የፋሲል ግንብ እድሳት እንዴት ተካሄደ? የመንጣቱ ምክንያት ምንድን ነው? Leave a comment

በኢትዮጵያ የአጼዎች እና የሥልጣኔ መናገሻነት ስማቸው ከሚጠቁሱት ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል ጎንደር አንዷ ናት።

ጎንደርን ማዕከል ያደረገው የ17ኛው እና የ18ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የእድገት፣ የምርት መፍለቂያ፣ የሃይማኖት ማዕከል እንዲሁም በኪነጥበብ ታላቅ ስፍራ የደረሰችበት ወቅት እንደሆነ ይጠቀሳል።።

የእነዚህ ታላላቅ ተግባራት ማሳያዎች መካከል ደግሞ ከጎንደር ነገሥታት መካከል አንዱ በነበሩት አጼ ፋሲለደስ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው የፋሲል ግንብ ነው።

በአስደናቂነቱ፣ በታሪካዊነቱ እና በኪነ ህንጻ ጥበቡ ብዙ የተባለለት እና እና በዩኔስኮ የዓለማችን ቅርስ አንዱ ሆኖ የተመዘገበው የፋሲል ግንብ ተሰነጣጥቆ እና አርጅቶ መቆየቱ በርካቶች ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ ነው።

የጥገና እድሳት እየተከናወለት ያለው ታሪካዊው የፋሲል ግንብ በቅርቡ ይፋ መደረጉን ተከትሎ መወዛገቢያ መሆኑ አልቀረም። ታሪካዊው ሽሯሟ ቀለም ያለው የፋሲል ግንብ ቀለሙ ነጥቶ መታየቱ ለበርካታ መላምት ክፍት እንዲሆን አድርጎታል።

የታሪካዊው ግንብ ቀለም ለዘመናት ከሚታወቅበት ተለውጦ ለምን ነጣ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳም ምክንያት ሆኗል።

ለዚህ ምላሽ የሚሰጡት በጥገና እድሳቱ በአማካሪነት እንዲሁም በጥናት የተሳተፉት አንጋፋው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ የፋሲል ግንብ የተሠራበትን የግንባታ ግብዓት በመጥቀስ ነው።

የፋሲል ግንብ ህንጻ ከመቶ ዓመታት በፊት ሲገነባ በአነስተኛ ድንጋዮች እና በኖራ ሲሆን፣ ለረጅም ዓመታት ዝናብ፣ በፀሐይ እና በተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስጥ ሲያልፍ በርካቶች የሚያውቁትን ይሄንን “ሽሯማ” መልክ እንዳመጣ ፋሲል ጊዮርጊስ ይናገራሉ።

አሁን እድሳቱ የተደረገበት ኖራ አዲስ በመሆኑ ቀለሙ ነጣ እንዳለም ያስረዳሉ ይላሉ።

ፋሲል እንደሚገልጹት የእድሳት ሥራው የተከናወነው የፋሲል ግንብ በመጀመሪያ በተገነባበት ማቴሪያል (ቁስ) በዋናነት በኖራ እና በድንጋይ ነው።

“የቅርስ አጠባበቅ ሕግን በተከተለ መልክ ነው የተሠራው” ይላሉ።

“የኖራው አዲስ መሆን ብቻ ይሄንን ነጣ ያለ ቀለም አምጥቷል” የሚሉት አርክቴክቱ ፋሲል የኖራ እና የድንጋይ መልኩ ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ወደ ድሮው መልኩ ይመለሳል ይላሉ።

ልዩነቱ አዲስ የመሆን እና የማርጀት ጉዳይ ነው ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ።

የፋሲል ግንብ መጀመሪያ ሲሠራ ኖራው ለብዙ ወራት ወይም ለዓመታት ተቀብሮ የነበረ ሲሆን፣ አሁንም ሲታደስ መነሻውን ተከትሎ ኖራው ለበርካታ ጊዜያት እንዲቀበር ተደርጎ ጥገናው መካሄዱን ጠቅሰዋል።

ቅርሶች በተፈጥሮ፣ በፀሐይ፣ በዝናብ፣ በአቧራ ምክንያት በዓመታት ቀለማቸው እየተቀየረ የሚሄድ ሲሆን፣ ይሄኛውም ከዓመታት በኋላ የሚታወቀውን ቀለም ይይዛል ይላሉ።

በዓለም አቀፉ የቅርስ ጥገና ሕግ መሠረት ዋነኛው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በተሠራበት ቁስ (ማቴሪያል) ታድሷል ወይ? የሚለው ነው የሚሉት ፋሲል፤ በተሠራበት ድንጋይ እና ኖራ መልሶ መጠገኑ ዋናው ነገር እንደሆነ አስረድተዋል።

“ይህንንም በትክክል መሥራቱን አረጋግጠናል” ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች የድሮ ቀለሙን ለማምጣት ለመልክ ሲባል ኬሚካል እንደሚቀላቀል የሚጠቅሱት አርክቴክት ፋሲል፤ እነዚህ ግን ኬሚካል ነክ ነገሮች ስለሆኑ ያልታሰበ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

“ቀለሙ እንደ ድሮው ቢመስል እንወድ ነበር፤ ሆኖም ለቀለም ተብለው የሚጨመሩ ነገሮች ያልታሰበ አደጋን በቅርስ ላይ ያመጣሉ” በማለት ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

አክለውም በዓለም የቅርስ አጠባበቅ ደረጃ ዋነኛው ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው የመነሻ ሃሳቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኖራው ትክክለኛ እና አስተማማኝ በመሆኑ የጥንቱ እንደያዘ የጥገና እድሳቱ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

“መነሻውን ሳይለቅ ጥርሳችንን ነክሰን የሠራንበት ነው” ሲሉ የሚናገሩት ፋሲል፣ የቀደመ መልኩ በጊዜ ብዛት ይመጣል ሲሉ የነበረው ገጽታ በጊዜ ሂደት እንደሚመለስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ታዲያ ይሄ በርካቶች በቀደመ መልኩ (ሽሯሟ) መልክ የሚያውቁት የፋሲል ግንብ መቼ ተመልሶ ይመጣ ይሆን? በሚል ቢቢሲ አርክቴክቱን ጠይቋአዋል።

ዝናብ ሲመታው እና የአየር ሁኔታዎች ሲፈራረቁበት እየተቀየረ ይሄዳል የሚሉት ፋሲል፤ ህንጻው ወደ ቀደመ ቀለሙ ለመመለስም ከሦስት እስከ አራት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል ብለዋል።

ፋሲል እንደሚገልጹት “አንዳንድ ቦታ ላይ በጣም የጠቋቆሩ [የግንቡ አናት ላይ] አካላት ነበሩ” ድንጋዮቹ ወደ ነበሩበት ለመመለስ እስከ አምስት ዓመት ድረስ የሚደርስ ወይም የግንቡ አናት ላይ ያሉትን ጠቆር ያሉትን የቀደመ ገጽታ ለማምጣት ከዚያ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ ያስረዳሉ።

የፋሲል ግንብ የእድሳት ጥገና እንዴት ተካሄደ?

የፋሲል ግንብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የተመዘገበ የዓለም ቅርስ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ስር ያለ ይህ ቅርስ ባለፉት ዓመታት በእርጅና የህልውና ስጋት እንደገጠመው ሲነገር ቆይቷል።

የፋሲል ግንብን በተመለከተ የኢትዮጵያ ቅርስ፣ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ከጥቂት ዓመታት በፊት ሙሉ ጥናት አድርጎ እንደነበር የሚያስታውሱት ፋሲል፤ እሳቸውም አባል የነበሩበት ይህ ጥናት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እና በጀት ባለመኖሩ ጥናቱ እንዲቀመጥ ተደርጎ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት መካሄድ የጀመረው እድሳት ሲጀመር ቀደም ሲል በባለሙያዎች የተደረገውን ጥናት መሠረት አድርጎ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በቅርሶች ጥገና እና እድሳት ጊዜ አንደኛው የሚታየው ቀደም ሲል የነበሩ ጥገናዎች ምን ምን ዓይነት ሂደትን ተከትለው ነበር የተከናወኑት የሚለው የጥናቱ አካል እንደሆነ ያወሳሉ።

የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ጥገናዎች ተደርጎላቸዋል። ከሃያ ዓመት ገደማ በፊት በአሁኑ ደረጃ ባይሆንም መጠነኛ ጥገና እንደተደረገላቸው ፋሲል ይናገራሉ።

ከዚያ ቀደም ደግሞ በ1960 ዓ.ም. ሳንድሮ አንጄሊኒ በተባለው ጣልያናዊ አርክቴክት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም ሞኑመንቶች ፈንድ እንዲሁም በዩኔስኮ አስተባባሪነት ጥገና ተደርጎላቸው ነበር። በወቅቱ የተደረገውን ጥገና በዋነኛነት የማጠናከር እንዲሁም ሊወድቁ ያሉ ነገሮችን እንደ ብረት ማሰሪያ በማስገባት ግንቡን እንዲደግፍ ማድረግ ነበር።

ባለሙያው የሚጠቅሱት ስህተት ተፈጽሞበታል የሚሉት ሌላኛው የእድሳት ሥራ የተከናወነው በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ፋሽስት ወረራ ወቅት የተደረገውን ነው።

በጎንደር ከትሞ የነበረው የጣሊያን አገዛዝ የጎንደርን አብያተ መንግሥት እንደ አስተዳደር ማዕከል ይጠቀምበት እንደነበር አስታውሰዋል። ከ1928 – 1936 የቆየው ወራሪ ኃይል የእቴጌ ምንትዋብ ግንብን፣ የአጼ ዮሐንስ ቤተ መጻህፍትን እና ሌሎችንም ህንጻዎች አድሷል።

ጣሊያኖች እድሳቶቹን በሚያከናውኑበት ወቅት የሠሯቸው ስህተቶች ብለው ፋሲል የሚነቅሷቸው ‘ኮምቦ ሞርታር’ ወይም የሲሚንቶ እና ኖራ ቅልቅል መጠቀማቸውን ነው።

በአሁኑ እድሳት በጣልያኖቹ በእቴጌ ምንትዋብ ግንብ እና በአጼ ዮሐንስ ቤተ መጻህፍት ላይ የተደረገው ያ የሲሚንቶ እና የኖራ ቅልቅል እንዲነሳ እና በዋነኛው ኖራ እንዲተካ ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት ሌላኛው የቀለሙን ልዩነት ያመጣው ይሄው የማስተካከል ሥራም እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ሌላኛው የጣሊያኖቹ ስህተት ብለው የሚጠቅሱት በአጼ ፋሲል እና የአጼ ዮሐንስ ቤተ መዘክሮች ላይ የተደረገውን እድሳት ነው።

እነዚህ ቤተ መዘክሮች ሲታደሱ በጥንት ጊዜ ከተሰሩበት ድንጋይ በበለጠ በትላልቅ ድንጋዮች ተሠርተው ነበር። በአሁኑ ወቅት በተደረገው የእድሳት ጥገና እነዚህ ትልልቅ ድንጋዮች እንዲነሱ እና “ወደ ቀደመ ማንነታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አይቼያለሁ” ይላሉ። ጥገናው ቀድሞ ወደ ነበረበት የመመለስ ሂደት እና የጥንቱን እንዳይለቅ የማድረግ ነው ይላሉ።

የፋሲለደስ ግንብ በቅርሱ ጣሪያ ላይ ከሚታዩ ችግሮች በተጨማሪ ግድግዳዎቹ ተሰነጣጥቀው፣ በቅርፁ የመንሸራተት እና የመዝመም እክሎችም ገጥመውት እንደነበር ከዚህ ቀደም የሥነ ሕንፃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ማሞ ጌታሁን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የፍቅር ቤተ መንግሥት ከተዘጋ ከ10 ዓመት በላይ እንዲሁም የዮሐንስ ቤተ መንግሥትም እንዲሁ መዘጋቱን እና ነው የታላቁ እያሱ ቤተ መንግሥትም ከፈረሰ በኋላ ጥገና እንዳልተደረገለትም ቢቢሲ ከጎንደር የቅርስ አስተዳደሪዎች ሰምቶ ነበር።

የዳዊት ቤተ መንግሥት እና የአፄ በካፋ ቤተ መንግሥትም እንዲሁ አደጋ ላይ እንደሚገኙ ሌሎቹም በርካታ ስንጥቆች እንዳሉባቸው እና በአንድና በሁለት ሴንቲ ሜትር ይለካ የነበረው ስንጥቅ ወደ 5 ሴንቲ ሜትር መስፋቱም ተጠቅሶ ነበር።

ቅርሶች እደሳ ሲደረግላቸው ምን ዓይነት ሂደቶችን መከተል አለበት?

ማንኛውም ቅርስ ሲጠገን መጀመሪያ ታሪኩ እንደሚጠና የሚጠቅሱት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፤ እንዴት ነው የተሠራው? እነማን ናቸው የሠሩት? ምን ዓይነት የግንባታ ግብዓቶችን ተጠቀሙ? የአሠራሩ ቴክኖሎጂ በደንብ ተደርጎ ይጠናል ይላሉ።

ጥናቱ ከተካሄደ በኋላ ቀጣይ የሚሆነው ሥራ አሁን ቅርሱ ያለበትን ሁኔታ መለካት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በመቀጠልም ዕቅዶች እና ንድፎች የሚዘጋጁ ሲሆን ንድፎቹ ላይ ፓቶሎጂ (የጉዳቱን መጠን) የሚያሳይ ንድፍ ይዘጋጃል።

ለምሳሌ ያህል የሚጠቅሷቸው የተሰነጠቀ ካለ ለምን ተሰነጠቀ? መንስዔዎቹ ምንድን ናቸው? በውሃ፣ በመሬት እንቅስቃሴ፣ በክብደት ብዛት ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሚለው ተለይቶ ትንታኔ እንደሚሠራ ይጠቅሳሉ።

ይህንንም በሰውኛ ሲገልጹት “ልክ የታመመ ሰው እንደማከም” ማለት ነው፤ የችግሩን መንስዔ ከተለየ በኋላ ለደረሰው ጉዳት መፍትሄ ይፈለጋል ይላሉ።

በአብዛኛው የቅርስ ጉዳቶች ከዝናብ እና ከዕድሜ መግፋት የሚመጡ ከመሆናቸውን አንጻር ለእነሱ ተገቢ መፍትሄ ይፈለጋል። ለጉዳቱ መፍትሄ የሚሆን በዘላቂነት ያንን መቋቋም ወይንም መቀልበስ በሚያስችል መልኩ ጥገናው ይካሄዳል።

መቀየርም ያለበት ነገር ካለ ያንን የህንጻውን ዕድሜ ሊጨምርና ሊያጠናክር የሚችል ነገር ነው ታስቦ የሚደረገው።

በአብዛኛው ጥገና በሚደረግበት ወቅት አዲስ ወይም ባዕድ የሆነ ቁስ የማይጨመር ሲሆን፣ ድንገት ባዕድ የሆነ ማቴሪያል ከገባ ይላሉ አርክቴክቱ በቀላሉ ሊነሳ ወይም ሊቀለበስ በሚችል መልኩ ነው የሚገባው።

ለምሳሌ የሚጠቅሱትም አንዳንድ ህንጻዎች ወለላቸው በክብደት ምክንያት ሊወድቅ የሚችል ከሆነ በዚያን ወቅት ወለሉን የሚደግፉ ብረት ወይም እንጨት እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።

ይህ በሚሆንበት ወቅት የገባው አዲስ ነገር ተመልካች ሊረዳው እና ሊያውቀው በሚችል መልኩ ነው የሚሠራው። በተጨማሪም አንድ ቅርስ ከተጠገነ በኋላ በዋናነት ክትትል እና የተለያዩ እንክብካቤዎች እንደሚሹ አጽንኦት ይሰጣሉ።

በአሁኑ ወቅት እድሳቱ እየተከናወነ ያለው የፋሲል ግንብ ጥገናው ከተጠናቀቀ በኋላ ከ30 እስከ 40 ዓመት ድረስ መቆየት እንደሚችል አርክቴክቱ ገልጸዋል። ሆኖም ይህ የሚወሰነው ተከታታይ የሆነ መጠነኛ ጥገና ሲደረግለት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በተለይም በመናፈሻው (ቴራሱ) ላይ የተቸከሉት እንጨቶች የዕድሜ መጠን ውስን ነው። በተለይም የኢትዮጵያ አየር ጠባይ ለእንጨት አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር እነዚህን ጨምሮ የተወሰኑ አካለት ከፍተኛ ክትትል እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት

የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1979 ዓ.ም. በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ቤተ መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማርያም፣ ራስ ግምብ እና ደረስጌ ማርያምን ያቀፈ ነው።

በአፄ ፋሲለደስ ግንብ ውስጥ ያሉት አብያተ መንግሥታት ከ100 በላይ ክፍሎች አሏቸው። ባለ ሦስት እና አራት ፎቅ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 7 ሄክታር (70 ሺህ ስኩየር ሜትር) ይሸፍናሉ።

ግንቡ የተሠራው ከ300 – 400 ዓመታት በላይ በኖረ የድንጋይ ካብ ሲሆን፣ በዋናነት ድንጋይ፣ ኖራ እና እንጨት ጥቅም ላይ ውለዋል። በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መሠራቱም ይነገርለታል።

በአፄ ፋሲለደስ ግንብ ውስጥ ያሉት አብያተ መንግሥታትን ልዩ የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ነገሥታት የራሳቸውን አሻራ እና ታሪክ ለትውልድ ትተው ማለፋቸው ነው። ቤተ መንግሥቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

1. የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት፡- ይህ ቀደምቱ ነው። ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ለማሳነፅ 10 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።

2. የአፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት፡- አፄ ፋሲለደስ ለ36 ዓመታት ከነገሡ በኋላ ልጃቸው እሳቸውን ተክተው ወደ ሥልጣን መጥተው ከ1667-1682 ዓ. ም. ሲነግሡ የተሠራ ነው።

3. የታላቁ አዲያም ሰገድ እያሱ ቤተ መንግሥት፦ የነገሡት ከ1682-1706 ዓ. ም. ነበር። ንጉሡ ጥሩ ፈረሰኛ ነበሩና በኮርቻ ቅርፅ የተሠራ ውብ ቤተ መንግሥት እንደተሠራ ታሪክ ያወሳራል።

4. የአፄ ዳዊት ቤተ መንግሥት፦ ለአምስት ዓመታት (ከ1716-1721 ዓ. ም.) ሲነግሡ ያሳነፁት ህንፃ ነው። ትልቅ የሙዚቃ ግንብ ያለው ሲሆን፣ ግንባር ቀደሙ የኪነ ጥበብ ማሳያ ህንፃ እንደሆነ ይነገራል። ጥቁር አንበሳ የሚባሉት አንበሶች መኖሪያ ይገኝ የነበረውም በዚህ ነበር።

5. የንጉሥ መሲሰገድ በካፋ ቤተ መንግሥት፦ ለዘጠኝ ዓመታት (ከ1721-1730) የነገሡ ሲሆን፣ የሳቸው ፍላጎት የነበረው ሕዝቡን ግብር የሚያበሉበት ትልቅ ሕንፃ መሥራት ነበር። ስለዚህም ከ250 በላይ ሰዎች መያዝ የሚችልና ፈረሶች የሚቆሙበት ቦታ ያለው ትልቅ የግብር አዳራሽ አሳነጹ።

6. የእቴጌ ምንትዋብ ቤተ መንግሥት፦ ከ1730-1755 ዓ. ም. የነገሡ ሲሆን፣ በጣና ገዳማት ላይም አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop