የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር
ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሐሙስ ኅዳር 20/2016 ዓ.ም. አገሪቱ ከኢትዮጵያ አንጻር የምትከተለውን ፖሊሲ በተመለከተ ምስክርነት የመስማት እና ማብራሪያ የተጠየቀበት ስብሰባ ተካሂዷል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እንዲሁም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጀት ዩኤስኤአይዲ አስተዳዳሪ ታይለር ቤክልማን ቀርበው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት ምስክርነት ሰጥተዋል።
ሐመር በዋናነት በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ስላሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከአገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንጻር እንዲሁም ቤክልማን አሜሪካ በኢትዮጵያ ስለምታካሂደው የሰብአዊ እርዳታ ምስክርነት እና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ማይክ ሐማር በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ስላጋጠሙ ግጭቶች አንስተው የአሜሪካ መንግሥት ያደረገውን ጥረት እና እያከናወነ ያለውን ተግባር አብራርተዋል።
ልዩ መልዕክተኛው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሲያደራድሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በአማራ ክልልም ዕድሉ ከተሰጠ ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን አመልክዋል።
ማይክ ሐመር በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆን እና መንግሥት ልዩነቶቹን በንግግር እንዲፈታ አሜሪካ ግልጽ አቋሟን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቋን ጨምረው ተናግረዋል።
ማይክ ሐመረ በተለይ በኢተዮጵያ ውስጥ ስላሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች በምክር ቤቱ ከታደሙ ሰዎች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ዋናዎቹን እነሆ. . .
የኮሚቴ ቤት አባላት ጥያቄ
የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጆን ጄምስ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያን መንግሥት አስተዳደርን ተችተዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን እና የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፈተሽ በተጠራው ስብሰባ ላይ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ እና አሁን እየሆኑ ያሉ ጉዳዮችን በማንሳት ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን አውስተዋል።
ጆን ጄምስ፤ “ስለ [ኢትዮጵያ] ብዙ ባወቅኩ መጠን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው እየተረዳሁ ነው። ብቸኛው [የኢትዮጵያ መንግሥት] ፍላጎት በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ የሚፈልገው እየተባባሰ ለመጣውን የምጣኔ ሃብት ችግር መፍሄ ማግኘት ነው” ብለዋል።
ከሚሺጋን ግዛት የተወከሉት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባሉ ጆን ጄምስ፤ የትግራዩ ጦርነት ያስከተለውን ጥፋት፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት መቀጠሉን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎትን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው አስተያየት ተጨማሪ የጦርነት ስጋት ይፈጥራል ወይ ሲሉ ለማይክ ሐመር ጥያቄ አቅርበዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት
ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከኮሚቴ አባላት ንግግር እና ጥያቄ በኋላ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊስ እና አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት አብራርተዋል።
የባይደን እና የሐሪስ አስተዳደር ለመላ ኢትዮጵያውያን ጥቅም ሲባል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲየዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እና ልማት እንዲኖር ፍላጎት አለው ያሉት ማይክ ሐመር፤ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ማስቆም እንዲሁም ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዙ ውጥረቶችን ማርገብ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት አብቅቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ካደረጉ በኋላ በጦርነቱ ለተፈጸሙ የበስዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት ማረጋገጥ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ቁልፍ ጉዳይ እንደሚሆን ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በትግራዩ ጦርነት በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን የፈጸሙት ላይ ክስ እንዲመሠረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደርን ነው ብለዋል።
ምስክርነቱ የተሰማበት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው ስብሰባ
ማይክ ሐመር በትግራይ በከፍተኛ ደረጃ ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀነሳቸው ሪፖርት እንደደራሳቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የኤርትራ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ድንበር ለቅቀው አለመውጣታቸው፣ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የማሰናበቱ ሂደት እየተጓተተ የጠቀሱት ሐመር ቀርተዋል ያሏቸውን ሂደቶችን አንስተዋል።
ጨምረውም በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ መፍትሄ አለማግኘቱን በማስታወስ ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥቱ የተፈራረሙት ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ማይክ ሐመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሥራ በመጀሩበት ወቀት ወደ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አቅንተው የቱርክ መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ ጦር መስጠቱ አሜሪካን እንዳሳሰባት እና ድሮኖቹ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ የበለጠ እያወሳሰበ መሆኑን ስጋታቸውን መግለጻቸውን አመልክተዋል።
ኦሮሚያ እና አማራ
የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት መፈረሙ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ሐመር፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም ንግግር እና ድርድር እንዲደረግ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛው አገራቸው አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች እጅጉን እንደሚያሳስባት ለኮሚቴ አባላት ተናግረዋል።
በሁለቱ ክልሎች የሕይወት መጥፋት፣ የመብት ጥሰት እና የምጣኔ ሃብት ውድመት አለ ያሉት ማይክ ሐመር፤ ሁሉም አካላት ከግጭት እንዲቆጠቡ አሜሪካ ስታሳስብ ቆይታለች ብለዋል።
በዚህም “ተዋጊዎችን ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ለማደራደር ጥያቄ አቅርበናል” በማለት ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የኢትዮጵያ መንግሥታትን በታንዛኒያ ሲያደራድሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በታንዛኒያው ድርድር ለግጭቱ ወታደራዊ አማራጭ መፍትሄ እንደማይሆን በመጠቀሰ የአሜሪካ መንግሥት ለወራት ውትወታ ካደረገ በኋላ ሁለቱ ወገኖቸ ለንግግር አንደተቀመጡ አና የሚፈለገው ውጤት እስኪመጣ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
“የምንፈልገውን አይነት ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት ከባድ ነው። ንግግሩ ከባድ ነበር። በዳሬሰላም ለሁለት ሳምንት ተኩል ቆይቻለሁ። አዎንታዊ ለውጦች ግን አሉ። ሰላማዊ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ቁርጠኞች ነን።”
ለዚህም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እና ሰጥቶ የመቀበል ውሳኔ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከተባባሰ ወራት ያሰቆጠረውን በአማራ ክልል እየተካሄደ የለውን ግጭትም ለማስቆም “ዕድሉ ካለ ለማደራደር እና ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ያሉት ማይክ ሐመር ግጭቶቹ በወታደራዊ እርምጃ እልባት ሊያገኙ እንደማይችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ከወራት በፊት በፌደራሉ መንግሥት በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ እና መገናኛ ብዙኃን ወደ ክልሉ እንዲደርሱ እንዲሁም ተቋርጦ የሚገኘው የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥትን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
“በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚፈጸሙት ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች፣ ስቃዮች እና እስሮች በእጅጉ አሳስበውናል” ያሉት ሐመር፤ “ይህን ለመንግሥት ግልጽ አድርገናል። …በእያንዳንዱ ንግግራችን የሰብዓዊ መብት መከበር የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዋና አካል መሆኑን ግልጽ አድርገናል።”
በአገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ደስተኛ አይደለንም ያሉት ማይክ ሐመር ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደረገው ንግግር ይቀጥላል ብለዋል።
ምጣኔ ሃብት
ልዩ መልዕክተኛው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሚባል የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ መግባቷን ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ወቅት አንስተዋል።
“የውጭ ምንዛሬ ክምችት በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ በአማካይ 30 በመቶ ነው” ያሉ ሲሆን፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በተመለከተ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሆና ከቆየችበት የአፍሪካ የእድገት እና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) መታገዷ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ጦርነቱን ለማቆም የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዳግም ከአጎዋ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል እየተጠና መሆኑን ሐመር ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ለአጎዋ ብቁ ስለመሆኗ ዳግም እየተጠና ነው። በሳምንታት ውስጥ ውሳኔ ያገኛል። …ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የቀጠለው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ነው። በተለይ ደግሞ በአማራ እና በኦሮሚያ። …በአጎዋ መስፍርቶች መሠረት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቀድመው መሻሻል አለባቸው” ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ እና የባሕር በር ጉዳይ
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እንዲሁም የተቀሩት የታችኛው የተፋሰስ አገራትን በሙሉ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምንት እንዲደረስ አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል ሐመር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ብለው መናገራቸው በቀጠናው ካሉ አገራት አልፎ ለአሜሪካ የስጋት ምንጭ እንደሆነ ማይክ ሐመር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ፍላጎቱ በኃይል ተፈጻሚ እንደማይሆን በይፋ እንዲሁም በግል ማረጋገጫ እንደሰጧቸው አመልክተዋል።
“ይህ ቀጠና በፍጹም የማይፈልገው ነገር ሌላ ጦርነት ነው። …በቀጠናውም ሆነ በኢትዮጵያ ግጭት እና አለመግባባት በሰላማዊ ንግግር ነው መፈታት ያለበት።”