በአስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 6፤ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ዓመታት አቋርጦት የነበረውን የቪዛ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ኤምባሲው አስታወቀ።
ነገር ግን በኢሚግሬሽን እና ዜግነት ህጉ ክፍል 243(መ) ስር ባሉት ኦፊሴላዊ የኤርትራ ዜጎች ላይ ያለው የቪዛ እገዳ ባለበት እንደሚቀጥል አስመራ የሚገኘው ኤምባሲው በድረ ገጹ ባወጣው ማስታወቂያ ገልጿል።
የቪዛ እገዳው ከዋና ዳይሬክተርነት ማዕረግ በላይ ላሉ የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት፣ በገዢው ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ፍትህ (ህግደፍ) ውስጥ በአመራርነት ላይ ያሉ የፓርቲ ኃላፊዎችን ይመለከታል።
በተጨማሪም እነዚህ የመንግሥት እና የፓርቲ ኃላፊዎች በትዳር አጋሮቻቸው እና ከ21 ዓመት በታች ባሉ ልጆቻቸው ላይ እገዳው ተፈጻሚ ይሆናል።
ከእነዚህ ግለሰቦች ውጭ የሆኑ ኤርትራውያን እና በኤርትራ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች የቪዛ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ የኤምባሲው ማስታወቂያ ላይ ተጠቅሷል።
የኤሜሪካ መንግሥት ከሶስት ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳቢያ በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የአሜሪካ የግምጃ ቤት የኤርትራ መከላከያ ኃይል ዋና ኢታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሃንስን በጥቁር መዝገብ ውስጥ ማስገባቱን ገልጾ ነበር።
በኋላም በኤርትራ ብሔራዊ ደህንነት ኃላፊ ብ/ጀኔራል አብርሃ ካሳ ማርያም እና በህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲ እና ፍትህ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሃጎስ ገብረህወት ላይ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ይታወሳል።
ኤርትራ በባለስልጣኖቿ ለተጣለባት ማዕቀብ በሰጠችው ምላሽ የአሜሪካ “ህገ ወጥ” ድርጊት እንዳሳዘናት ገልጻ’ “መሰረተ ቢስ ውንጀላ ተጨባጭነት የሌለው እና የስም ማጥፋት” ስትል ውድቅ አድርጋዋለች።
በኤርትራ እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት በአጠቃላይ በኤርትራ ነጻነት የመጀመሪያዎቹ አመታት ወቅት አዎንታዊ ነበር። ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ጀምሯል።
የኤርትራን የሰብዓዊ መብት አያያያዝ፣ አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት እና የፖለቲካ ጭቆና አጥብቃ የምትተቸው አሜሪካ፤ “በቀጠናው ግጭት ውስጥ ላላቸው ተሳትፎ እና ጽንፈኛ ቡድኖችን ደግፈዋል” በሚል በሀገሪቱ እና በባለስልጣኖቿ ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች።
ማዕቀቦቹ የጦር መሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ አድርጓል።
የኤርትራ መንግሥት አልሸባብን እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን ይህም ከአስር ዓመት ቆይታ በኋላ ከአራት አመት በፊት መነሳቱ ይታወሳል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ቃለመጠይቆች ኤርትራን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ሰለባ አድርጓል በሚል በአሜሪካ የሚመራውን የምዕራባውያን ፖሊሲ በተደጋጋሚ አውግዘዋል።
የኤርትራ መንግሥት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና ቢል ክሊንተን አስተዳዳሮች የተከተሉትን “የተሳሳቱ ፖሊሲዎች” በማለት ሲተች ቆይቷል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አሉታዊ ያሏቸውን ፖሊሲዎች ለማረም ከአስተዳደራቸው ጋር “በንቃት በመምከር” እና ችግሮቹን እና መፍትሄዎቻቸውን የሚገልጽ “አጠቃላይ ሰነድ” አስረክበዋል ሲል የሚያዝያ 2021ዱ የአሜሪካ መግለጫ ያትታል።
ሆኖም ግንኙነቱ በሚጠበቀው ደረጃ አላደገም። በተለይም የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአምባሳደር ደረጃ ወደ አስፈፃሚ ጉዳዮች (ቻር ዲ ኤፌፌርስ) ከተቀነሰ በኋላ ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው።
በኤርትራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኤርትራውያን እና በአሜሪካ ለቋሚ ነዋሪዎች የሚሰጠውን የቪዛ አገልግሎት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 13፤ 2017 አቋርጧል።
ብዙ ኤርትራውያን የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ለመጓዝ ይገደዱ ነበር።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/