“ኤችአይቪ በደሜ ውስጥ በመኖሩ ያለ ፈቃዴ እንድመክን ተደረግኩ” Leave a comment

1 ታህሳስ 2023

በኬንያ ኤችአይቪ በደማቸው አለ በሚል ሳያውቁ እንዲመክኑ የተደረጉ አራት ሴቶች ካሳ እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤት ወስኗል።ግለሰቦቹ ለዘጠኝ ዓመታት ካደረጉት የፍርድ ቤት ትግል በኋላ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ የሚሆን እያንዳንዳቸው 20 ሺህ ዶላር እንዲሰጣቸው ተበይኗላቸዋል።የኬንያ ፍርድ ቤት ብያኔውን ባሳለፈበት ወቅት ስማቸውን አልገለጸም። አራቱ ሴቶች ታሪካቸውን ለቢቢሲ ያጋሩ ሲሆን፣ ቢቢሲም የግለሰቦቹን ማንነት ለመጠበቅ ሲል ስማቸውን ቀይሯል።ፔንዳ በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኘው ፑምዋኒ በተሰኘው የመንግሥት ሆስፒታል መንታ ልጆቿን ከተገላገለች በኋላ የተከተለውን ነገር ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።ከመንትዮቹ መወለድ በኋላባይላተራል ቲዩባል ሊጌሽንየተባለው፣ የሴት እንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦን በመቀንጠብ፣ በከፊል በመቁረጥ፣ በመቋጠር ወይም በማስወገድ በዘላቂነት የሚያመክነውን ቀዶ ሕክምና ሳታውቀው እንድታደርግ ሆኗል።

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?  የመንታ ልጆቿ አባት ሕጻናቱ ሳይወለዱ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ነበር ሕይወቱ ያለፈው። ፔንዳም በጸነሰችበት ወቅት ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ እንዳለ ታውቅም ስለነበረ ጉዳይዋን ለሕክምና ባለሙያዎች አስረድታ ትከታተል ነበር። በወቅቱ ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ነፍሰጡር እናቶች በቀዶ ሕክምና (ሴክሽን እንዲወልዱ) እና በምጥ እንዳይወልዱም ይበረታታ የነበረበት ጊዜ ነው። ከወለዱም በኋላ ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ በጡት ወተት አማከይነት እንዳይተላለፍ ለመከላከል በሚል እንዳያጠቡም ይመከሩ ነበር።በአሁኑ ወቅት በኬንያ አብዛኛው የወሊድ አገልግሎት ነጻ ቢሆንም፣ ፔንዳ በምትወልድበት ወቅት ክፍያው እንደሷ ላሉ አቅመ ደካሞች ፈታኝ ነበር። ፔንዳ ከወለደች በኋላ መንታ ልጇቿን እንዳታጠባ እና የዱቄት ወተት ብቻ እንድትሰጣቸው ተነገራት።ለእሷም ሆነ ለሕጻናቱ ነጻ ምግብ የማግኘት መብት እንዳላት ቢነገራትም፣ ይህ የሚሆነው ግን የቤተሰብ ዕቅድ እንደምትጠቀም ማስረጃ ማምጣት የምትችል ከሆነ ብቻ ነው ተባለች።መገለል እና መድልዎን እየታገለች የነበረችው እናት፣ ይህ ሲነገራት በጣም ደነገጠች።ማስረጃውንም ለማምጣት በፑምዋኒ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ስታናግር በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ የሚሠራው ማሪ ስቶፕስ የቤተሰብ ዕቅድ መርሃ ግብር እንዳለው ነገሯት።

ፔንዳም ወደተነገራት የማሪ ስቶፕስ ክሊኒክ አቀናች። በክሊኒኩም ፔንዳ አንድ ቅጽ እንድትፈርም ተሰጣት። በቅጹ ላይ የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዋ እንዲቆረጥ ወይም እንዲወገድ ፍቃድ ሰጥቻለሁ የሚል ነበር። ማንበብ የማትችለው ፔንዳም ምን እንደሆነ ማንም ሳይነግራት ቅጹን ፈረመች። ሌላኛዋ እናት ኒማም ከፔንዳ ጋር ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳላት ትናገራለች። በኬንያ ትልቁ በሆነው የሕዝብ ሆስፒታል፣ ፑምዋኒ አራተኛ ልጇን ልትወልድ ሄደች። አራተኛ ልጇን በጸነሰችበት ወቅት ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ አንዳለ ታውቅ ነበር። በማህጸኗ ውስጥ ያለው ልጇም ይያዝ ይሆን የሚለው ያሳስባትም ነበር። በሆስፒታሉ ውስጥ ከወለደች በኋላም የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዋን የማስቆረጥ ቀዶ ሕክምና ካላደረች የምግብ ዘይት እና የበቆሎ ዱቄት ለመቀበል ብቁ እንዳልሆነች በሆስፒታሉ የሥነ ምግብ ባለሙያ እንደተነገራት ገልጻለች።ይህም ብቻ ሳይሆን ቀዶ ሕክምናውን ካላደረገች በሆስፒታሉ የወለደችበትን የአገልግሎት ሂሳብንም መክፈል እንዳለባት በኚሁ ባለሙያ እንደተነገራት ገልጻለች።በምትወልድበት ዕለትም አንድ ተረኛ ነርስ ሦስት ልጆች ስላሏት የቤተሰብ ዕቅድ አገለግሎት መጠቀም እንዳለባት መከሯት።በምክር ብቻ አላለፏትም ነርሷ የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዋ እንዲቀረጥ ወይም እንዲቆረጥ እና በቀዶ ሕክምና ለመውለድ የሚያስችላትን ቅጽ እንድትፈርም ሰጧት።ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር። የመሰለኝ ተራ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ነበርብላለች።አክላምሂደቱን በደንብ ቢያብራሩልኝ ኖሮ በዚያ ወረቀት ላይ ፊርማዬን አላስቀምጥም ነበርስትል ታስረዳለች።ሦስተኛዋ ሰለባ ፉራሃ ደግሞ ከሁለቱ ለየት ያለ ነው። ሦስተኛ ልጇን በፑምዋኒ ሆስፒታል ለመውለድ ባቀናችበት ወቅት ስለ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ያነሳላት ሰው አልነበረም።በወሊድ ወቅት ወደ ልጇ የኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይተላለፍ በሚል በቀዶ ሕክምና እንድትወልድ በተጠየቀችው መሠረት እሱን ተስማማች። ልጇን ወልዳ ከነበረችበት ሰመመን ስትነቃም ከዚህ በፊት ገጥሟት የማያውቅ የከበደ ህመም ተሰማት። አንዲት ነርስ የማምከን ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላት ነገረችኝ ትላለች።ለባለቤቴ የሆነውን ነገር ለመናገር በጣም ፈራሁ። እናም በውስጤ ደብቄ ለመያዝ ወስኜ ነበርስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።በኋላ ግን ባለቤቷ ሲያውቅ በጣም መጠጣት ጀመረሰካራም ሆነ፣ በኋላም መኪና ገጭቶት ሞተ። እነዚህ ተቋማት ሕይወቴን አበላሽተውታልትላለች።

አራተኛዋ ተጎጂ ፋራጃ ሦስተኛ ልጇን ከተገላገለች ከሁለት ወራት በኋላ የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዋ እንዲቋጠር እንድትስማማ ከፍተኛ ጫና እንደደረሰባት ለቢቢሲ ተናግራለች።ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ በመኖሩ ልጇን የጡት ወተት እንዳታጠባው በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል። ለሕጻኑ የሚሆን የዱቄት ወተት ለማግኘትም የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ አገልግሎት እንደምትጠቀም ማስረጃ ማምጣት ነበረባት።ተስፋ ቆርጬ ነበር። ባለቤቴም ጥሎኝ ሄደ። የቤት ኪራይም መክፈል ነበረብኝ። ምን ማድረግ እችል ነበር?” ስትል ትጠይቃለች።ፋራጃ ለኬንያ ከፍተኛ ፍረድ ቤት እንደተናገረችው ወደ አንድ ክሊኒክ ሄዳ እንድትፈርም አንድ ቅጽ ተሰጣት። ፋራጃም ማንበብ አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን፣ የምትፈርመውን ወረቅት ይዘትም ያስረዳት ሰው አልነበረም። አማራጭ የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ አገልግሎት ሆነ መቼም መውለድ እንደማትችል አልተነገራትም።የጤና ባለሙያዎች እነዚህ ሴቶች ለምን እንደሚፈርሙም ሆነ የሚደረግላቸውን ቀዶ ሕክምና በግልጽ ባለማስረዳታቸው በፍርድ ቤት ሊያሸንፉ ችለዋል።የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሴቶቹ መረጃ ሳይሰጣቸው እንዲሁም ያለፈቃዳቸው በዚህ ቀዶ ሕክምና ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ የሴቶቹን መሠረታዊ መብቶች እንዲሁም ቤተሰብ የመመሥረት መብትን የጣሰ ተግባር ነው ብሎታል።አራቱ ሴቶች የሚከፈላቸው ካሳም ከዓለም አቀፉ ማሪ ስቶፕስ ተቋም፣ ፑምዋኒ ሆስፒታል እንዲሁም የቤተሰብ ዕቅድ ምክር አገልግሎት ሰጥቷል የተባለው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ተውጣጥቶ ይሆናል።አራቱን ሴቶች ወክሎ ሲሟገት የነበረው ኬሊን ኬንያ የተሰኘው የኤችአይቪ መብት ተሟጋች ቡድን ዋና ዳይሬክተር አለን ማሌቼ፣ ብያኔው በአፍሪካ ውስጥ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው እና እንዲመክኑ ጫና ለተደረገባቸው ሴቶችም መሠረታዊ ነው ይላሉ። በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳሉ እና ወደ ፍርድ ቤትም እንዳመሩ ገልጸዋል።በኬንያ የማሪ ስቶፕስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ ሁኔታው ለሁሉም አካላት ረጅም ጊዜ የወሰደ እና ፈታኝ ነበር ብለዋል።አስር ዓመት የሚጠጋ ጊዜ የወሰደውን የፍርድ ሂደት ውሳኔ እንቀበላለን። በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፍቃድ ማግኘት ምንጊዜም ከምናከናውናቸው ተግባራት አካል ነውብለዋል።

የዓለም አቀፍ የሥነ ተዋልዶ መብቶች ማኅበረሰብ አባል እንደመሆናችን መጠን ኤችአይቪ በደማቸው ያሉ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን መገለሎችን እንገነዘባለን። ጥብቅ ሥልጠናዎችን እና ክትትል ማድረጋችንን እንቀጥላለን። በምንሰጣቸው እንክብካቤዎች መቼም ቢሆን ቸልተኝነት አናሳይምብለዋል።የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ ፍራንስ በበኩሉ በኬንያ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን በሕክምና ሴቶችን የማምከን ሂደት ውስጥ አልተሳተፍኩም ብሏል። የቤተብ ምጣኔ ዕቅድ አገልግሎት ፈላጊዎች የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦን ማስቆረጥ እንደ አማራጭ አድርገው ከወሰዱ የማማከር፣ የማሳወቅ እና ወደተመረጡት ተቋማት የማስተላለፍ ሥራ ነው የምሠራው ይላል።በሴቶቹ ላይ ለደረሰው ነገር በተወሰነ መልኩ እንደ የሕክምና ተቋም ኃላፊነቱን እንቀበላለን። በመረጃ ላይ የተደገፈ ፍቃድ የማግኘት ሥራችንን እንቀጥላለንሲሉም በኬንያ የኤምኤስኤፍ የፕሮጀክት አስተባባሪ / ሃጂር ኢሊያስ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የፑምዋኒ ሆስፒታል በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ ከቢቢሲ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።በኬንያ ውስጥ ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ምን ያህል ሴቶች ያለፈቃዳቸው እንዲመክኑ ስለመደረጋቸው ትክክለኛ መረጃ የለም። ነገር ግን በአፍሪካ በሥርዓተ ጾታ እና ሚዲያ ላይ የሚሠራውሮብድ ኦፍ ቾይዝበአውሮፓውያኑ 2012 በሠራው ጥናት መሠረት 40 ሴቶች በአስገዳጅ መልኩ መክነዋል። ከእነዚህም መካከል አምስቱ ብቻ ናቸው የከሰሱት። የኬንያ ፍርድ ቤት ካሳ የወሰነላቸው አራቱ ሴቶች፣ ውሳኔው ካሳ ብቻ ሳይሆን የፍትህ ጥያቄያችንን መልሶልናል ይላሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop