የካሊፎርኒያን ሰደድ እሳት እየተዋጉ ያሉት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከሄሊኮፕተር ላይ ቀይ እና ሮዝ ዱቄት ሲነሰንሱ ታይቷል።
በእሳት የጋዩ የሎስ አንጀለስ መንደሮች በሮዝ እና በቀይ ቀለም ተውጠዋል። ቤቶች እና መኪኖች ላይ የሚታየውም ይህ ቀለም ነው።
እሳት እንዳይስፋፋ ወይም መጠኑ እንዲቀንስ የሚያደርግ ኬሚካል ነው።
በሺህ ሊትሮች በሚለካ መጠን ይህ ኬሚካል ከሄሊኮፕተር እየተለቀቀ እንደሆነ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ይህ ኬሚካል ፎስ-ቼክ ይባላል። የሚያቀርበውም ፕሪሜትር የተባለ ድርጅት ነው።
ይህ ኬሚካል በአውሮፓውያኑ ከ1963 ጀምሮ በአሜሪካ እሳት ለማጥፋት ጥቅም ላይ ውሏል።
በካሊፎኒያ የእሳት ተቆጣጣሪ ተቋም ውስጥም ጥቅም ላይ ይውላል።
በ2022 በአሶሺየትድ ፕረስ በወጣ ዘገባ መሠረት በዓለም ቁጥር አንድ እሳት መከላከያ መሣሪያ ነው።
በደቡባዊ ካሊፎርኒያ እየተባባሰ ከሄደው ሰደድ እሳት ጋር በተያያዘም ይሄ ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል።
አምራቹ ድርጅት እንዳለው የእሳት አደጋውን መከላከል ሲቻል ዱቄቱን ማጽዳት ይቻላል።
“ሳይጸዳ ቆይቆ ባለበት ከደረቀ በኋላ ለማጽዳት ከባድ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሞቀ ውሃ አጥቦ ቀለሙን ማስለቀቅ እንደሚቻል ተቋሙ አስታውቋል።
ፎስ-ቼክ እንዴት እንደሚሠራ በግልጽ የተባለ ነገር የለም። ከዚህ ቀደም ግን 80 በመቶ ውሃ፣ 14 በመቶ ለማዳበሪያ የሚውል ጨው እና 6 በመቶ ቀለም መሆኑ ተገልጿል።
ቀለሙ ቀይና ሮዝ የሆነው ለአውሮፕላን አብራሪዎች እና እሳት አደጋ ተከላካዮች በጉልህ እንዲታይ ነው። ከቀናት በኋላ ቀለሙ ይደበዝዛል።
ይህ ኬሚካል የሚረጨው በደን ውስጥ እና በሌሎች ተቀጣጣይ በሆኑ ቆሶች ላይ ሲሆን፣ የሰደድ እሳት መስፋፋትን እንደሚገድብ ይታመናል።
የአሜሪካ የደን ጥበቃ እንዳለው፣ ኬሚካሉ እሳትን የማርገብ ወይም እሳት ኦክስጅን አግኝቶ እንዳይስፋፋ የማገድ ኃይል አለው።
የተቀጣጣይነት ኃይሉንም የሚቀንስ ኬሚካል ነው።
አካባቢ ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጫና አንጻር አወዛጋቢ ሆኖ ነበር።
በ2022 የደን ጥበቃ ተቋም ሠራተኞች ለአካባቢ ጥበቃ ተቋም ክስ አቅርበው ነበር። የፌደራል መንግሥት የኬሚካል እሳት በዕጸዋት ላይ በማፍሰስ የአገሪቱን የንጹህ ውሃ አቅርቦት ሕግ መጻረሩን በክሳቸው አካተዋል።
ይህ ኬሚካል ውጤታማ እንዳልሆነ እና ዓሣ እንደሚገድልም ገልጸው ነበር።
በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ታይቶ አሸናፊ ከሆኑ በኋላ የደን ጥበቃ ተቋም ከአካባቢ ጥበቃ ተቋም ፈቃድ እየጠየቀ ኬሚካሉን መጠቀም ጀምሯል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከማየቱ አስቀድሞ በ2018 በሰደድ እሳት የተጎዳችው የካሊፎርኒያ ከተማ ፓራዳይዝ የቀድሞ ከንቲባ ግሬግ ቦሊን የዳኛውን ውሳኔ አድንቀዋል።
የደን ጥበቃ ተቋም ፎስ-ቼክ የሚባለውን ኬሚካል በፎስ-ቼክ ኤልሲ95 መተካቱን አስታውቋል።
ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው፣ በውሃ አካባቢዎች እና ለመጥፋት በተጋለጠ ብዝሃ ሕይወት አቅራቢያ ኬሚካሉ ጥቅም ላይ አይውልም።