ኸዲጃ እና ሪሐና እህትማማቾች ናቸው። ሁለቱም በተለያየ ምክንያት፣ በተለያዩ ቀናት ሐኪም ጎብኝተው ሁለቱም የቫይታሚን-ዲ እጥረት አላባችሁት ተባሉ።
በሥራ ቦታ የሚያውቋቸው ሌሎች በርካታ ሰዎችም እንዲያ መባላቸውን ስለሚያውቁ ተገረሙ።
ኸዲጃ እና ሪሐና በሳምንት ዐርብ ከጁምዓ ስግደት በኋላ የቤተሰብ ፕሮግራም አላቸው። እየተገናኙ ይበላሉ፤ ይጨወታሉ።
በዚህ የቤተሰብ ጉባኤ የቫይቲምን-ዲ ነገር እንደ ዋዛ ተነሳ። “አለብሽ ተባልኩ” የሚለውን ተከትሎ “እኔም-እኔም-እኔም” መባባል ሆነ።
“ከተሰበሰብነው ውስጥ ግማሻችን ቫይታሚን-ዲ አለባችሁ ተብለናል። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ትላለች ሪሐና።
“የእኛን አገር ሐኪሞች ብዙ አላምናቸውም። ድሮ ታይፎይድ አለባችሁ ይሉን ነበር፤ አሁን ደግሞ ቫይታሚን-ዲ እጥረት አለባችሁ ማለትን ፋሽን አድርገውታል” ትላለች ታላቅ እህቷ ኸዲጃ።
የጤና ባለሙያዎች ግን ነገሩ ወዲህ ነው ይላሉ።

“የአዲስ አበባ ሕዝብ 75% እጥረት አለበት”
ዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተባብሮ የሠራው ጥናት ውጤት አስደንጋጭ ነው።
ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹ እጥረት አለበት። ከአዲስ አበባ ሕዝብ ደግሞ ሦስት አራተኛው (¾) ቫይታሚን-ዲ አጥሮታል። ይህ ነገር ከኑሮ ውድነቱ ጋር የተያያዘ ይሆን?
አይደለም።
ይህ አሐዝ በተለይ 13 ወር ፀሐይ ለሚጠጣ ሕዝብ ስላቅ ይመስላል።ምክንያቱም የቫይታሚን-ዲ ዋና አከፋፋይ ፀሐይ ስለሆነች።
ዶክተር ፍጹም ጥላሁን በአሜሪካን አገር በሕክምና ሙያ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ።
ውስብስብ የሕክምና መረጃዎችን በሕዝብ ቋንቋ አውርዶ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ በመፍጠር ብዙ ሥራ በመሥራት ይታወቃሉ።
‘ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐኪም ቤት የሄደ አዲስ አበቤ ሁሉ ቫይታሚን-ዲ እጥረት አለብህ የሚባለው ለምንድነው?’ ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተውናል።

የፎቶው ባለመብት,Getty Images
“አኗኗራችን ተለውጧል- ምርመራው ዘምኗል”
የሕክምና ባለሙያዎች የኑሮ ዘይቤያችን መቀየሩን አብዝተው ያወሳሉ።ከኮምፒውተር መምጣት ወዲህ እየጎበጥን ነው፤ ከዘመናይ ስልክ ወዲህ እየፈጠጥን ነው።
ይህ ነገር ጣጣ ይዞብን እየመጣ ነው። አያት ቅድመ አያቶቻችን ንቁ ነበሩ። የእኛ አኗኗር ፍዝ ሆኗል።የጤና ጣጣ ይዞብን ይመጣል።
ብዙ ሰው ጠዋት ተንደርድሮ ቢሮ ይገባል።ምሳ እዚያው ክበብ ውስጥ ይበላል። ሲመሽ ወደ ቤት ይነጉዳል።
ታዲያ ከፀሐይ ጋር በየት ይገናኛል? አኗኗራችን ተቀይሯል።
ተማሪ ትምህርት ቤት ይውላል፣ ካድሬ ቀኑን ሙሉ ስብሰባ ነው። ነጋዴው ሱቁ ቆሞ ይሸጣል። ከፀሐይ ጋር በየት በኩል ይገናኛል?
ለመሆኑ አዲስ አበቤ በሺህ በመቶ ሺዎች ለቫይታሚን ዲ የተጋለጠው ለዚህ ይሆን?
ዶክተር ፍጹም አንድ ቁልፍ ምክንያት ያነሳሉ።
“በፊት ምርመራ አልነበረም። ስለዚህ ቫይታሚን-ዲ እጥረት እምብዛምም አይታወቅም ነበር ።አሁን ብዙ ሰው ለአጠቃላይ ጤና ምርመራ ሲሄድ እጥረት እንዳለበት ይነገረዋል . . . ።”

የፎቶው ባለመብት,Getty Images
ኖርዌይ እና አዲስ አበባ
ኦስሎ ፀሐይ ብርቅ ናት።
አዲስ አበባ ፀሐይ መከራ ናት።
ብዙ አዲስ አበቤ ፀሐይን እንደ ደመኛ ነው የሚያያት። ታነጫንጫለች። መልስ ስጠኝ ከሚል የታክሲ ጭቅጭቅ ቀጥሎ ብዙ ሰው የሚነጫነጨው በፀሐይ ንዳድ ይመስላል።
በአንጻሩ የስካንዲኒቪያን ሰዎች መሳቅ የሚጀምሩት ፀሐይ ስትወጣ ነው። እዚያ ብልጭ ብላ ትሰወራለች። ለጥቂት ወራት ብቻ።
ሆኖም ከኦስሎ ሕዝብ ይልቅ የአዲስ አበባ ሕዝብ በብዙ እጥፍ በቫይታሚን-ዲ እጥረት ይሰቃያል።
እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል? 13 ወር ሙሉ ፀሐይ እየወጣች?
ዶክተር ፍፁም ”ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው” ብለው ይንደረደራሉ።
“ይህ የሆነው በሜላኒን ምክንያት ነው” ይላሉ።
ምንድነው ደግሞ ሜላኒን?
እኛ አፍሪካውያን እና ባለ ጥቁር ቆዳ ሕዝቦች ሜላኒን አለን።ፈረንጆቹ ግን የላቸውም።
ሜላኒን የተፈጥሮ ጥላ ነው። የቆዳ ዣንጥላ ማለት ነው።ለቆዳችን “የጨረር ባለሥልጣን” ሆኖ ያገለግላል።
በዚህ የተነሳ “ቫይታሚን-ዲ በቀላሉ ማምረት የሚችሉት በተለምዶ ፈረንጅ የምንላቸው ሰዎች ናቸው። ቆዳቸው ነጣ ያሉ ሰዎች።”
ጥቁር ቆዳ ግን ‘ማገዶ ይፈጃል’። ፀሐይ በቀላሉ አይዘልቀውም።
ፈረንጆች ላይ ግን አልትራቫዮሌት ሰውነታቸው ላይ ሲያርፍ በቀላሉ ቆዳቸውን ሰርጎ ይገባል።
በሌላ አነጋገር ቫይታሚን ዲ ሰርጾ እንዳይገባ ይሄ ሜላኒን ደንቃራ ሆኖ ይቆማል።
ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
ቫይታሚን-ዲ የማምረት አቅማችን አናሳ ነው ማለት ነው።
ዶክተር ፍጹም፣ “ይህ ማለት ግን ሜላኒን አያስፈልገንም ማለት እንዳልሆነ ልብ እንድንል አበክረው ያሳስቡናል።
ከቆዳ ካንሰር የሚጠብቀን ማን ሆነና።

የፎቶው ባለመብት,Getty Images
“ዓሣ ማን አቅምሶን?!”
የሥነ ምግብ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ይሁኔ አየለ በበኩላቸው ፀሐይ ብርቅ በሆነችበት በስካንዲኒቪያን የቫይታሚን እጥረት የሌለው በምክንያት ነው ይላሉ።
“የእነርሱ ዋና ምግባቸው ዓሣ ነው።ዓሣ ደግሞ በቫይታሚን-ዲ የበለጸገ ነው።”
ዓሣ ብላ ብሎ መምከር ለብዙ የአዲስ አበባ ሰው በቁስል ላይ እንጨት መስደድ ነው።
ምክንያቱም ዓሣ የሃብታም ምግብ ነው።
”ዓሣ ቤት” ብዙ ሰው ምግቡን ደጋግሞ ፎቶ የሚያነሳው ለምን ሆነና።
ምን ተሻለ?
በዚህም በዚያም የአዲስ አበባ ሕዝብ ከቫይታሚን-ዲ እጥረት ማምለጥ አልቻለም፤ በዋናነት በሁለት ምክንያት።
አንደኛ፣ ከፀሐይ ንዳድ ሸሽቶ ቫይታሚን ዲ ያጥረዋል፣ ዓሣ ለመብላት ደግሞ ገንዘብ ያጥረዋል።
ምናልባት ለዚህ ይሆን 75 በመቶ የአዲስ አበባ ሕዝብ በቫይታሚን-ዲ እጥረት የሚሰቃየው?
ዶክተር ፍጹም ለዚህ አስደንጋጭ አሐዝ ሦስተኛ መላምት አላቸው።
የከተማው አየር በጭስ ታፍኗል፤ ከመኪና እና ከፋብሪካ በሚወጣ ጭስ (Smog) ከባቢ አየሩ ላይ ተሰግስጎ የፀሐይ ጨረርን እየገፋው ነው።
ይሄ ክፉ ጭስ ከተማዋን እንደ ብርድ ልብስ ይጋርዳታል። ይሄ ማለት ፀሐይ ቢነካንም ቀጥታ ጨረሩን አናገኘውም እንደማለት ነው።
የሥነ ምግብ ባለሙያው ዶክተር ይሁኔ ደግሞ ሌላም ምክንያት አለ ይላሉ።
”የምግብ ማበልጸግ ሥርዓት” በእንግሊዝኛ (food fortification) በሌላው ዓለም ይዘወተራል።በእኛ አገር ግን የለም።
ምን ማለት ነው ደግሞ እሱ?
በውጭው ዓለም የቫይታሚን እጥረት እንዳይከሰት ምግቦቻቸው ሆን ብለው ያበለጽጉታል። “ያ ልምድ በኢትዮጵያ አለመኖር ጎድቶናል” ባይ ናቸው፣ ዶክተር ይሁኔ።
ዶክተር ፍጹም፣ ከዶክተር ይሁኔ ሐሳብ ጋር ስምም ናቸው። እየኖሩትም ነው።
“እኔ በምኖርበት አሜሪካ ለምሳሌ ወተት ስትገዛ በቫይታሚን-ዲ የበለጸገ (Vitamin D fortified) የሚል ተጽፎባቸው ታያለህ።”
እጥረት እንደሚያጋጥም ስለሚታወቅ ነው እንዲያ የሚያደርጉት።

ዓሣ ውድ ነው – ፀሐይ ርካሽ ነው
ዋናው የቫይታሚን-ዲ ምንጭ ፀሐይ ናት። እሷን ‘በነጻ እንመገብ’ ይላሉ ባለሙያዎች።
‘ቫይታሚን-ዲ’ን ከብዙ ቫይታሚኖች ልዩ የሚያደርገው ሰውነታችን ራሱ ስለሚሠራው ነው።
ሰውነታችን እሱን ለመሥራት አስፈላጊው ‘ቅመማ ቅመም’ ሁሉ አለው። ከእኛ የሚፈልገው በቂ የፀሐይ ብርሃን ብቻ ነው። ፀሐይ እንደ ዘይት ሆና ታገለግላለች።
ቆዳችን ሥር ስብ መሰል ነገር አለ። ልክ ፀሐይ ሲያገኝ ‘ተቁላልቶ’ ከቆዳችን ወደ ጉበት ይሄዳል። ጉበት ውስጥ ደግሞ ትንሽ ‘በስሎ’ ወደ ወደ ኩላሊት ይወርዳል። በመጨረሻ ቫይታሚን-ዲ ይሆናል።
ሰውነታችን ይህን ቫይታሚን እንዲሠራው ግን በፀሐይ መለኮስ አለበት።ቁልፉ ነጥብ እሱ ነው።
ፀሐይ ሩቅ ከሆነችብን ግን ዓሣ የግድ ነው።እጥረት አለባችሁ የተባሉ ሰዎች ከዓሣ ዝርያዎች ሳመን (Salmon) የሚያህለው የለም። ሰርዲን እና ቱናም መልካም ነው።
የሥነ ምግብ ባለሙያው ዶክተር ይሁኔ በኢትዮጵያ ባሕል በጣም ድንቅ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ”ምግብ ላይ ቂቤ መጨመር” ነው ይላሉ።
”ይሄ ነገር ብዙ ሰው ጉዳት ይመስለዋል፤ኮሌስትሮል ይጨምራል ይላል። ሳናውቀው የጠቀመን የሚመስለኝ ግን ቂቤ ጣል ማድረጋችን ነው” ይላሉ።
ቫይታሚን-ዲ ከአትክልት እና ከእንሰሳት ተዋጽኦ ምግቦች ይገኛል።
ዕንቁላል አስኳሉ ምርጥ ነው። ጉበት ከተገኘ አይከፋም።ከአትክልት ዘር እንጉዳይ ወደር አይገኝላትም።

ሒጃብ እና ዣንጥላ ቫይታሚን ዲ ያጎድላሉ?
“13 ወር ፀሐይ አለ ማለት እኮ ፀሐይ እያገኘን ነው ማለት አይደለም” ይላሉ ዶክተር ፍጹም።
ዛሬ ዛሬ ብዙ ሰዎች በተለይም ሴቶች ዣንጥላ ይይዛሉ፤ ፀሐይ እንዳይመታቸው።ሰን ስክሪን ይቀባሉ፤ ፀሐይ እንዳትጎዳቸው።
ታዲያ አልትራቫዮሌት-ቢ ጨረር እንዴት ያግኛቸው?
ሌላው በሃይማኖትም ወይ በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ተሸፋፍነው የሚውሉ ሰዎች ይበልጥ ለእጥረቱ ይጋጠለጣሉ። ለምሳሌ ቀሳውስት፣ ለምሳሌ ሂጃብ የሚለብሱ ሴቶች፣ ሻሽ ሸብ አድርገው የሚውሉ እናቶች።
ምን ተሻለ?
ዶክተር ፍጹም ይመክራሉ። በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ቀናት ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ሰውነታችንን ለፀሐይ ማጋለጥ በቂ ነው።
በቤታችን ግቢ ውስጥ ሊሆን ይችላል።
ፀሐይን ለማጣጣም ምርጡ ሰዓት ደግሞ ከጠዋት 4፡00 ሰዓት እስከ ቀትር 9፡00 ነው። ብዙ ሰው ያን አለማግኘቱ ነው የጎዳን።
ብዙ አዲስ አበቤ በዚያ ሰዓት ወይ ቢሮ ነው ወይ ቤት ነው፣ ወይ ትምህርት ቤት ነው። ወይ ታክሲ ሰልፍ ላይ ነው፤ ጥላ ይዞ።
ይህ ሊሆን ይችላል የአዲስ አበባን ሰው ይበልጥ የጎዳው።ምርመራ መስፋፋቱ እንዳለ ሆኖ።

የፎቶው ባለመብት,Getty Images
ቫይታሚን ዲ ምን ይሠራልናል? ቢቀርስ?
ካልሺየም የሚባለው እጅግ አስፈላጊ ንጥረ ነገር ወደ ሰውነታችን መግባት የሚችለው ቫይታሚን-ዲ ስናገኝ ነው።
አጥንት ያለ ካልሺየም ጨርቅ ነው። ካርቶን ነው። ይሳሳል-ይፈርሳል።
ቆመን ስንሄድ አይመስልም እንጂ ሸክላ ነን። በቀላሉ እንሰበራለን።ቆመን የምንሄደው በካልሺየም ብርታት ነው።
ሕጻናት በቂ ፀሐይ ካላገኙ እግራቸው ደጋን ይሆናል። እንደዚያው ሆነው ያድጋሉ።መቆም ይደክማቸዋል።
ዶክተር ይሁኔ በተለይ ልጆች ቡዳ እንዳይመታቸው እያሉ መሸፋፈን ይቅር ሲሉ አበክረው ይመክራሉ።
“ቅባት እየቀቡ፣ በጋቢ ጠቅልሎ ፀሐይ ማሞቅም ልክ አይደለም።”
ሽማግሌዎች በደንብ ፀሐይ ካላገኙ ‘ወገቤን’ ማለት ይጀምራሉ።ብዙ ሰው እርጅና ያመጣብኝ ጣጣ ነው ብሎ ይቀመጣል። ልክ አይደለም።
እጥረቱ ያለበት ሰው ሌላም ምልክት ያሳያል።
ቶሎ ቶሎ እንታመማለን። ቶሎ ቶሎ ጉንፋን ይይዘናል። ቶሎ ቶሎ ቶንሲል ያጠቃናል።
ጡንቻችን ይሟሽሻል። ድብርት ይመላለስብናል። የትከሻ እና የክንድ መዛል ይኖራል።
ብዙ ሰዎች መድኃኒት ወስጄም አልተሻለኝም ይላሉ። ዶክተር ፍጹም ለዚህ ምላሽ አላቸው።
“አንቲ ባዮቲክስ አይደለም። መድኃኒት ስለወሰድን ወዲያው አይሻለንም። ጊዜ ይወስዳል። የአጥንት ጥንካሬ ጊዜ ይፈጃል። መንቀሳቀስ አለብን።”
ሌላም ምክር አላቸው።
“ምርመራ ላይ ሰዎች የቫይታሚን-ዲ እጥረት አለብህ ሲባሉ ሁሉም ህመማቸው በእሱ ምክንያት የመጣ ይመስላቸዋል። ቫይታሚን-ዲ እጥረት ተጓዳኝ ችግር ነው እንጂ ዋና ችግር ላይሆን ይችላል።ሁሉም ህመማችን ከዚያ የመጣ ነው ማለትም አይደለም።”
ለምሳሌ ዘላቂ የኩላሊት እና የጉበት ህመምተኞች የቫይታሚን-ዲ እጥረት ምልክቶችን ያሳያሉ።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ቫይታሚን-ዲ በስፋት እና በጥራት ያስፈልገዋል።
አለበለዚያ ዶክተር ይሁኔ እንደሚሉት “በአካሉ የበቃ፣ በአእምሮው የነቃ” የሚሉት ትውልድ አይፈጠርም።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)