27 ህዳር 2023
ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ቬርሞንት ግዛት ሶስት ፍልስጤማዊ ተማሪዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን መሰረት አድርጎ ምርመራ እንዲያደርግ ቤተሰቦቻቸው ጠይቀዋል። ሂሳም አዋርታኒ፣ ታሃሲን አህመድና ኪናን አብዱልአህሚድ የተባሉት ተማሪዎች ከቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ከአንድ ግለሰብ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ በኋላ ተኩስ እንደከፈተባቸው ፖሊስ ገልጿል። ፖሊስ ተጠርጣሪውን እየፈለገ ሲሆን ተማሪዎቹ ላይ ለምን ጥቃተት እንደከፈተ ምርመራ እያደረገ ነው። ተማሪዎቹ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ወቅት ኬፊያ የተባለውን እና በአረብ ባህል አንገት ወይም ጭንቅላት ላይ የሚደረገውን ዥንጉርጉር ስካርፍ መሳይ ለብሰው ነበር። ሁለቱ ተማሪዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የበርሊንግተን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ጆን ሙራ የገለጹ ሲሆን አንደኛው ተማሪ ግን የከፋ ጉዳት እንደደረሰበት ጠቁመዋል። ኪናን አብዱልአህሚድ በሃርቫርድ ኮሌጅ ውስጥ ተማሪ ነበር። የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ የብራውን ዩነቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሆኑ ተመላክተዋል። ከተጎጂዎቹ የአንዱ አጎት የሆነው ሪች ፕራይስ፣ ሶስቱም ተማሪዎች በ20 ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው ከጥቃቱ በፊት በእርሱ ቤት ውስጥ የልደት ድግስ እንደታደሙ ተናግሯል።“ቤታችንን ለቀው ከወጡ ከ5 ደቂቃ ከልበለጠ ጊዜ በኋላ በበራችን በኩል የሚያልፍ ድምጽ የሚያሰማና መብራቱ ብልጭ ድርግም የሚል የፖሊስ መኪና አየን። የሆነ ችግር እንደተፈጠረ ገባን። ዘመዴና ጎደኞቹ እንደሆኑ ግን የምናውቀው ነገር አልነበረም” ብሏል። ቤተሰቦቻቸው ቀደም ብሎ የፍልስጤም ደጋፊ በሆነ አንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አማካኝነት መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫቸዋውም “የህግ አስከባሪ አካላት፣ የተሟላ ምርመራ እንዲያደርጉና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ወንጀል አድርገው እንዲወስዱት እንጠይቃለን። ተኳሹ ለፍትህ እስኪቀርብ ድረስ ሰላም አይሰማንም” ብለዋል። የአሜሪካ የኢስላም ምክር ቤት ጥቃት አድራሹን ለመያዝ የሚያስችል መረጃ ለጠቆመ 10 ሺህ ዶላር እንደሚሸልም ቃል ገብቷል። ከሁለት ወራት በፊት የእስራኤልና ሀማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአሜሪካ ሙስሊም ጠልና ጸረ ሴማዊነት ክስተቶች ተባብሰዋል። አካላዊ ጥቃት ማድረስን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርን ይጨምራል። ቀድሞ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት እጩ ቀርበው የነበሩት የቬርሞናንት የምክር ቤት አባሉ በርኒ ሳንደርስ ጥቃቱን አውግዘዋል። በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ሶስት ፍልስጤማውያን እዚህ በርሊንገተን ቬርሞንት ውስጥ ለጥቃት መዳረጋቸውእጅግ የሚያስደነግጥ ነው ያሉ ሲሆን “ጥላቻ እዚህ ወይም ሌላ የትም ስፍራ ቦታ የለውም” ብለዋል። በዩኬ የፍልስጤም ተልዕኮ አምባሳደር የሆኑት ሁሴን ዞምሎት በማህበራዊ ድረ ገጻቸው የሶስቱን ተማሪዎች ፎቶ “ፍልስጤማውያን ላይ በጥላቻ የሚደረግ ወንጀል ሊቆም ይገባል” ብለዋል።