የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዜዳንት የሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ፥ ” በወረራ ” ተይዘዋል ያሏቸውን የትግራይ ክልል ግዛቶችን በሰላም ስምምነቱ መሰረት ነጻ እንዲወጡ እና የአካባቢዎቹ ሰላምና ደህንነት ተረጋግጦ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቄያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ወስደው እንዲሰሩ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መግባባት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውጭ የክልሉ ጸጥታ ኃይል ምንም አይነት የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንዳልተንቀሳቀሱ ከሰላም ስምምነቱ ጋር የሚጣረስ አንድም ነገር ላለመፈጸም በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ጄነራሉ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነቱን ለመገምገም በአፍሪካ ህብረት በተመራው የስትራቴጂክ ግምገማ ወቅት እስካሁን ድረስ ስላልተሰሩ ጉዳዮች ተነስቶ እንደነበር እና እንዲሰራባቸው አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።
ከስትራቴጂክ ግምገማው በኃላም ለውጦች መታየታቸውን አመልክተዋል።
መሰረታዊ ከሚባሉት የስምምነቱ ክፍሎች እና ካልተፈጸሙት አንዱ ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው መመለስ ነው ያሉት ጄነራሉ ” ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የትግራይ ግዛት መከበር አለበት ብለዋል።
” በዚህ ላይ ‘ እንደ ራያና ጸለምቲ ቀላል ነው ፤ ምዕራብ ትግራይ ነው ከባዱ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሁሉም ቀላል ነው ሁሉም ከባድ ነው ‘ እየተባለ ምክንያት ይቀርባል። አንዳንዴ ደግሞ ‘ አከራካሪ ቦታዎች ‘ እያሉ ይገልጹታል ሆኖም በህገ መንግሥቱ መሰረት ትግራይ ትግራይ ነው አከራካሪ የሚባል ነገር የለም ጥያቄ ካለ እንኳን በህግ አግባብ ነው መተግበር ያለበት ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ‘ በኃይል ይዣለሁ ፣ ይዣለሁ ማለቱ ፍጹም ሰላም አያመጣም ” ሲሉ አክለዋል።
ጄነራሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሮች ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ መልኩ እንዲፈቱ እንደሚፈልግ ገልጸው ” ለዚህም የመከላከያ ሰራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ኃላፊነት ወስደው እንዲሰሩ እየተደረገ ያለው ” ብለዋል።
” በወረራ ተይዟል ” ባሉት የትግራይ ክፍል ሁሉም ነገር ያለ አግባብ መቀየሩን አስታውሰው ” ሁሉም ፈርሶ ወደነበረበት የትግራይ ቅርጽ እንዲመለስ ፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ የጸጥታ ኃይል ስምምነቱን የሚያፈርሱ ተግባራት ላለመፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ ነው ብለዋል።
” በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎችም ፦
– በራያ አላማጣ፣
– በኦፍላና ፣
– በኮረም ላይ ትኩረት አድርገው የሚናፈሱት ወሬዎች ከእውነት የራቁ ናቸው። እነሱ እንደሚሉት በኃይል መያዝ የምንፈልገው አካባቢ የለም። በስምምነቱ መሰረት በፌዴራል መንግሥት ጥረት ነጻ እንዲሆንልን ነው የምንፈልገው ” ሲሉ ገልጸዋል።
” ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥና ዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነትን የማይቀሰቅስ ተግባር እንዲፈጸም ነው የምንፈልገው በእርግጥ ችግሩን በሰላም ለመፍታት በነበረው ሂደት አለመግባባትና ፍጥጫ ነበር ይህ ለራሳቸው ሆነ ለሀገራችን ስለማይጠቅም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የሰላም ተባባሪ እንዲሆኑ እንጥራለን ” ብለዋል።
ዛሬ የአማራ ክልል መንግሥት በሰጠው ይፋዊ መግለጫ፤ ” ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል ” ሲል ከሷል።
እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል መንግሥት የሰጠው አስተያየት የለም።
ምንጭ፡-(@tikvahethiopia)