የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ያልተለመደ ጉዞ አደረጉ።
ፕሬዚደንቱ ከአገራቱ መሪዎች ጋር ይወያዩባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ አጀንዳዎች መካከል በጋዛ እና በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲሁም የነዳጅ ዘይት ምርት ይገኙበታል።
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) መጋቢት ወር ላይ የእስር ትዕዛዝ ካወጣባቸው በኋላ ከሩሲያ የወጡት ፑቲን፣ ሐሙስ ከኢራኑ መሪ ጋር በሞስኮ እንደሚገናኙም ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው፣ ዩክሬናውያን ሕጻናትን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሩሲያ አባረዋል በሚል የጦር ወንጀል ክስ ነበር። ሆኖም የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም ሆኑ ሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልተቀበሉትም።
የእስር ማዘዣውን ተከትሎም የሩሲያው መሪ ነሐሴ ላይ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን የብሪክስን ጉባኤ እና መስከረም ላይ በሕንድ የተካሄደውን የቡድን 20 አገራት ስብሰባን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ አልተገኙም።
ፑቲን አሁን ላይ ጉዞ ያደረጉት ተፅዕኖ ለመፍጠር እና ምዕራባውያኑ ሩሲያን ለማግለል የሚያደርጉትን ጥረት ለማዳከም ፍላጎት ስላላት ነው ተብሏል።ፑቲን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች (ዩኤኢ) ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የሩሲያው መሪ ለዩኤኢ ፕሬዚደንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን “ ግንኙነታችን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉም ነግረዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ንግድ እና ነዳጅ ዘይት ከሚነጋገሩባቸው አጀንዳዎች ውስጥ እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን ክሬሚሊን በመግለጫው “ የአረቡ ዓለም የሩሲያ ዋነኛ የምጣኔ ሃብት አጋር ናት “ ብሏል። የሩሲያው ፕሬዚደንት በቀጣይ ከልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ለመገናኘት ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል። በቴሌቪዥን በተላለፈ አጭር ውይይት ወቅትም ፑቲን ልዑሉ ሞስኮን እንዲጎበኙ ጋብዘዋቸዋል።
ፑቲን “ እያደገ የመጣውን ወዳጅነታችንን ማንም ሊከለክለው አይችልም” በማለትም በቀጠናው ባሉት ጉዳዮች ዙሪያ “መረጃዎችን መለዋወጥ እና ግምገማ ማድረግ” አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ልዑሉ በበኩላቸው የሁለትዮሽ ትብብሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉትን በርካታ ውጥረቶች ለማስወገድ ማገዛቸውን ተናግረዋል።
አወዛጋቢው የሩሲያ ቼቺን ሪፐብሊክ መሪ ራምዛን ካድይሮቭም በፑቲን እና በሳዑዲው ልዑል ስብሰባ ላይ ታይተዋል።
ከስብሰባው ቀደም ብሎ ክሬሚሊን ሁለቱ መሪዎች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ያለው ግጭት እንዲረግብ በሚያደርጉ መንገዶች ዙሪያ እንዲሁም በሶሪያ ፣ በየመን እና ሱዳን ያለው ግጭት በተመለከተ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እንደሚወያዩ ገልጿል።
የሩሲያ የዜና ወኪል ታስም የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ፑቲን እና ልዑል አልጋ ወራሹ በኦፔክ ትብብር ላይ መምከራቸውን እንዳረጋገጡ ዘግቧል።
ፑቲን ከኢራኑ ፕሬዚደንት ኢብራሒም ሬሲ ጋር ሐሙስ ዕለት ተገናኝተው በጋዛ ስላለው ጦርነት እንደሚወያዩም የክሬሚሊን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ፑቲን እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ላይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የጎበኙት በሩሲያ የተያዘችውን የዩክሬን ክፍል፣ ኢራን እና ቻይናን ብቻ ነው።