በምያንማር የወንጀል ካምፖች ተይዘው የነበሩ “138 ኢትዮጵያውያን” መለቀቃቸውን ምንጮች ገለጹ……. Leave a comment

በምያንማር በሚገኙ የሳይበር ወንጀል ካምፖች በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው የነበሩ “138 ኢትዮጵያውያን” ተለቅቀው በትናንትናው ዕለት ወደ ታይላንድ መግባታቸውን በሀገሪቱ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ አማርኛ ተናገሩ።

ኢትዮጵያውያኑ ዜግነታቸውን የማጣራት እና ሌሎች ሂደቶችን ካለፉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮቹ ገልጸዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር ብዛት ያላቸው የሳይበር (የበይነ መረብ) ማጭበርበር የሚከናወንባቸው ካምፖች የሚገኙባት ሀገር ነች።

በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 154 ግቢዎች ውስጥ የሚፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀሎች በአብዛኛው የሚከናወኑት “የሥራ ዕድል ታገኛላችሁ” በሚል ተታልለው በግዳጅ ለዚህ ድርጊት በተዳረጉ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ነው።

ከእነዚህ ዜጎች መካከልም ታይላንድ ውስጥ ሥራ ታገኛታችሁ በሚል ተታልለው ወደ ምያንማር የተወሰዱ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።

የኢትዮጵያውያኑ ተጎጂዎች ወላጆች ኮሚቴ 300 ገደማ ኢትዮጵያውያንን ስም የመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር “ሦስት ሺህ ይደርሳል” ተብሎ እንደሚገመት ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያውያኑ መደብደብ እና በኤሌክትሪክ ሾክ መደረግን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ቅጣቶች ይፈጸሙባቸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከእነዚህ ካምፖች ለማስወጣት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ከምያንማር መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።

ምያንማር በሚገኙ እነዚህ ካምፖች ውስጥ የነበሩ 260 የውጭ ሀገር ዜጎች ትናንት ረቡዕ የካቲት 5/2017 ዓ.ም. ከሰዓት ተለቅቀው አጎራባች ወደ ሆነችው ታይላንድ ገብተዋል።

ከ19 ሀገራት ከተወጣጡት ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላዩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በታይላንድ የሚገኙ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት የውጭ ሀገራት ዜጎች ዝርዝር መረጃ እንደሚያሳየው፤ ከ260ዎቹ ተመላሾች መካከል “138 ያህሉ ኢትዮጵያውያን” ናቸው።

አንድ ምንጭ፤ “በዚህ ቡድን ውስጥ ብቻ 138 ኢትዮጵያውያን አሉ። ነገር ግን ማንነታቸው ላይ የፓስፖርት እና ሌሎች መረጃዎች አልተሰበሰቡም” ብለዋል።

ከኢትዮጵያውያን ቀጥሎ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የጎረቤት ሀገር ኬንያ ዜጎች ሲሆኑ፣ 24 ኬንያውያን ተለቅቀዋል ተብሏል።

የፊሊፒንስ ዜጎች በ16፤የማሌዥያ ዜጎች ደግሞ በ15 ተከታዮቹን ደረጃዎች እንደያዙ ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።

ከተለቀቁት ሰዎች መካከል የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ እና የቡሩንዲ ዜጎች እንደሚገኙበት የቢቢሲ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ቢሮ ዘግቧል።

ከተለቀቁት ዜጎች መካከል 221 ያህሉ ወንዶች፤39 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እንደሆኑም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

ከተለቀቁት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል “የተወሰኑት ታይ ቻንግ” ከተባለው የማጭበርበሪያ ካምፕ እንደሆነ ቀሪዎቹ ደግሞ “ኬኬ ፓርክ” እና “ሽዌ ኮኮ” ከተባሉት ብዛት ያላቸው ካምፖች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ነው።

በካምፖቹ ውስጥ የነበሩት 260 ሰዎች እንዲለቀቁ ያደረገው አካባቢውን የሚቆጣጠረው “ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው።

ቡድኑ፤ በካምፑ የነበሩ ሰዎችን ያስለቀቀው አጎራባቿ ታይላንድ ካምፖቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ በሚል ወደ አካባቢው የሚሄደውን የኤሌክትሪክ ኃይል እና የነዳጅ አቅርቦት ካቋረጠች በኋላ ነው።

ካረን በተባለው የምያንማር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድኑ ያስለቀቃቸውን ሰዎች ወደ ታይላንድ የላከ ሲሆን ሲደርሱም የሀገሪቱ ሠራዊት ተረክቧቸዋል።

የተለቀቁት ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በታይላንድ መንግሥት መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

የተለቀቁት ሰዎች፤ የታይላንድ መንግሥት ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝርዝር ሰለባዎች በዘረጋው “national referral mechanism” በተባለው ሂደት የማጣሪያ ውስጥ ያልፋሉ።

ይህ ሂደት የመጡት ሰዎች በትክክልም የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚከናወን ነው።

ሰዎቹ ተጎጂ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ዜግነታቸውን የማጣራት እና ሌሎች ሂደቶች ይከናወናሉ።

ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ከካምፖቹ ወጥተው ወደ ታይላንድ የገቡ ኢትዮጵያውንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሂደት ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅ ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ መንግሥት በታይላንድ ኤምባሲ የሌለው መሆኑ የዚህ መጓተት አንዱ ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመላክ የሚሠሩ ድርጅቶች በታይላንድ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ሥራዎች ደርቦ የያዘውን በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲን የሚያገኙት ታይላንድ በሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ በኩል ነው።

ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ የሕንድ ኤምባሲ ለሚቀርቡለት የዜግነት ማረጋገጥ ጥያቄዎች “በቶሎ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑ” የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን በፍጥነት መመለስ ላይ ስጋት እንደሚፈጥር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት ከካምፖቹ ወጥተው ወደ ታይላንድ የገቡ 10 ገደማ ኢትዮጵያውያንም በማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ አክለዋል።

የተለቀቁ ሰዎች ሻንጣዎቻቸውን ይዘው እየተራመዱ

የፎቶው ባለመብት,THAI NEWS PIX

የምስሉ መግለጫ,ከተለቀቁት ሰዎች የተወሰኑት

ቢቢሲ፤ በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲ እና በምያንማር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የያዘው በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለተለቀቁት ዜጎች መረጃ ይኖራቸው እንደሆነ ለማጣራት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

ወደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የተደረጉ የስልክ ጥሪዎችም ወዲያው ምላሽ አላገኙም።

ከምያንማር ወደ ታይላንድ የገቡትን ሰዎች በተመለከተ፤ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሀገሮቻቸው ኤምባሲዎች ጋር በመተባባር የሰነድ ማረጋገጥ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚያከናውን የሀገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የምያንማር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፉተም ዊቼያቻይ፤ ሀገራቸው በታጣቂዎች ተለቅቀው ወደ ታይላንድ የሚገቡ ሰዎችን በሙሉ እንደማይቀበሉ መናገራቸውም ዘገባዎች ጠቅሰዋል።

“የመጡበት ሀገር የማይቀበላቸው ከሆነ አንቀበላቸውም” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በምያንማር ከማጭበርበሪያ ካምፖች ወጥተው ወደ ታይላንድ ለሚገቡ ውጭ ሀገር ዜጎች መጠለያ እንደማይዘጋጅ ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop