112ኛ ዓመት ልደታቸውን ሊያከብሩ ዝግጅት ላይ የሚገኙት የዓለማችን አዛውንቱ ወንድ፤ ረዥም ዕድሜ መኖር “ምንም የተለየ ምስጢር የለውም” ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1912 በእንግሊዟ ሊቨርፑል ከተማ የተወለዱት ጆን ቲኒስውድ፤ ጊነስ ዎርልድ ሬከርድስ ከተባለው የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ሽልማት ሲቀበሉ ይሄን ያክል ዕድሜ የኖርኩት “እንዴት እንደሆነ አላውቀውም” ብለዋል።
የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ የሆኑት ጆን፤ ሳውዝፖርት በሚገኝ የዕድሜ ባለፀጋዎች መኖሪያ ነው የሚገኙት። ባለፈው ሚያዚያ የ114 ዓመቱ ሁዋን ቪሴንቲ ፔሬዝ ሞራ መሞታቸውን ተከትሎ በዕድሜ ያሉ ቁጥር አንድ ወንድ ባለፀጋ የሚለው ማዕረግ ለጆን ተሰጥቷል።
በአሁኑ ወቅት የዓለማችን የዕድሜ ባለፀጋዋ ሰው ጃፓናዊቷ ቶሚኮ ኢቶካ ሲሆኑ በዚህች ምድር ላይ 116 ዓመታትን ኖረዋል።
“ወጣት ሳለሁ ብዙ እንቀሳቀስ ነበር” የሚሉት ጆን “ብዙ እርምጃ አደርግ ነበር፤ ነገር ግን ከሌሎች የተለየ ያደረግኩት ነገር የለም” ሲሉ ያክላሉ።
“ወይ ብዙ ዓመት ትኖራለህ፤ ወይ አጭር ዕድሜ ትኖራለህ። ምንም የምትለውጠው ነገር የለም።”
ጆን ቲኒስውድ፤ የተወለዱት ታይታኒክ የተሰኘችው መርከብ በሰመጠች ዓመት ሲሆን፤ 112ኛ ዓመት ልደታቸውን ለማክበር እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
“እኔ ከሌሎች የተለየሁ ነኝ ብዬ አላስብም። ምንም የሚለየኝ ነገር የለም።”
ጆን ሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ከተቋቋመ ከ20 ዓመታት በኋላ ነው የተወለዱት። ሊቨርፑል ካነሳቸው ዋንጫዎች ከሁለቱ በቀር ሁሉንም አይተዋል ማለት ነው።
አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር የሁለት ዓመት ሕፃን ነበሩ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ደግሞ 27ኛ ዓመት ልደታቸውን በማክበር ላይ ነበሩ።
በብሪታኒያ ጦር አርሚ ፔይ ኮር ሆነው ሲያገለግሉ ወታደሮችን ወደ ካምፓቸው በመመለስ እና የምግብ አቅርቦት በማስተባበር ነበር። አሁን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተረፉት ትልቁ የዕድሜ ባለፀጋ ሆነዋል።
ባለቤታቸው ብሎድዌንን የተዋወቋቸው 1942 ሊቨርፑል ከተማ በአንድ የዳንስ መድረክ ላይ ነው።
ልጃቸው ሱዛን የተወለደችው በ1943 ሲሆን ጥንዶቹ ለ44 ዓመታት አብረው ከቆዩ በኋላ ባለቤታቸው ብሎድዌን በ1986 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በ1972 ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ለሼል እና ቢፒ የሒሳብ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል።
ሁሌም አርብ በመጣ ቁጥር ዓሳ እና የድንች ጥብስ መብላት የሚያስደስታቸው ጆን የሚከተሉት የተለየ የአመጋገብ ሥነ-ሥርዓት እንደሌላቸው ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2012 100ኛ ዓመታቸውን ከደፈኑ በኋላ በ14 ዓመት ከሚበልጧቸው ከሟቿ የእንግሊዝ ንግሥት ኤሊዛቤት ሁለተኛ በየዓመቱ የልደት ስጦታ ይላክላቸው ነበር። ይህን ባሕል ንጉሥ ቻርልስ ሶስተኛም ቀጥለውበታል።
እሳቸው ልጅ በነበሩ ጊዜ ከነበረው ሁኔታ እና አሁን ካለው የትኛው የተሻለ ነው ተብሎ ስለጊዜው የተጠየቁት ጆን “በእኔ አስተሳሰብ ድሮ ከነበረው ይህን ያህል የተሻሻለ አይደለም” ሲሉ መልሰዋል።
“ምናልባት በአንዳንድ አካባቢዎች ሁኔታቸው ተሻሽለው ሊሆን ይችላል። በአንዳንግ አካባቢዎች ደግሞ ሁኔታው ብሷል።”
በ2013 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጃፓናዊው ጂሮሞን ኪሙራ 116 ዓመት ከ54 ቀናት በመኖር ቁጥር አንድ የዕድሜ ባለፀጋ ነበሩ።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)