የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከጥር 30/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ የቤንዚን ሽያጭ ህጋዊ ሰሌዳ ላላቸው ተሽከርካሪዎች በኩፖን ብቻ እንዲከናወን ውሳኔ አስተላለፈ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሳድሁን “ይሄንን ሂደት በማይከተሉ [እና] አሰራሩን በማይዘረጉ የአስተዳደር መዋቅሮች እና የማደያ ባለቤቶች ላይ ህጋዊ የሆነ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ውሳኔውን ያስተላለፈው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም ለሁሉም የክልሉ ዞኖች የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ በጻፈው ደብዳቤ ነው።
የቢሮው ደብዳቤ የነዳጅ ምርት እጥረቱ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱን” ያትታል። ደብዳቤው አክሎም “ህገ ወጥ የነዳጅ ምርት ሽያጭም በዛው ልክ እያሻቀበ” መሆኑን ጠቁሟል።
የባለ ሁለት እግር ሞተሮች “በየቀኑ ተመላልሶ መቀዳት ለኮንትሮባንድ ሽያጭ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ችግሩን ለማባባስ ዋነኛ መንስኤዎች” መሆናቸውን ማረጋገጡን ቢሮው በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።
አቶ ሳሙኤልም በተመሳሳይ “ሞተር ሳይክል የያዙ ወጣቶች ቀኑን ሙሉ ሌላ ስራ ትተው ከአንዱ ማደያ ወደ ሌላ ማደያ እየተዘዋወሩ ነዳጅ በመቅዳት በሃይላንድ እየተሸጠ መሆኑን አረጋግጠናል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ምርቱ በተፈለገው አግባብ እየተሰራጨ ስላልሆነ አሰራሩን በተለያየ ጊዜ ለማስተካከል የሚደረጉ ጥረቶች አሉ” የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ “አንዱ ግብይት ስርዓቱን በኤሌክትሮኒክስ የሽያጭ ዘዴ ማከናወን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በጻፈው ደብዳቤ፤ “የነዳጅ ምርት ሽያጭ በኤልክትሮኒክስ (ቴሌ ብር እና ሲቢኢ ብር) የመገበያያ መንገዶች ብቻ እንዲፈጸም” ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
“ይህን ችግር ለመቅረፍ ሁለተኛው አማራጭ ከኤሌክትሮኒክስ ሽያጭ በተጨማሪ ኩፖንን ተጠቅሞ ሽያጭ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ሲሉ አቶ ሳሙኤል ክልሉ የወሰደውን ሁለተኛ አማራጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ ቢሮ በደብዳቤው የነዳጅ ማደያ ያለባቸው ከተሞች ከጥር 30/2017 ዓ.ም ጀምሮ “የትኛውም ተሽከርካሪ በኩፖን ብቻ እንዲስተናገድ” የሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከዚህ በተጨማሪም “ታርጋ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ህጋዊ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እስኪያወጡ ድረስ እንዳይስተናገዱ” አሳስቧል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ ነዳጅ ለመግዛት ግዴታ የተደረገው ኩፖን “የአሽከርካሪው እና የተሽከርካሪው ሙሉ መረጃ [እና] ሊቀየሩ የማይችሉ የተሽከርካሪ መለያዎች” ይሰፍሩበታል።
ነዳጅ ከአንድ ማደያ የሚያስፈልገውን ነዳጅ የቀዳ አሽከርካሪ “ሁለተኛ ተመልሶ የመቅዳት ዕድል አይኖረውም” የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ “እንደከዚህ በፊቱ እየቀዳ ወስዶ የሚገለብጥበት ከእጥፍ በላይ እየሸጠ ማኅበረሰቡን የሚያስቃይበት ሁኔታ እንዳይኖር እና ቁጥጥር ለማድረግ ስለተፈለገ ነው ይህን አሰራር ተግባራዊ የምናደርገው” ሲሉ ተናግረዋል።
ይኸው አሰራር ከዚህ በፊት እንደ ዲላ እና አርባምንጭ ባሉ ከተሞች መሞከሩን ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል “ውጤታማ ስለነበር ነው አሁን ወደ ተግባር የገባነው” ብለዋል።
ይሄንን አሰራር በማይከተሉ የአስተዳደር መዋቅሮች እና የማደያ ባለቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ “ከዚህ በፊትም ብዙ የእርምት እርምጃዎች ሲወሰዱ ነው የቆዩት አንዳንድ ማደያዎች አካባቢ የማሸግ፣ በገንዘብ የመቅጣት እርምጃዎች ተወስደዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ምርት አላግባብ ይዘው በተገኙ አካላት ላይ ምርት በመውረስ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራዎችም በተመሳሳይ እየተሰራ” መሆኑንነም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ የተጻፈው ደብዳቤም “ያንን [እርምጃ] አጠናክረን እንቀጥላለን በሚል ነው የተጻፈው” ሲሉ አክለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ነዳጅ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ የሚያደርግ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል።
በአዋጁ መሠረት “የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ” ማንኛውም ሰው፤ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)