ማጨስን ያገዱ አገራት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ እገዳዎችስ ምን ውጤት አስገኙ? Leave a comment

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) “ሲጋራ የማያጨስ ትውልድ ለመፍጠር” በሚል ሲጋራ እንዳይሸጥ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ በፓርላማው ይሁንታ አግኝቶ አልፏል።

ይህ ሕግ ከጸደቀ በዓለም ላይ በሲጋራ ላይ ከተጣሉ ከባድ እገዳዎች መካከል አንዱ የሚሆን ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

እስካሁን ከ150 በላይ አገራት ማጨስ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የተለያዩ ሕጎችን አውጥተዋል።

በዩኬ ማጨስን የሚያግደው ረቂቅ ሕግ ምን ይላል?

በአዲሱ ረቂቅ ሕግ መሠረት በእንግሊዝ እና በዌልስ ሲጋራን እና ሌሎች ኒኮቲን ያላቸው የትምባሆ ውጤቶችን ከአውሮፓውያኑ ጥር 1/2009 በኋላ ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች መሸጥ ሕገ ወጥ ነው።

ስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድም ተመሳሳይ ሕግ ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን ላይ በዩኬ እንደ ሲጋራ ያሉ የትምባሆ ውጤቶችን ለመግዛት የሚቻልበት ዝቅተኛው ዕድሜ 18 ዓመት ነው።

አዲሱ ሕግ ይህንን በየዓመቱ በአንድ ዓመት ከፍ የሚያደርገው ሲሆን፣ በጊዜ ሒደት ማንም ሰው ትምባሆ መግዛት እንዳይችል ሊያደረግ ይችላል።

ይህ ሕግ የረቀቀው እንደ አውሮፓውያኑ 2023 በኒው ዚላንድ የፀደቀውን ሕግ መነሻ በማድረግ ነው።

የኒው ዚላንድ ሕግ በተመሳሳይ ከ2009 በኋላ ለተወለዱ ታዳጊዎች ትምባሆ እንዳይሸጥ ይከለክላል።

ሕጉ ባለንበት የአውሮፓውያኑ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ተግባራዊ መሆን የነበረበት ቢሆንም፣ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ሕጉ ተሽሯል።

ማጨስ ላይ እገዳ የጣሉ ሌሎች አገራትስ የትኞቹ ናቸው?

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው 151 አገራት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው እና በቤት ውስጥ ማጨስን የሚከለክል ሕግ አላቸው።

እነዚህ ሕጎች ከ10 ሰዎች መካከል የሰባቱን [5.6 ቢሊዮን የዓለምን ሕዝብን] ሰዎች በሚያጨሱት ትምባሆ ምክንያት ከሚመጡ የጤና ጠንቆች እንደሚጠብቁ ድርጅቱ ገልጿል።

በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ማጨስን የከለከለች የመጀመሪያዋ አገር አየርላንድ ናት።

አየርላንድ ቢሮ ውስጥ፣ መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እንዲሁም እንደ የሕዝብ መጓጓዣዎች ባሉ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እንዳይጨስ እገዳ የጣለችው ከ20 ዓመታት በፊት ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 16 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ተመሳሳይ ሕግ አውጥተዋል፤ ነገር ግን የተወሰኑ አባል አገራቱ በደንብ ተግባራዊ እንደማያደርጉት ኅብረቱ ገልጿል።

አሁን ላይ በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ እያንዳንዱ አገርም የፀረ ማጨስ ሕግ አለው።

ኡራጓይም እንደ አውሮፓውያኑ 2006 ዝግ በሆኑ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እንዲሁም በሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ማጨስን አግዳለች።

ፓራጓይ ማጨስን በተመለከተ ብሔራዊ ሕግ በማውጣት ከአህጉሯ የመጨረሻዋ አገር ናት።

ነዋሪዎቿ የትምባሆ ውጤቶችን ማጨስ የሚችሉት በውስን፣ ሕዝብ ባልተሰባሰበባቸው እና ከቤት ውጪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ብቻ እንዲሆን ገደብ የጣለችው ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር።

ሜክሲኮ በዓለም ላይ ጥብቅ ከሆኑ ገደቦች አንዱ የሆነውን የፀረ ማጨስ ሕግ ያስተዋወቀችው ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነበር።

ይህ ሕግ በመናፈሻዎች፣ በባሕር ዳርቻዎች፣ በሆቴሎች፣ በቢሮዎች፣ በምግብ ቤቶች እንዲሁም በሌሎች የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ማጨስን ይከለክላል። ይህ ማለት ሜክሲኳውያን ከቤታቸው ውጪ የትም ቦታ ማጨስ አይችሉም።

ካናዳ በካናዳ በወጣው ሕግ መሠረትም ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ የትምባሆ አምራቾች በሚያመርቷቸው ሲጋራዎች ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ማተም ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ፓን አሜሪካ የጤና ድርጅት ከሆነ በአሜሪካ በማጨስ እንዲሁም አጫሾች በሌሎች ሰዎች በሚፈጥሩት ብክለት ምክንያት በዓመት ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ይሞታሉ።

ማጨስን የሚያግዱ ሕጎች ምን ውጤት አስገኙ?

የዩኬ የጤና እና እንክብካቤ ጥናት ብሔራዊ ተቋም በ21 አገራት ላይ የተጣሉ የፀረ ትምባሆ ገደቦች ያስገኟቸውን ውጤቶች ተመልክቷል።

ተቋሙ በዚህ ጥናቱ ክልከላዎቹ የልብ ህመም እና ስትሮክ እንዲሁም የመተንፈሻ አካል ህመም በሆኑት ብሮንካይትስ እና አስም በሽታዎች የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን አመልክቷል።

ዝግ በሆኑ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እና የሥራ ቦታዎች ማጨስን የሚከለክለው እና እንደ አውሮፓውያኑ 2007 የወጣው ሕግ በመላው ዩኬ እንዲተገበሩ ሆኗል።

ብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ሕጉ በመላ ዩኬ ከተተገበረ በኋላ በነበረው ዓመት ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ ሲሆን፣ ሆስፒታል የገቡት 1 ሺህ 200 ሰዎች ብቻ ነበሩ።

በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች የተጣለውን የማጨስ እገዳን ተከትሎ በስኮትላንድ ከአስም ጋር በተያያዘ ሆስፒታል የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በአንድ አምስተኛ ዝቅ ማለቱንም የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመልክቷል።

በስኮትላንድ እገዳው ከመጣሉ በፊት በአስም ምክንያት ሆስፒታል የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር በየዓመቱ 5 በመቶ ይጨምር ነበር።

እገዳዎቹ በርካታ ሰዎች ትምባሆ የማጨስ ልምዳቸውን እንዲተዉም አነሳስቷል።

እንደ የዩኬ መንግሥት መረጃ ከሆነ በአገሪቷ እንደ አውሮፓውያኑ 2006፣ 22 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች አጫሽ ነበሩ። ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት ወደ 14 በመቶ ዝቅ ብሏል።

ባለፉት 15 ዓመታት በዓለም ዙሪያ በተወሰዱ የፀረ ማጨስ እርምጃዎች ምክንያት የዓለም የአጫሾች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው በ300 ሚሊዮን ገደማ መቀነሱንም የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop