ሶማሊያ በቀይ ባህር ዳርቻዋ ለኢትዮጵያ የባህር በር ሰጥታለች መባሉ ሐሰት ነው ሲሉ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሙዓሊም ፊቂ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተሰራጨው መረጃው ሃሰት ነው ሲሉ አስረግጠው “ፍጹም መሰረት የለውም” ሲሉ ሐሙስ፣ ታህሳስ 17/ 2017 ዓ.ም ባወጡት የኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው “ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እንዲሁም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽነትን ለማስፈን ምንግዜም ቁርጠኛ ናት” ብለዋል።
የኢትዮጵያን እና የሶማሊያን ቁርሾ እልባት ያስገኘው የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ ፣ ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የንግድ የባህር በር በቀይ ባህር በኩል ሰጥታለች መባሉን ተከትሎ ነው ሚኒስትሩ ይህንን ማስተባባያ ያወጡት።
ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት ግብጽ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የምታገኘው መዳረሻ በንግድ ወደብ ላይ የተወሰነ እና በሶማሊያ ግዛት ሉዓላዊነት ስር የሚቆይ ይሆናል ማለታቸውን አንዳንድ ሚዲያዎች ዘግበው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የውጭ ጉዳይ የምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዲ ዘነበ በበኩላቸው የአንካራውን ስምምነት አስመልክቶ
“ከሞቃዲሾ ጋር የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር፣ የባህር በር ማግኘት ብቻ ሳይሆን በህንድ ውቅያኖስ በኩል ወደ ኤደን ባህረ ሰላጤ መዳረሻ ማግኘት ያስቻለ ነው” ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመውን የአንካራን ስምምነት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ያስገኘውን ዘርፈ ጥቅም አወድሰዋል።
ዶ/ር ዘነበ ይህንን የተናገሩት “የተሻሻለው የኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚል በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በተዘጋጀ የቃለ መጠይቅ መድረክ ላይ መሆኑ በፓርቲው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ሰፍሯል።
ስምምነቱ፣ የተከተለተው መግለጫ እና ከእሱ ጋር የተያያዘው የድርጊት መርሃ ግብር ለአፍሪካ ቀንድ በርካታ ጥቅሞችን ማስገኘቱን ጠቅሰዋል። ቀጣናዊ የጋራ አጀንዳዎችን ከማምጣት በተጨማሪ ውጥረቶችን በመቀነስ እና ሰላምን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ “ህጋዊ ጥያቄ” አላት የሚለውን “ዕውቅና እንዲሰጠው አድርጓል” ሲሉ አሞካሽተውታል።
ከዚህ ባለፈ ” ኢትዮጵያ ስለ ድንበር አካባቢዎች እና ክልሎች ከመናገር ባለፈ በህንድ ውቅያኖስ መዳረሻን መወያየት” ያሻገረ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ በቀይ ባህር መዳረሻ የውጭ አካል መገኘት ተቀባይነት የለውም ሲሉ አሳስበው ነበር።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር አብዲላቲ “ከቀይ ባህር ዳርቻ ካሉት የቀይ ባህር ሃገራት በስተቀር የየትኛውም አካል መገኘት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ከሰሞኑ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በካይሮ የሁለትዮሽ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።
የሚኒስትሮቹ ውይይት በቅርቡ በቱርክ አደራዳሪነት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰውን ድርድር ጨምሮ ቀጣናዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ነበር።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።
ቱርክ በአገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ፕሬዝዳንቷን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት ለወራት ስትጥር ቆይታ ከስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አስታውቀዋል።
ኤርዶዋን ስምምነቱን “ታሪካዊ” በማለት በሁለቱ አገራት መካከል “ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊያ በር እንደታገኝ የሚያደርግ ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
“በነበረን ስብሰባ በተለይ ኢትዮጵያ ካላት የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ፍላጎት አንጻር፣ ወንድሜ ሼክ ሐሰን ኢትዮጵያ ወደ ባሕር መተላላፊያ በር እንድታገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል ኤርዶዋን።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ስር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ” እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
ለዚህም ሁለቱ አገራት ንግግሮችን በማካሄድ በወራት ውስጥ አጠናቀው ለስምምነት ለመቅርብ ተስማምተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት መቻሉን አመልከተዋል።
“የኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ፍላጎት ጎረቤቶቻችንን ጭምር የሚጠቅም ሰላማዊ ጥረት ነው፣ ይህ ፍላጎት በትብብር መንፈስ እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባውም” ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም “ገንቢ ውይይት” ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን “በትብብር፣ በወዳጅነት እና በጠላትነት ሳይሆን በጋራ ለመሥራት ከሚኖር ፈቃደኝነት ጋር ወደ ቀጣዩ ዓመት ያሸጋግራል” ብለዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)