዴት ነው የሚያልፏቸው?
ይህ ጽሑፍ በበይነ መረብ ግብይትና ከዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዳስሳል።
ባንኮች የውጭ ምንዛሬን በካርድ ጭነው መስጠት ለምን ይመርጣሉ?
‘ዶላር ካርዱ ላይ ጭኖ መስጠት ሕይወት ያቀላል?’ ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የባንክ ባለሙዎች። እንዴት?
አንደኛ የዶላር ኖት (የወረቀቱ ገንዘብ) እንደልብ የለም። ሁለተኛ በዚህ የካሽ እጥረት የተነሳ ባንኮች ደንበኞችን ለማስተናገድ ተቸግረው ነበር።
“አንድ ደንበኛህ ዶላር እፈልጋለሁ እያለህ የለኝም ስትለው ጥሩ ስሜት አይፈጥርም’ ይላሉ አቶ ካሳዬ። ካርዶቹ ግን አሁን አሁን ችግሩን በከፊል እየፈቱት ይመስላል።
አቶ ካሳዬ ይህ በካርድ የውጭ ምንዛሬ የመስጠት አሠራር የባንኮችን ራስ ምታት የቀነሰ ሆኗል ይላሉ። ‘ለደንበኞቻችንም ለኛም የአእምሮ ሰላም ያመጣ’ ሲሉም ያሞካሹታል። ምን ማለታቸው ነው?
ቀደም ሲል ደንበኞች የውጭ ምንዛሬ ሲጠይቁ ባንኮች የተጠየቀውን መጠን ለመስጠት ይቸገሩ ነበር። አሁንም ችግሩ ተቃለለ እንጂ አልተቀረፈም።
ይህ በሁለት ምክንያት ነው። አንዱና ቀጥተኛው ምክንያት ዶላር የላቸውም። ሁለተኛው ደግሞ ቢኖራቸውም በስስት ነው መጠቀም ያለባቸው። ቢኖራቸውም ካሽ ዶላር የላቸውም።
ሌላው ምክንያት በዚያም በዚህም ብለው ያገኟትን የውጭ ምንዛሬ ጠቅልለው የራሳቸው ማድረግ አይችሉም። ለብሔራዊ ባንክ በመቶኛ መገበር አለባቸው።
ስለዚህ ደንበኞች የዶላር ጥያቄ ሲያነሱ ሊስተናገዱ የሚችሉበት ቀዳዳ ጠባብ ሆኖ ቆይቷል።
በካርድ መስጠት ግን መጠነኛ እፎይታን ይሰጣል ይላሉ አቶ ካሳዬ። ይህም ዋናው ችግር በአገሪቱ የዶላር ኖት በካሽ እጥረት ስላለ ነው።
አቶ ካሳዬ ከደንበኛውም አንጻርም ቢሆን በካርድ ዶላር ይዞ መሄድ ምቾት የሚሰጥ እንደሆነ ይገልጻሉ። ‘’ለምሳሌ ዶላር ቢጠፋ አትተካውም፤ ካርዱ ቢጠፋ ይተካል። በዚያ ላይ ውጭ አገር ብዙ አገልግሎት ሰጪዎች ካሽ ዶላር አይቀበሉም። ይላሉ።
ባንኮች ለተጓዦች ዶላሩን በካርድ መጫን ከቻሉ ያንኑ ዶላር በካሽ መስጠት ለምን ይከብዳቸዋል? የሚል የዋህ ጥያቄ እናንሳ። በካርድም ሰጡ፣ በካሽ ያው ዶላሩ ከእጃቸው መውጣቱ አይቀርም በሚል እሳቤ የተነሳ ጥያቄ እንደሆነ ልብ ይሏል።
ለዚህ ምላሽ የሚሰጡን አቶ መልካሙ ናቸው።
አቶ መልካሙ ነገሩን ሲያስረዱ ባንኮች ያላቸውን የዶላር ክምችት ሁለት ገጽታ እንዳለው በማስታወስ ነው።
አንድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ (Forex Reserve) በቢሊዮን ዶላር ሊኖረው ይችላል። ይህን ገንዘብ ግን በካሽ ማግኘት አይችልም።
ይህ ክምችት ለምሳሌ በአሜሪካ ሲቲ ባንክ ነው የሚቀመጠው። ባንኩ ይህን ገንዘብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ቢያከማችም በእጁ ያገኘዋል ማለት ግን አይደለም።
አንድ የኢትዮጵያ ባንክ ይህን ያህል የውጭ ምንዛሬ ክምችት ኖሮት በካሽ ያለው ግን የዚህ አንድ መቶኛው እንኳን ላይሆን ይችላል።
ስለዚህ ለደንበኞች በካሽ የዶላር ኖት መስጠት ለባንኮች ፈተና ይሆንባቸዋል። በመላው አገሪቱም ዶላር በካሽ ስለሌለ።
“ለዚህም ነው ለባንኮች በካርድ ዶላር ጭኖ መስጠት ትልቅ እፎይታ የሚሆነው”
‘ዶላር’ የሚለው ቃል በዚህ ጽሑፍ ‘የውጭ ምንዛሬ’ የሚለውን ሰፊ ሐሳብም የሚወክል እንደሆነ ልብ ይሏል።
ካሽ አገሪቱ ውስጥ የለም። ቱሪስቶችም ቢሆን ካሽ ይዘው አይመጡም። ካርድ ነው ይዘው የሚመጡት። በአጭሩ ዶላሩ አለ-ኖቱ የለም።
አገር ውስጥ ያለው የዶላር ኖት መጠን ባንኩ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ክምቸት የማይወክለውም አንዱ ለዚሁ ነው።
ስለዚህ ከባንክ አንጻር ብዙ ደንበኛ ለመድረስ “ዶላርን በካርድ እየጫኑ” መስጠት በብዙ እጥፍ ተመራጭ መንገድ ሆኗል።
ዓለም የወረቀት ገንዘብን እየተወ ነው። የወረቀት ገንዘብ በጥቂት ዘመን እንደ አሞሌ ጨው ታሪክ ሊሆን እየተንደረደረ ነው።
“አሁን እኮ ተመርቀህ ቆንጆ CV ለመገንባት እንኳ ኦንላይን ክፈል ትባላለህ” ይላሉ አቶ ካሳዬ ነገሩ ሁሉ ወደ በይነ መረብ እየዘመነ ስለመምጣቱ ሲያስረዱ።
“ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ሲስተም ጋር ለመቀላቀል የዓለም አቀፍ ካርድ ማስጀመራችን ትልቅ እምርታ ነው ይላሉ” ባለሙያው አቶ መልካሙ፤ አገሪቱ በፋይናንስ ሲስተም ተነጥላ እንደቆየች በማስታወስ። ገና ብዙ ርቀት እንደሚቀረንም በማስገንዘብ።