የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ “የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል” – የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል…… Leave a comment

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት “ባለፉት ወራት” በአሥመራ ላይ “ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል” በማለት ከሰሱ።

ኢትዮጵያ፤ ቀጣናውን “የከበቡት” ችግሮች “መፍለቂያ እና ማዕከል ናት” ሲሉ የከሰሱት ሚኒስትሩ የማነ፤ አገራቸው በኢትዮጵያ “የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት” እንደሌላት ገልጸዋል።

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ የማነ፤ ይህንን ክስ ያቀረቡት ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11/2017 ዓ.ም. በይፋዊ ኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ነው።

በአስር ነጥቦች የተቀመጠው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ጽሑፍ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ሰኞ ዕለት በአል ጀዚራ የዜና ምንጭ ድረ ገፅ ላይ ላወጡት ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ አስተያየት፤ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እና በቀጣናው አገራት ውስጥ “በግጭት ጠማቂነት” የሚከስስ ነው።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ላለፉት 30 ዓመታት ከአገራቸው ድንበር “በራቁ ብዛት ያላቸው ግጭቶች ውስጥ እንደተሳተፉ” በጽሑፋቸው የገለጹት ዶ/ር ተሾመ፤ ፕሬዝዳንቱ የትግራይ ጦርነትን “እንደ ዕድል” በመጠቀም ወታደሮቻቸው “ወደ ክልሉ ገብተው ውድመት” ማስከተላቸውን አትተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ “መሰናክል” እንደነበር ጠቅሰዋል።

ኢሳያስ ኢትዮጵያ ውስጥ “በትግራያ ክልል ማቆሚያ የሌለው ግጭት እንዲቀጥል” ይፈልጋሉ ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነትን ዋጋ ለማሳጣት በአማራ ክልል ሚሊሺያዎችን አደራጅተዋል” ሲሉም ከስሰዋል።

“[ፕሬዝዳንት ኢሳያስ] በቅርቡ በሰላም ስምምነቱ ደስተኛ ካልሆኑ በህወሓት ውስጥ ካሉ አካላት ጋር የጋራ ጉዳይ በማግኘቱ [ከእነርሱ ጋር] አጋርነት ፈጥሯል” ሲሉ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን ክፍፍል ለራሳቸው ዓላማ “ለመጠቀም እየሞከሩ” መሆኑን አል ጀዚራ ላይ በወጣው የአስተያየት ጽሑፋቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ሙላቱ፤ በኢትዮጵያ የሚከሰት አዲስ ግጭት ጉዳቱ በአፍሪካ ድንበሮች ውስጥ ብቻ እንደማያበቃ በማንሳት፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “እንደ ኢሳያስ” ባሉ አካላት ላይ “ዲፕሎማሲያዊ ጫና” እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ለዚህ ጽሑፍ ምላሽ የሰጡት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ፤ ዶ/ር ሙላቱ “ኤርትራን ‘በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ግጭት’ እየቀሰቀሰች ነው በሚል በመክሰስ ሐሰተኛ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል” ሲሉ ተችተዋል።

ዶ/ር ሙላቱን “ታሪካዊ ሁነቶችን አዛብቶ በማቅረብ” የከሰሱት የኤርትራው ሚኒስትር፤ አገራቸው በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈችው “ህወሓት በኤርትራም ላይ መጠነ ሰፊ እና በየደረጃው የሚከናወን ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ” ስለነበረው እንዲሁም “በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ” መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ የማነ፤ አገራቸው ከህወሓት ጥቃት ላመለጡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት “መጠለያ” መስጠቷን ጠቅሰው፤ ኤርትራ “በኢትዮጵያ የጨለማ ቀናት ላበረከተችው የማይተካ ሚና በይፋ ምስጋና ማግኘቷን” አስታውሰዋል።

የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት “ኢትዮጵያ መንግሥት እና የአገር ውስጥ ተዋናዮቹ ጉዳይ” መሆኑንም የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አንስተዋል።

“ኤርትራ፤ በኢትዮጵያ ውስጣዊ የሆነን ጉዳይ የማደነቀፍም ሆነ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም” ሲሉ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ቀረበውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን የማደናቀፍ ክስ ተከላክለዋል።

ኤርትራ ወታደሮቿን “ዓለም አቀፍ እውቅን ባላቸው ሉዓላዊ ድንበሮች ውስጥ እንደገና” ማሰማራቷን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ “የኤርትራ እና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን” ውሳኔን “በቅን ልቦና ያልተቀበሉ ወይም ግጭት የመቀስቀስ” ዓላማ ያላቸው አካላት እንደ ባድመ ያሉ አካባቢዎች በማንሳት የኤርትራ ወታደሮች “በድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ” የሚል “ሐሰተኛ ውንጀላ” እያቀረቡ ነው ብለዋል።

በኤርትራ ላይ እየተደረጉ ያሉት “መጥፎ ዓላማ” ያላቸው ድርጊቶች እና “ትንኮሳዎች” በዚህ ብቻ የተገደቡ እንዳልሆኑ አቶ የማነ በፅሁፋቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ምክንያቱን “ለመረዳት በሚያዳግት” ሁኔታ “ባለፉት ወራት” በኤርትራ ላይ “ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል” ሲሉ ከስሰዋል።

እንደ አቶ የማነ ገለጻ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እያደረገ ያለው፤ “‘ከተቻለ በሕጋዊ፣ ካስፈለገም በወታደራዊ’ መንገድ ወደቦችን እና የባሕር በር ለማግኘት ባለው አጀንዳ” እንደሆነም አስፍረዋል።

የኤርትራው መንግሥት ቃል አቀባይ በዚህ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመው “ግልፅ ያልሆነ” የመግባቢያ ስምምነት በቀጣናው ላይ “ድንገተኛ የሆነ አለመረጋጋት እና እረፍት የለሽነት” ፈጥሯል ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሌላ የማያባራ ውስጣዊ ጦርነት ውስጥ ገብታለች” ሲሉም በጽሑፋው ጠቅሰዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፤ “ቀጣናውን የከበቡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮች የሚፈልቁት እና ማዕከላቸውን የሚያገኙት በኢትዮጵያ እንጂ በሌላ ቦታ አይደለም” ብለዋል።

በአገሪቱ ያለውን “ግጭት ምንጩ ከውጭ በማስመሰል ወይም ኤርትራን ማምለጫ በማድረግ” በአገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ እንደማይገኝም ሚኒስትሩ አቶ የማነ በጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በግላቸው የጻፉት እና በአል ጀዚራ ላይ የወጣውን ጹሁፍ እንዲሁም ከኤርትራ በኩል የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop