የስኳር በሽታ ምንድነው? እራሳችንን ከበሽታው እንዴት መጠበቅ እንችላለን? Leave a comment

28 ህዳር 2023

የስኳር በሽታ ዕድሜ ልክ አበሮ የሚቆይ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ ከባድ ህመም ነው። ህመሙ የሚከሰተው ሰውነት በደምስር ውስጥ ያለን ስኳር (ግሉኮስ) በሙሉ በተገቢው መጠን ማመንጨት ሲያቅተው ነው። ይህም እንደ የልብ ድካምን፣ ስትሮክን፣ ዐይነ ስውርነትን፣ የኩላሊት ሥራ ማቆምን ሊያስከስት እና ከወገብ በታች ያለን የሰውነት ክፍል ላይ ከባድ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። በመላው ዓለም በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ ባለፉት 40 ዓመታት የታማሚዎች ቁጥር በአራት እጥፍ ጨምሮ አሁን 422 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ይሰቃያሉ። የስኳር ህመም ምንም እንኳ አደገኛ ቢሆንም፣ በሽታው ካለባቸው ሰዎች መካከል ገሚስ የሚሆኑት የጤና እክሉ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም። ነገር ግን የሕይወት ዘይቤን በመቀየር ለዚህ አደገኛ ህመም የመጋለጥ ዕድልን መቀነስ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የስኳር በሽታን እንዴት ይከሰታል?

ስንመገብ ሰውነታችን ካርቦሃድሬቶችን ወደ ስኳር (ግሉኮስ) ይቀይራል። በቆሽት ውስጥ የሚመረተው ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን የሰውነታችን ሕዋሳት ኃይል ለማመንጨት ስኳር እንዲይዙ ትዕዛዝ ይሰጣል።  ኢንሱሊን ሳይመረት ሲቀር ወይም በአግባቡ ሳይሰራ ሲቀር እና ስኳር በደማችን ውስጥ ሲከማች የስኳር በሽታ ይከሰታል።

የስኳር በሽታ ዓይነቶች

የተለያዩ አይነት የስኳር በሽታዎች አሉ። ዓይነት 1  በሚባለው የስኳር በሽታ ቆሽት ኢንሱሊን ማምረት አቁሞ ግሉኮስ በደም ቧንቧ ውስጥ ይከማቻል። ተመራማሪዎች ይህ ለምን እንደሚሆን ትክክለኛውን ምክንያት ባያውቁትም በዘር እንደሚተላለፍ ወይም በቆሽት ውስጥ ኢንሱሊን የሚያመርቱት ሴሎች በኢንፌክሽን ሲጠቁ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።  የስኳር በሽታ ካለባቸው አጠቃላይ ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ዓይነት 1 የሚባለው የስኳር በሽታ አለባቸው።

ዓይነት 2 የሚባለው የስኳር በሽታ ደግሞ ቆሽት በቂ የሆነ ኢንሱሊን አያመርትም ወይም ሆርሞኑ በተገቢው ሁኔታ ሥራውን ሳያከናውን ሲቀር ነው። ኢንሱሊን በቆሽት ውስጥ የሚመረት ሆርሞን ሲሆን፣ ሰውነታችን ስኳር እንዲዋሃድ የሚስችል ነው።  ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ብዙ ጊዜ የሚያጠቃው በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ እና ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎችን ነው። ከልክ በላይ ውፍረት እና ብዙ እንቅስቃሴ በማያደርጉ ወጣቶች ላይ እንዲሁም በደቡብ እስያ በሚገኙ የተወሰኑ ዘሮች ላይ ይከሰታል።  አንዳንድ ነፍሰጡር ሴቶችም ከእርግዝና ጋር የሚመጣ የስኳር ሕመም ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህ የሚሆነው ሰውነት ለእናት እና ለጽንሱ በቂ የሆነው ኢንሱሊን ማምረት ሲያቅተው የሚከሰት ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ 6 አስከ 16 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ከእርግዝና ጋር የሚመጣ የስኳር ሕመም ያጋጥማቸዋል። በሽታው ወደ ዓይነት 2 እንዳይቀየር ነፍሰጡር እናቶች የስኳር መጠናቸውን በአመጋገባቸው ማስተካከል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም ኢንሱሊን መውሰድ ሊኖርባቸው ይችላል። ከዚህ ውጪ ሰዎች ለስኳር በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን በምርመራ ሊያውቁ ይችላሉ። በሰውነት ውስጥ ከፍ ያለ የጉሉኮስ መጠን ወደ ስኳር በሽታ ሊያመራ ይችላል።

የስኳር በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ የማይቋረጥ የውሃ ጥም እና ከተለመደው ውጪ በተደጋጋሚ መሽናት በስፋት የሚስተዋሉ የስኳር በሽታ ምልክቶች ናቸው። የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት የሰውነት ቁስለት፣ ብዥ ያለ ዕይታ እንዲሁም ቀላል የሰውነት መቁሰል እና ቶሎ አለመዳን ሌሎችም በብዙዎች ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶች ናቸው።  እንደ የብሪቲሽ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ከሆነ ዓይነት 1 የስኳር በሽታ ምልክቶች ገና በለጋ ዕድሜ የሚስተዋል ሲሆን ሕመሙም ከባድ ነው። ዓይነት 2 በተባለው የስኳር በሽታ አይነት ከባድ ጉዳት ላይ ሊወድቁ የሚችሉት ዕድሜያቸው 40 እና ከዚያ በላይ የሆኑ፣ በሽታው ያለባቸው እናት፣ አባት፣ ወንድም ወይም እህት ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት ያላቸው፣ ከደቡብ እስያ አገራት አካባቢ የሆኑ ቻይናውያን፣ አፍሮካረቢያን ወይም ጥቁር አፍሪካውያን ዝርያ ያላቸው ላይ ይከሰታል።

የስኳር በሽታን መከላከል ይቻላል?

የስኳር በሽታ መከሰት የሚመሠረተው በዘር ወይም በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ነው። ይሁን እንጂ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በመከተል እና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የስኳር መጠንን መቆጣጠር ይቻላል። ስኳርን በጥራጥሬዎች እና አትክልቶች በመተካት በደም ውስጥ ያለን የስኳር መጠን መቆጣጠር ያስችላል። በፋብሪካ የተቀነባበሩ ጥፋጭ ምግቦችን እና መጠጦችን፤ ነጭ ዳቦ እና ፓስታን ማስወገድ ጠቃሚ ነው። ነጭ የስንዴ ዱቄት፣ ነጭ ዳቦ፣ ነጭ ሩዝ፣ ነጭ ፓስታ፣ ለስላስ መጠጦች፣ እንደ ከረሜላ ያሉ ጣፋጮች ለጤና ጠንቅ ከመሆናቸው በላይ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑት ንጥረ ነገሮቻቸው የወጡላቸው ናቸው። የስኳር በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ጥራጥሬዎችን መመገብ ጠቃሚ ውጤት እናዳላቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ጉልህ ጥቅም አለው። የብሪታኒያ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት በፍጥነት መራመድ እና ደረጃ መውጣትን ሊጨምር የሚችል በሳምንት 2.5 ሰዓት አንቅስቃሴ ማድረግን ይመክራል።

የስኳር በሽታ የሚያስከትላቸው ችግሮች?

በደም ሰር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር የደም ስሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ ይችላል። ደም በሰውነት ውስጥ እንደልብ ካልተንሸራሸረ ደም ወደሚያስፈልገው የሰውነት ክፍል ላይደርስ ይችላል። ይህ ደግሞ ነርቭን ሊጎዳት፣ ዕይታን ሊያሳጣ እና በእግር ላይ ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት ለዐይን ስውርነት፣ ለኩላሊት ሥራ ማቆም፣ ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ለሌሎችም ከባድ ጉዳቶች ዋነኛ ምክንያት የስኳር በሽታ ሊሆን ይችላል። በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ 1.6 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ቀጥተኛ ምክንያቱ የስኳር በሽታ ነበር።

ምን ያህል ሰዎች የስኳር በሽታ አለባቸው?

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በአውሮፓውያኑ 1980 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 108 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ 2014 ላይ አሃዙ ወደ 422 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። እንደ ዓለም አቀፉ የስኳር በሽተኞች ፌዴሬሽን ከሆነ፣ የስኳር በሽታ ካለባቸው 80 በመቶ ያህሉ የሚገኙት የአመጋገብ ሥርዓት በፍጥነት እየተቀየረባቸው በሚገኙት በመካከለኛ እና አስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ነው። እያደጉ ባሉ አገራት ውስጠ ያሉ ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑት በድህነት እና ርካሽ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ስለሚመገቡ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want