የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር የፋይናንስ ህግን ጥሰዋል በሚል መቻል ስፖርት ክለብ ላይ የ21 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሲዳማ ቡና ላይ የ18 ሚሊዮን ብር ቅጣት ማስተላለፉን አስታውቋል።
ኩባንያው መቀለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማም እያንዳንዳቸው በ3 ሚሊዮን ብር እንዲቀጡ መወሰኑን ሰኞ የካቲት 17/2017 በማኅበራዊ ገጾቹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በአራት ክለቦች ላይ በድምሩ የ45 ሚሊዮን ብር ቅጣት ተላልፏል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ህጉን ተላልፈዋል ያላቸውን የአራቱ ክለብ 15 ተጫዋቾችን እያንዳንዳቸውን በ200 መቶ ሺህ ብር ቀጥቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ አመራሮችም ለሁለት ዓመት በየትኛም ክለብ ውስጥ በአመራርነት እንዳይሳተፉ አግዷል።
ኮሚቴው አደረግኩት ባለው ማጣራት የክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር በተሰኘው መመሪያ ላይ ከተቀመጠው ህግ ውጪ የ7 ተጫዋቾችን ዝውውር ፈጽሟል የተባለው መቻል ስፖርት ክለብ ላይ በድምሩ የ 21 ሚሊዮን ብር ቅጣት ጥሎበታል።
በሌላ በኩል የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በተመሳሳይ የሕግ ጥሰት 6 ተጨዋቾችን በማስፈረሙ በደምሩ 18 ሚሊዮን ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
ክለቦቹ ፈጽመውታል የተባለውን ጥሰት አክስዮን ማኅበሩ ሲያብራራ የተጫዋቾች የቅድመ ክፍያ ገንዘብን አክሲዮን ማኅበሩ በማያወቀው መንገድ በሶሦስተኛ ወገን አማካኝነት ለመክፈል ሞክረዋል ብሏል።
ይህም ተጫዋቾች ፈርመውበታል ከተባለው ይፋዊ ገንዘብን በላይ የሆነ ገንዘብ እንዲያገኙ ያደረገ ነው ተብሏል።
በዚህ ሂደት ፊርማቸውን ያኖሩ ተጫዋቾችም የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
ምንይሉ ወንድሙ፣ ዳዊት ማሞ፣ ደሳለኝ ከተማው፣ ነስረዲን ኃይሉ፣ በረከት ደስታ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ፍሪምፖንግ ሜንሱ የተባሉ የመቻል ስፖርት ክለብ ተጫዋቾች ቅጣቱ የተጣለባቸው ናቸው።
በተመሳሳይ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተጨዋች የሆኑት ሀብታሙ ታደሰ፣ መስፍን ታፈሰ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ የብሑራዊ ቡድን አምበል ያሬድ ባየህ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ደስታ ዳሙ እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
በተጨማሪም ህግ በመተላለፍ የአብስራ ተስፋዬ የተባለውን ተጫዋች ያስፈረመው መቀለ 70 እንደርታ እንዲሁም እስራኤል እሸቱ የተባለውን ተጫዋች ያስፈረመው ሀዋሳ እያንዳንዳቸው በ3 ሚሊዮን ብር ተጨዋዎቹ ደግሞ በ200 ሺህ ብር ተቀጥተዋል።
ደምብ ተላልፏል የተባሉት መቻል ስፖርት ክለብ እና ሲዳማ ቡና በቀጣዮቹ የተጫዋች ዝውውር እንዳይሳተፉ እና ተጫዋቹን በማስፈርም ሂደት የተሳተፉ የክለብ ቦርድ ሰብሳቢ እና ሥራ አስኪያጆቸን ጨምሮ ለሁለት ዓመታት በማንኛውም ክለብ ውስጥ በአመራር እንዳይሳተፉ አግዷቸዋል።
ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክልል ከተሞች እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21 ሚሊዮን ብር የተቀጣው መቻል በ27 ነጥብ በሊጉ ሰንጠረዥ 4ኛ ላይ ይገኛል። 18 ሚሊዮን ብር የተቀጣው ሲደማ ቡና ደግሞ በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቅጣት የተጣለባቸው ክለቦች እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር ቅጣቱን በተመለከተ በዚህ ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ረቡዕ 19/2017 የሚከፈት ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ የውድድር ዘመን ደግሞ ሐሙስ ይጀመራል።
ባለፈው እሑድ የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ በሰጡት መግለጫ ሌሎች ተጫዋቾች ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አስታውቀው ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ዝውውሮች የፋይናንስ ሕጉን እንዳይተላለፉ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸውም ገልፀዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)