ሞባይላችን እንቅልፋችንን እያደናቀፈ መሆኑን ልብ ብለናል? ሌሊት ለምን እንቅልፍ እምቢ ይለናል? Leave a comment

አንዳንድ ሰው ሌሊት ዓይኑ ይፈጣል። አንዳንዶች በውድቅት ሌሊት ንቅት ብለው እንደፈጠጡ ያነጋሉ።

በውድቅት አንድ ጊዜ ከተነሱ መልሶ ለመተኛት ይቸገራሉ።

ኢንሶማኒያ ይባላል የሕክምና ስሙ። ሁሉም ሰው በሕይወት ዘመኑ ያጋጥመዋል።

ጥቂቶችን ለጥቂት ጊዜ ብቻ ያሰቃያቸዋል። ብዙዎች ደግሞ ለዘመናት በእንቅልፍ እጦት ይሰቃያሉ።

አንዳንዴ የዕድሜ ጉዳይ ነው። የአኗኗር ዘይቤያችንም ተጽእኖ አለው። አልኮል እና ስልክም ነገሩን ያብሱታል።

ቢቢሲ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

ዶክተር ፌይዝ ኦርካድ በሰሴክስ ዩኒቨርስቲ የሳይኮሎጂ ምሁር ናቸው።

“ብዙውን ጊዜ መተኛት የሚያቅተኝ ሐሳብ ሲበዛብኝ ነው። ያን ጊዜ መጽሐፍ አነባለው። ሰውነቴ ዘና ማለት ይጀምራል። ከዚያ ሳላስበው እተኛለሁ” ይላሉ።

ዶክተር አሊ ሐሬ በእንቅልፍ ላይ ጥናት የሚያካሂደው ማኅበር የብሪቲሽ ስሊፕ ሶሳይቲ መሪ እና በሮያል በርመተን ሆስፒታል ሐኪም ናቸው።

“ብዙውን ጊዜ መተኛት የሚያቅተኝ ባሌ አልጋ ላይ ሲገላበጥ እና ሲያንኮራፋ ነው። ይህን ጊዜ አልጋ እለያለሁ። ሌላ ክፍል ሄጄ እተኛለሁ” ይላሉ።

ኢንሶማኒያ ምንድነው?

በሳምንት ለሦስት ቀናት እንቅልፍ ለመተኛት መቸገር እና ይህም ቢያንስ ለሦስት ወራት ከዘለቀ ‘ኢንሶማኒያ’ ይባላል። የሕክምና እርዳታ የሚያሻው ይህን ጊዜ ነው።

አልፎ አልፎ እንቅልፍ እምቢ አለን ማለት ግን ኢንሶማኒያ አለብን ማለት አይደለም።

የሚያስጨንቁን ነገሮች አእምሯችን ላይ ካሉ ያነቁናል፣ እረፍት ማድረግን ሳይሆን ለችግሩ መፍትሄ እንድንሰጥ ይገፋፉናል።

ሌላው ደግሞ ዕድሜ ነው። የእንቅልፍ ሰዓት ከዕድሜ ጋር ያረጃል። ዕድሜ ሲገፋ የእንቅልፍ ጥራት የእንቅፍ ርዝመት እየቀነሰ ይመጣል።

ብዙ ሰዎች እያረጁ ሲመጡ እንቅልፋቸው የተበጣጠሰ እየሆነ ይመጣል።

ጎረምሶች በበኩላቸው በጊዜ መተኛት እና አርፍዶ መነሳት ይችላሉ። ሲያረጁ ደግሞ ቶሎ ተኝቶ፣ ወፍ ጭጭ ሳይል መንቃት ይመጣል።

ለጭንቀት የተጋለጡ ሰዎች አሉ። ይሄ ነገር አንዳንዴ በቤተሰብ ይወረሳል። ጭንቀታም ሰዎች ለእንቅልፍ ችግር ይጋለጣሉ።

ከእንቅልፍ ከነቃን በኋላ መልሶ ለመተኛት መቸገር

ድንገት እኩለ ሌሊት ላይ ከእንቅልፍ ቢባንኑ እና መልሰው መተኛት ባይችሉስ?

ባለሙያው እንደሚሉት ይሄ ነገር የብዙ ሰዎች ችግር ነው። መፍትሄውም ቀላል አይደለም።

“ስንነቃ መልሼ መተኛት አልችልም ብለን አብዝተን ማሰብ እንጀምራለን። ለመተኛት በጣም ሰናስብ እና ስንሞክር ደግሞ እንቅልፍ የማጣት ዕድላችን ይጨምራል” ይላሉ።

መፍትሔው ለመተኛት መሞከር ሳይሆን ለመንቃት መወሰን ነው። ለመተኛት እየሞከሩ እንቅልፍን ከማጥፋት እንቅልፍ በራሱ መንገድ እንዲመጣ መተው የተሻለው አማራጭ ነው።

“ለምሳሌ ላለመኮላተፍ ስንሞክር የበለጠ እንኮላተፋለን። አንድን ባህሪ ለማዳበር በተፈጥሯዊ መንገድ እንዲመጣ መፍቀድ አለብን” ይላሉ ባለሙያው።

የተሻለ እንቅልፍ ለማግኘት ሁሌም በተመሳሳይ ሰዓት መተኛት እና መንቃት ይመከራል።

ሁሌም በተመሳሳይ ቦታ በመተኛት አእምሮ እንቅልፍ እና መተኛ ቦታን እንዲያስተሳስር ማድረግ ሌላው መንገድ ነው።

የእንቅልፍ እጦት

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

ዶ/ር ሐሬ እንደሚሉት ከእንቅልፍ ከነቃን በኋላ ለግማሽ ሰዓት ከአልጋ መነሳት ተመልሰን እንድንተኛ ይረዳል።

የእንቅልፍ መድኃኒቶች ከመውሰድ ይልቅ የሥነ ልቦና ድጋፍ ማግኘትን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

ሰዎች የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ወይም ለመቆጣጠር የባህሪ ለውጥ ላይ የሚያተኩረው የሥነ ልቦና ድጋፍ በእንግሊዝኛው ኮግኒቲቭ ቢሄቪየራል ቴራፒ ከ70 አስከ 80 በመቶ በሚጠጉ ሰዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ አሳይቷል።

አንዳንድ ሰዎች ማግኒዥየም መውሰድ ለእንቅልፍ ይረዳል ብለው ያምናሉ። ባለሙያዎች ግን ይሄን መላ ምት የሚደግፍ በቂ ጥናት የለም ብለው ይከራከራሉ።

“እምብዛም በእንቅልፍ ላይ ለውጥ ሲያመጣ አይታይም” ይላሉ ባለሙያው።

ሜላቶኒን በመውሰድ የተሻለ እንቅልፍ ለማግኘት የሚሞክሩም አልታጡም። ውጤቱ ግን ከሰው ሰው ይለያያል። ለሁሉም ሰው ላይሠራም ይችላል።

ስልክ፣ አልኮልና ዕድሜ

ማረጥ፣ የአልኮል መጠጥ ማብዛት እና ወጥ የሆነ የሥራ መርሃ ግብር አለመኖር እንቅልፍ ያዛባሉ።

ማረጥ ለሴቶች አስቸጋሪ የእንቅልፍ መቀዠባበር የሚፈጥር ነገር ነው ይላሉ ዶ/ር ሐሬ። ይህ የሚከሰተው ደግሞ የሆርሞን ለውጦች ስለሚኖሩ ነው።

ከዚህ ሌላ በማረጥ ጊዜ የአእምሮ ጭንቀት በርከት ይላል።

አልኮልን በተመለከተ ዶክተር ኦርካርድ የሆርሞን ለውጥ መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን በሌሊት ለሽንት መነሳት እና የአእምሮ እረፍት ማጣትን ያስከትላል።

አልኮል የእንቅልፍ ጸር ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን ቢራ ስቀማምስ በደንብ እተኛለሁ ይላሉ። በጊዜ ሂደት ግን እውነታው እየተቀየረ ይመጣል።

ሌላው ሐኪሙ የሚመክሩት ዋና ነገር ዓይናችንን ለስክሪን አለማጋለጥ ነው።

በመኝታ ሰዓት በፍጹም ስልክ አትመልከቱ ይላሉ። ሌሊት እንቅልፍ እምቢ ሲላችሁም ስልካችሁን ከመመልከት ታቀቡ ይላሉ።

ይህ ግን ለብዙ ወጣቶች የሚስማማ ምክር አይደለም፤ በተለይ በዚህ ዘመን።

ለዚህ ደግሞ መፍትሄው ስልካችሁን ከመኝታ ቤት ውጭ ማሳደር መልካም ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop