በኢትዮጵያ የሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ የሚሰማ ጉዳይ ነው።
የእግር ኳስ ክለቦች በገንዘብ አቅማቸው አናሳነት ጋር በተያያዘ ህልውናቸውም እየተፈተነ ነው።
ለተጫዋቾች ደመወዝ ባለመክፈላቸው በርካታ ክሶች ተደጋግመው ይቀርቡባቸዋል። ተገቢውን ክፍያ ባለመፈጸማቸው ንብረታቸው ስለተያዘባቸው ክለቦች የተሰማበት አጋጣሚ አለ።
ሆኖም በተጋነኑ ክፍያዎች፣ የሆቴሎች፣ ትራንስፖርት አገልግሎት እና ሌሎች ወጪዎች ምክንያት ከዓመት ዓመት ክለቦች የሚያወጡት ወጪ እየሻቀበ ይገኛል።
ለምሳሌ ያህል እንኳን የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ወጪ በምናይበት ወቅት አምና ከነበረበት በ38 በመቶ ማደጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሚል እና የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር መልክ ለማስያዝ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል።
በዚህ መመሪያ መሠረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች ቡድን አባላት የሚያወጡት ወጪ ገደብ ተበጅቶለታል።
ከሰሞኑ በተደረገው 4ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ መጽደቁን የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ይናገራሉ።
ለዚህ መመሪያ መነሻ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት አክስዮን ማህበሩ ያስጠናው የዳሰሳ ጥናት አንድ ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጥናቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችን በተመለከተ የተካሄደ ሲሆን፣ ጊዜ የወሰደ እና ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት እንደነበርም አስታውሰዋል።
የፕሪሚየር ሊጉ ቁመና፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ያለው ግንኙነት፣ የክለቦች አወቃቀር፣ የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ምን መምሰል አለበት የሚሉና ሌሎችንም ጉዳዮችን ዳሷል።
ገደቡ ያካተታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች
የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር “የክለቦቹ ብቻ ሳይሆን የተጨዋቾችም የህልውና ጉዳይ ነው” በማለት የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ ለዚህም ሲባል የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲዘጋጅለት ምክንያት ሆኗል።
“ይህ የክፍያ ስርዓት አስተዳደር ቦርዱ ያዘጋጀው መመሪያ ነው። መመሪያው ከእግር ኳስ ፌደሬሽን ጋርም ውይይት ተደርጎበታል” ብለዋል አቶ መሉጌታ።
በተጨማሪም መመሪያው ለክለቦችም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት፤ በጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
ዋና ዋና ጉዳዮች
በሂደት የሚካተቱ እንዳሉ ሆነው መመሪያው 10 አንቀጾች አሉት።
በቀጣዩ ዓመት 2017 ተግባራዊ እንዲሆን እቅድ ተይዞለታል።
መመሪያው የተጫዋቾችን እንዲሁም የአሰልጣቾችን ደመወዝ እንደማይገድብ አቶ ሙሉጌታ ያስረዳሉ።
“ማንም የተጫዋችን ደመወዝ መገደብ አይቻልም፤ ለአሰልጣኝን ደመወዝ ይህን ክፈሉ ያንን አትክፈሉ ብሎ መገደብ አይቻልም” ብለዋል።
እንደ አቶ ሙሉጌታ ከሆነ መመሪያው ዋና ዓላማው ያደረገው ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሚከፈለውን አጠቃላይ ክፍያ ጣሪያ ማስቀመጥን ነው።
መመሪያው ክለቦች ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረጉ፤ ለሦስተኛ ወገኖች የሚከፈሉ ወጪዎችን መቀነስ እና በአጠቃላይ ግልጽነት ያለው የክለቦችን ወጪ ስርዓት እንዲዘረጋ ማድርግን ታሳቢ አድርጓል።
በዚህ ወቅታዊ አቅምን ብቻ መሠረት ያደረገ የወጪ ስርዓት እንዲኖር እና የክለቦችን ቀጣይነትም ከግምት ያስገባ የፋይናንስ ስርዓት መሆኑን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የ2017 የክለቦች የክፍያ ጣሪያ 57 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ጽድቋል።
“ይህ ወጪ ማለት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሚሳተፉ ክለቦች ዋና ቡድን ተጫዋቾች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ለደመወዝ እና ለጥቅማ ጥቅም የሚያወጡት ነው” ብለዋል።
ይህንን የወጪ ጣሪያ ለማስቀመጥ በተለይም በ2015 እና 2016 ክለቦች ያወጡትን ከግምት ገብቶ የተዘጋጀ ነው።
ክለቦች ለዋናው ቡድን ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣት አይፈቀድላቸውም።
“ይህ ማለት ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት እና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚያወጧቸውን ወጪዎችን አይጭምርም።”
የአውሮፓ ክለቦች የፋይናንስ ተጠያቂነትን ለማስፈን ‘ፋይናንሻል ፌይር ፕሌይ’ በሚል ክለቦች ያገኙት ገቢ እና ወጪያቸውን የሚገድቡበት አሠራር አለ።
ፕሪሚየር ሊጉ ለዚህ ገደብ እንደ መነሻ የወሰደው የአውሮፓውያኑ የፋይናንስ ፖሊሲ ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ይህንን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“እኛ ገቢንም ወጪንም መቆጣጠር ሳይሆን ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሚወጣውን ክፍያ የመቆጣጠር ጉዳይ [ላይ ነው ያተኮርነው]። የሚወጣው ክፍያ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደዋለ ተደጋግሞ ይገለጻል። ተጫዋቾቹ፣ ክለቡ እና አሰልጣኙ እየተጠቀሙ አይደለም። የአገሪቱ እግር ኳስም ከዚህ ተጠቃሚ አይደለም። ይህንንም ስርዓት የማስያዝ ጉዳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
‘ችግራችን ነው’ በማለት ይህ ሃሳብ የቀረበው በክለቦቹ ሲሆን “ያስጠኑትም ያጸደቁትም ክለቦቹ ናቸው” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ “አተገባበሩን በተመለከተ የሚዋቀር ኮሚቴ ይኖራል” ብለዋል።
አተገባበሩን የሚከታተለው ኮሚቴ የህግ ባለሙያዎች፣ የፋይንስ ደህንነት፣ የጸረ ሙስና ኮሚሽን እና ሌሎችን በመያዝ ይዋቀራል።
ወደ ስድስት የሚጠጉ አባላት የሚኖሩት ይህ ኮሚቴ ከአክስዮን ማህበሩ ጋር በመተባበር የሚቆጣጠረው ይሆናል።
ተጫዋቾችም ሆኑ አሰልጣኞች ለአንድ ክለብ ከፈረሙበት ቀን ጀምሮ እስከ ውድድር ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ክትትል ይኖራል።
ይህንን ተግባራዊ የማያደርጉ ክለቦች ደግሞ ቅጣት የሚጠብቃቸው ይሆናል።
“የብር፣ የነጥብ ቅነሳ. . . ሊሆን ይችላል። እነዚህ ደንቡን ይፋ ስናደርግ የሚገለጹ ናቸው” ብለዋል አቶ ሙሉጌታ።
ዋናው ጉዳይ የክለቦችን ወጪ መገደብ አይደለም። የወጪ ገደብ የተጣለው በተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ላይ ብቻ ሲሆን ሌሎች ወጪዎች ግን ምንም ገደብ አይኖርባቸውም።
ቡድኖቹ ከ 57 ሚሊዮን ብር አይብለጥ እንጂ ለተጫዋቾች እና አሰልጣኞች መክፈል ይችላሉ።
ለእያንዳንዱ ተጫዋች እና አሰልጣኝም ይህንን ያህል ክፈሉ የሚል ነገር መመሪያው አላስቀመጠም።
ሌሎች ወጪዎችን ግን ክለቦቹ እንዳላቸው አቅም ማውጣት የሚችሉበትን ዕድል ክፍት ያደረገ ነው።
ከዚህ ቀደም የተጫዋቾችን ደመወዝ ለመወሰን ሙከራ ተደርጎ ነበር። ተጫዋቾች ወርሃዊ ደመወዛቸው ከ50 ሺህ ብር እንዳይበልጥ የሚለው አሠራርም ከጥቂት ዓመታት በፊት ወጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር።
ሆኖም ይህን ዓይነቱን አሠራር የሚደግፍ ህግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል። በመሆኑም “ይህንን ያህል ክፈሏቸው ብሎ ማስገደድ ሌላ ተጠያቂነት የሚያመጣ ጉዳይ ነው” ብለዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የተጫዋቾቹን ደመወዝ የመገደብ ጉዳይ ነበር። የአሁኑ ግን ለአሠራር አስቸጋሪ በመሆኑ ጥናት ላይ ተመስርቶ “ጥቅል ክፍያው ላይ ገደብ ማድረግ ነው። ይህ በአፈጻጸም ደረጃም ይለያል። ስርዓትም የማዘጋጀት ጉዳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ስለዚህ በዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ ተንቀሳቀሱ፤ ቀሪውን ደግሞ ለእግር ኳስ ልማት አውሉት የሚል ነው” ብለዋል።
የአሁኑ የፋይናንስ ስርዓት መመሪያው የተጫዋቾችንም የሆነ ክለቦችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ለመጨው የውድድር ዓመት፣ 2017 የጸደቀው ገንዘብ ያለፉት ሁለት ዓመታት የክለቦች ወጪን ግንዛቤ ውስጥ ባመስገባት ሲሆን በቀጣይነትም መሻሻሎች ይኖራሉ ተብሏል።
ለ2018 የውድድር ዘመን ደግሞ የዋጋ ግሽበት እና ሌሎች ጉዳዮች ከግምት ገብተው የወጪ ገደቡ እንደሚሻሻል ኃላፊው ይገልጻሉ።
ይህ መመሪያ ከመጽደቁ በፊት ዝውውር እንዳይፈጸምም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለክለቦች ደብዳቤ ጽፏል።
ይህም የሆነው ውል ያላቸውን ተጫዋቾች እና አዲስ የወጣውን የወጪ ገደብ ከግምት አስገብተው ወደ ተጫዋቾች ዝውውር እንዲገቡ ለማድረግ በማለም ነው።
ክለቦቹ በዘንድሮው ዓመት ከተቀመጠው የ57 ሚሊዮን ብር ገደብ በላይ ክፍያ ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች ቢከፍሉም፤ ለ2017 የውድድር ዓመት በተቀመጠው የወጪ ገደብ ውስጥ አድርገው ቡድናቸውን እንዲያዋቅሩ የሚያስገድድ ይሆናል።
ይህ የወጪ ገደብ በእጅ አዙር የተጫዋቾችን እና የአሰልጣኞችን ገቢ የሚገደብ ነው የሚል ቅሬታ አያስነሳም ወይ? በሚል ቢቢሲ ለአቶ ሙሉጌታ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።
እሳቸውም በምላሹ “መመሪያው ለተጫዋችም ሆነ ለአሰልጣኝ የሚከፍለውን ክፍያ በተመለከተ ገደብ አያወጣም። ለተጫዋቾቻችሁ ይህን ያህል ክፈሉ የሚል ነገርም የለውም። የሚያስቀምጠው ስለጥቅል ክፍያ ጣሪያ ነው። ስለዚህ በጀቱን የማስተካከል የክለቡ ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
በአዲሱ መመሪያ ዙሪያ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበርን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )