ከአልጀሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኒ ኸሊፍ ጋር በተደረገው የኦሊምፒክስ የቦክስ ፍልሚያ በ46 ሰኮንዶች ውስጥ አቋርጣ የወጣችው ጣሊያናዊቷ አንጄላ ካሪኒ ተፋላሚዋን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ አለች።
ቦክሰኛዋ ኢማኒ ኸሊፍ በሰውነቷ ካለው የሆርሞን [የወንዶች የሚባለው የቴስቴስትሮን ሆርሞን] መጠን ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የሴቶች የዓለም ሻምፒዮና የውድድር ብቃት መመዘኛዎችን ባለማሟላቷ ምክንያት እንዳትሳተፍ ከተደረጉት ሁለት ሴቶች መካከል አንደኛዋ ነበረች።
በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክስ ላይ ግን የሴቶች የቦክስ ውድድር ተሳታፊ ሆናለች።
የ25 ዓመቷ አልጀሪያዊቷ ቦክሰኛ በዚህ ፍልሚያ እንድትሳተፍ መፈቀዱ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አወዛጋቢ ሆኖ ቢታይም፣ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የመወዳደር መብቷን በማስጠበቅ ተከላክሏታል።
“ይህ ሁሉ ውዝግብ ያሳዝነኛል” ስትል በሰኮንዶች ውስጥ ፍልሚያውን ትታ የወጣችው ካሪኒ ለጣሊያኑ ጋዜጣ ዴ ሎ ስፖርት ተናግራለች።
“ለተፋላሚዬም አዝናለሁ። ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ መፋለም ትችላለች ካለ ያንን ውሳኔ አከብራለሁ” ብላለች።
ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ ፍልሚያዋን ማቋረጧ ትክክለኛ እርምጃ እንደነበር ገልጻ፤ ከተፋላሚዋ ኢማኒ ጋር እጅ ባለመጨባበጧ እንደተጸጸተች ገልጻለች።
“እንዲህ ለማድረግ አላሰብኩም ነበር። እሷንም ሆኖ ሁሉንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። የኦሊምፒክ ውድድሬ በባዶ ስለቀረ ተበሳጭቼ ነበር” ስትል ገልጻለች።
ኢማኒ ጋር ከተገናኙ “እንደምታቅፋትም” ተናግራለች።
ሐሙስ ዕለት ሐምሌ 25 / 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የቦክስ ፍልሚያ ለሰላሳ ሰኮንዶች ፊቷ ላይ ቡጢዎች ያረፉባት ካሪና መሃል ላይ እረፍት በመውሰድ አቁማ ነበር። ለአጭር ጊዜ በውድድሩ ከቀጠለች በኋላ ግን ፍልሚያውን አቁማለች።
“የሕይወት ዘመን ግጥሚያዬ ሊሆን ይችል ነበር፤ ነገር ግን ሕይወቴን ማትረፍ ነበረብኝ” ስትል ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራ ነበር።
ባለፈው ዓመት ምርመራዎቹን ያካሄደው በሩሲያ የሚመራው ዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበር ኢማኒ “በሴቶች ውድድር ላይ ለመሳተፍ በዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት አልቻለችም” ሲል ውድቅ አድርጓት ነበር።
በሴቶች የቦክስ ውድድር ተሳታፊ የሆነችው ኢማኒ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በሴት አትሌትነት እውቅና ሰጥቷታል።
“አልጀሪያዊቷ ቦክሰኛ ሴት ሆና ነው የተወለደችው፣ በሴትነት ተመዘግባለች፣ ሙሉ ሕይወቷን የኖረችው በሴትነት ነው፣ ሴት ቦክሰኛ ናት፣ ሴት ሆና የተመዘገበችበት ፓስፖርት አላት” ሲሉ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ማርክ አዳምስ ተናግረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)