ዜሌንስኪ በፕሬዚዳንት ትራምፕ “ጠንካራ አመራር” ስር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ….. Leave a comment

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በአገራቸው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ጠንካራ አመራር” ስር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።

ዜሌንስኪ ይህንን ያሉት ባለፈው ሳምንት ወደ ዋይት ሃውስ አቅንተው ከትራምፕ እና ከምክትላቸው ጋር ያደረጉት ውይይት ወደ ተግሳጽ እና ዘለፋ መቀየሩን ተከትሎ ነው።

በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የተላለፈውን ይህንን ሙግት ተከትሎ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ያቋረጠች ሲሆን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ይህንን “የሚያሳዝን” ሲሉ ዘለግ ባለ የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፋቸው አስፍረዋል።

ትራምፕ የዩክሬኑን መሪ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመምጣት ዝግጁ አይደለም ብለው ቢወነጅሏቸውም ዜለንስኪ “ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጦርነቱን መቋጨት የሚቻልባቸውን የመጀመሪያ ደረጃዎችንም ዘርዝረዋል።

“ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲቆም ለመስራት ዝግጁ ነን። በመጀመሪያ እስረኞን መፍታት፣ ተኩስ አቁም፣ የሚሳኤል እገዳ፣ ረጅም ርቀት ያላቸው ድሮኖችን ማስቆም፣ የኃይል ማመንጫዎች እና ሌሎች የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መቆም፣ በባህር ላይ እና በአየር ላይ ተኩስን ማስቆም” ነው ሲሉ ዘርዝረዋል።

“ከዚያ ወደ ሚቀጥሉት ደረጃዎች መሸጋገር እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር በመስራት ጠንካራ የሆነ የመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረስ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ዜሌንስኪ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር የተደረገው ውይይትን አስመልክቶ “በሚፈለገው መንገድ አልሄደም። እንዲህ መሆኑ ያሳዝናል” በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋለ።

አክለውም “ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው። ለወደፊቱ የሚደረጉ ትብብሮች እና ግንኙነቶች ገንቢ እንዲሆኑ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በዋሽንግተኑ ውይይት አሜሪካ እና ዩከሬን የማዕድን ውል ለመፈራረም ባይችሉም ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ አሁንም ቢሆን አገራቸውን ይህንን ስምምነት ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ ተናግረዋል።

በመሪዎቹ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲ ቀውስ ተከትሎ በትናንትናው ዕለት አሜሪካ ከዚህ ቀደም ታደርገው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ “ማቆሟን እንዲሁም እንደምትገመግመው” አስታውቃለች።

የዩክሬኑ መሪ በዚሁ የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፋቸው አሜሪካ እስካሁን ለአገራቸው ላደረገችው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናቸውን ችረዋል።

“አሜሪካ የዪክሬን ሉዓላዊነት እና ነጻነት እንዲጠበቅ ያደረገችውን ድጋፍ ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጠው ነው” ሲሉ አስፍረዋል።

በትራምፕ የመጀመሪያ ጊዜ አስተዳደር ወቅት አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠቻትን ጸረ-ታንክ ሚሳኤል በመጥቀስ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለዩክሬን ጃሌሊንስ ሲሰጡ ነገሮች የተቀየሩበትን ሁኔታ እናስታውሳለን። ለዚህም በጣም እናመሰግናለን” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በዋይት ሃውስ በነበረው ኃይለቃል በተሞላበት ውይይት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ አሜሪካ ለዩክሬን ያደረገችው ወታደራዊ ድጋፍ ” የሚገባ ምስጋና አላሳየህም” በሚል ዜሌንስኪን ወቅሰዋቸው ነበር።

“በዚህ ውይይት ላይ አንዴ እንኳን ‘አመሰግናለሁ’ ብለሃል?” ሲል ቫንስ የጠየቃቸው ሲሆን ፤ ትራምፕም ይህንን ባስተጋባ መልኩ “ምስጋና ቢስ” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

ዜሌንስኪ በውይይቱ ላይ ራሳቸውን ለመከላከል የሞከሩ ሲሆን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ለምትሰጡን ድጋፍ በሙሉ አሜሪካውያንን በጣም አመሰግናለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop