የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች መካከል ተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊያደርግ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ለሚተገብረው የሠራተኞች ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ለፈተና እንደሚቀመጡ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ለቢቢሲ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ባለፉት ሳምንታት ከሠራተኞቹ ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።
163 ሺህ ገደማ ሠራተኞች በስሩ ያሉት የከተማ አስተዳደሩ፤ በሚተገበረው ለውጥ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የከተማዋን የመንግሥት ሠራተኞችን በአዲስ መልኩ መደልደል የሚለው ይገኝበታል።
ቢቢሲ የተመለከተው ለለውጡ ትግበራ የተዘጋጀ የሥልጠና ሰነድ እንደሚያመለክተው በመጀመሪያው ዙር ይህ ድልድል እንዲተገበርባቸው የተመረጡት የከተማ አስተዳደሩ 16 ተቋማት ናቸው።
ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር፣ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ትራንስፖርት፣ ፐብሊክ ሰርቨሲ እና ሰው ሀብት ልማት፣ ፕላን እና ልማት፣ ሥራ እና ክህሎት፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች ይገኙበታል።
ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የከተማይቱ ኤጀንሲዎች እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ድልድሉ ከሚተገበርባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተካትተዋል።
እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ድልድል የሚደረግባቸው በማዕከል ቢሮዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ላይ ባሉ ጽህፈት ቤቶቻቸው ጭምር ነው።
እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ለመጀመሪያው ዙር ትግበራ የተመረጡት “ብዙ ተገልጋይ የሚያስተናግዱ እንዲሁም ብልሹ አሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ መጓደል ያለባቸው” በመሆናቸው እንደሆነ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያስረዳው አዲሱ የሠራተኞች ድልድል ከመከናወኑ በፊት የእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች ለፈተና ይቀመጣሉ።
የቢሮ ኃላፊው፤ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ፈተና ለመስጠት ያቀደው የሠራተኞቹን “የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ፈተናው የባህሪ እና የቴክኒክ ምዘናዎች እንደያዘ የገለጹት ዶ/ር ጣሰው፤ “የሚሰጠው የቴክኒክ ምዘና [ሠራተኞቹ] ከሚሠሩት ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። የባህሪው [ፈተና] ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡን የሚፈታተኑ የባህሪ ችግሮች ስላሉ ያንን ክፍተት ለመሙላት አመላካች እንዲሆን ተስቦ የተዘጋጀ ነው” ሲሉ የፈተናውን ይዘት አብራርተዋል።
ኃላፊው፤ ምዘናው በአዲስ አበባ እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ መዘጋጀቱን የገለጹ ሲሆን፣ ፈተናው የሚሰጠውም በዩኒቨርስቲ ወይም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል። እስካሁን ባለው መረጃም ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ፈተናውን የሚወስዱ ሠራተኞች ቁጥር ከ14 ሺህ በላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“[ፈተናውን] የማያልፉ [ሠራተኞች] እንዳይኖሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ እንዲያጠኑ ተነግሯል። ፈተናው ለማለፍ በሚያስቸግር መንገድ በጣም የተወሳሰበ፣ አብስትራክት እና ንድፈ ሀሳባዊ የሆነ ሳይሆን [የሠራተኞችን አቅም ለመለካት] አመላካች ሆኖ ነው የተዘጋጀው። ብዙዎቹ ሊያልፉ ይችላል የሚል ግምት ነው የተያዘው” ሲሉም የሚጠበቀውን ውጤት ገልጸዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው የሪፎርም ሥልጠና ሰነድ እንደሚያስረዳው የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ፈተናውን ለማለፍ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። “ከዚህ [የማለፊያ ውጤት] በታች [የሆነ] ነጥብ ያገኘ ባለሙያ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ባሉት የአስተዳደር እርከኖች” ላይ እንደሚመደብ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች የተቀመጠው የፈተና ማለፊያ ነጥብ ደግሞ 60 በመቶ ሲሆን፤ ይህንን ነጥብ የማያስመዘግቡ አመራሮች ለዳይሬክተርነት ወይም ለቡድን መሪነት ኃላፊነት መወዳደር እንደማይችሉ ሰነዱ አስቀምጧል።
የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው፤ “[ሠራተኞች ፈተናውን] የማያልፉ ከሆነ ዝቅ ተደርገውም ሊመደቡ ይችላሉ። ድልድሉ ካለቀ በኋላ ሌሎች አማራጮችም ታይተው ምን ሊደረግ እንደሚችል የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ መፍትሄ ይፈለግላቸዋል” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ መልኩ ሠራተኞቹን ሲደለድል ከፈተናም በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችን እንደሚጠቀም ዶ/ር ጣሰው ገልጸዋል። የሥልጠና ሰነዱ የሠራተኞች ድልድልን በተመለከተ “ትኩረት የሚሹ አዳዲስ ጉዳዮች” በሚል ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ጉዳይ ነው።
ድልድሉ ሲከናወን “ሕብረ ብሔራዊነት እና አካታችነት በጥንቃቄ” መተግበር እንዳለበት በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። “አካታችነት እና ፍትሐዊነትን” በሚመለከተው የሰነዱ ክፍል ላይ በዳይሬክተርነት እና ቡድን መሪነት የሥራ መደቦች ላይ አመራሮች ሲመደቡ “የሜሪት ሥርዓት” እንደሚጠበቅ ያስረዳል።
ይሁንና ይህ የአመራሮች ድልድል “የብሔር ብሔረሰብ ስብጥርን ባካተተ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ” እንደሚከናወን ይገልጻል። ሰነዱ አክሎም፤ “በመሥሪያ ቤቱ ካሉ የሥራ መደቦች [መካከል] በተመሳሳይ ማንነት የተያዙት ከ40 በመቶ መብለጥ የለባቸውም” ሲል ይህንን ድልድል በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ባጸደቀው ደንብ ላይ የተቀመጠውን አሰራር ያስረዳል።
መሥሪያ ቤቶቹ ድልድሉን ሲያከናውኑ ይህንንን የብሔር ስብጥሩን ለመጠበቅ እንዲችሉ “ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች በመለየት በዝውውር እንዲሟሉ” እንደሚደረግም በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው ግን “ከ40 በመቶ መብለጥ የለበትም” በሚል የተቀመጠው አሠራር፤ የሚተገበረው የቡድን መሪዎች እና ዳይሬክተሮች ድልድል ላይ ብቻ እንደሚሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዚህ ድልድል ወደ ሠራተኛ የወረደ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። የድልድል ደንቡ ውስጥም የለም። የተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ከተወሰነ ፐርሰንት በላይ መሆን የለበትም የሚለው ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ዶ/ር ጣሰው፤ “ከተማዋ የአገሪቱ ዋና ከተማ ናት። ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያሉባት ስለሆነች ያንን ሥዕል የሚያሳይ እንዲሆን መደረግ ስላለበት የተቀመጠ ነገር ነው” ሲሉም ይህ አሠራር ተግባራዊ የሚደረግበትን ምክንያት ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚተገብረው ይህ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም እና የሠራተኞች ድልድል እስከ ታኅሣሥ 25/2016 ዓ.ም. ድረስ ለማጠናቀቅ በጊዜያዊነት ዕቅድ መያዙን የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በማዕከል መሥሪያ ቤቶች ያሉ ሠራተኞችን ወደ ወረዳዎች ለማሰራጨት ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ኅዳር ወር ነው።
ካቢኔው በወቅቱ፤ “በማዕከል ደረጃ የሚታየውን የሠራተኛ ክምችት ከተማዋ ከምታመነጨው ገቢ እና ለሕብረተሰብ ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር የማይመጣጠን [ነው]” ሲል በወቅቱ ለውሳኔው መነሻ የሆነው ምክንያት ገልጾ ነበር። የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች “ከፍተኛ የሥራ ጫና ወዳለባቸው ወረዳ እና ተቋማት” የሚበተኑት “ሙያዊ እና ተፈላጊ ችሎታቸውን” ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም የከተማዋ የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቆ ነበር።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn
ምንጭ(ቢቢሲ)