ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቅርቡ በምርምር እና በትምህርት ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቷቸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከፕሮፌሰር በቀለ ጉተማን ጨምሮ፣ ለኤሜሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ለፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ የሜዳሊያ ሽልማት አበረክቷል።
በተጨማሪም ከአራት አስርት ዓመታት በላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በትጋት ሲያገለግሉ የቆዩ ምሁራንም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአምቦ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ፣ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም እዚያው ነው የተከታተሉት።
ፕሮፌሰሩ እንዴት ወደ ፍልስፍና ትምህርት እንደተሳቡ ሲጠየቁ ዩኒቨርስቲ እስኪገቡ ድረስ ስለ ፍልስፍና ትምህርት ምንም ፍንጭ እንዳልነበራቸው ይናገራሉ።
በ1970 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ምሑሩ፣ የመረጡትን ሳይሆን የፍልስፍና ትምህርት እንዲማሩ በተቋሙ መመደባቸውን ያስታውሳሉ።
“ያኔ የፍልስፍና ትምህርት በዩኒቨርስቲው ትልቅ ስም ነበረው። ከባድ ትምህርት ነው ተብሎም ይፈራ ነበር። እዚያ ስመደብ በጣም ደስ አለኝ፤ እና የመጀመሪያ ዲግሪዬንም በጥሩ ነጥብ አጠናቀቅኩ።
“በወቅቱ የበአገሪቱ ነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁለት ብቻ ስለነበሩ የተማረ የሰው ኃይልም በጣም ጥቂት ነበረ። ስለዚህ የተመረቀ ሁሉ በመንግሥት ተቋም ስለሚቀጠር ምን እሠራለሁ የሚል ስጋት አልነበረኝም” ይላሉ።
ከፍልስፍና ትምህርት ውጪ ሌላ ምንም አልተማርኩም
ፕሮፌሰር በቀለ፣ ያለ ምርጫቸው የገቡበት የፍልስፍና ትምህርትን ማጥናት ከጀመሩ በኋላ ወደ ሌላ የጥናት ዘርፍ ለመግባት ፍላጎት አድሮባቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጀርመን ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኦስትሪያ በፍልስፍና ትምህርት ተከታትለዋል።
“አንዴ ከፍልስፍና ጋር ከተዋወቅክ ጭራሽ መለየት አስቸጋሪ ይሆናል። ፍልስፍና መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ጠይቆ ለመመለስ የሚጥር ነው። በተለያየ አቅጣጫ አስፍተን እንድናስብ ያደርጋል። ለምሳሌ እውነት ምንድን ነው? እውነት ነው ተብለው የሚጠሩ ነገሮች ምን ዓይነት ናቸው? የሚሉትን በመጠየቅ ለመመለስ ጥረት የሚደረግበት ነው” ይላሉ።
ትምህርቱ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ከሃይማኖት ጋር የሚጣረስ ነገር አለው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ልዩነቱ ግን መልስ አሰጣጥ ላይ መሆኑን ያብራራሉ።
“ሁለቱም እውነት ሆኖ ያለው ነገር ምንድን ነው? ብለው ይጠይቃሉ። ሃይማኖት የሚሰጠው መልስ በራሱ መንገድ፣ በእግዚአብሔር እና በእምነት ላይ ይመሠረታል። ፍልስፍና ግን እውቀት እና ምክንያት ላይ ነው መሠረት የሚያደርገው።”
“ፍልስፍና ሕይወት ራሱ ምንድን ነው? ይላል። ሕይወት ትርጉም አለው የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳል። ፈላስፋዎቹ ይህችን ዓለም የሚረዱበት መንገድ ይበልጥ ትምህርቱን እንድወድ አደረገኝ” ሲሉም ያክላሉ።
ፍልስፍና የሰውን አስተሳሰብ ያሰፋል
ፕሮፌሰር በቀለ፣ የፍልስፍና ትምህርት በአጭር መንገድ ጠይቆ መልስ የሚሰጥ ሳይሆን “አንድንጠይቅ እና መልስ እንድንሰጥ የሚያነቃቃ ስለሆነ አስተሳሰብን ያሰፋል” ይላሉ።
ይህ የፍልስፍና ትምህርት ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያለው ስለሆነ፣ የፍልስፍና ምሑራን ሃይማኖትን የሚከተሉበት ሁኔታ ላይ ልዩነቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።
ብዙ ሰዎች የፍልስፍና መጽሐፍን ካነበቡ በኋላ ከሚከተሉት ሃይማኖት ጋር ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ “ይህ የሚመነጨው በበቂ ካለመረዳት እንዲሁም ደግሞ ይህ ጉዳይ ጥቂት መጽሐፍን አንብቦ ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
በሌላ መንገድ ደግሞ ከፍልስፍና ትምህርት በኋላ፣ ማኅበረሰቡ ከሚኖርበት ማኅበራዊ አውድ ውጪ ሆኜ እኖራለሁ ካሉም ሌላ ችግር መሆኑን ያነሳሉ።
“ሁሉንም ነገር አንደ ፍልስፍና እገልጻለሁ፤ እንደዚያ እኖራለሁ ከተባለ ችግሮች ያጋጥማሉ። ማኅበረሰቡ የሚለውን መቃወም አይቻልም። እርሱን አይቶ ማለፍ ያስፈልጋል።”
ፍልስፍናን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ተመሳሳይ መረዳት ላይ መድረስ አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር በቀለ፣ የግል ሕይወት እና የማኅበረሰቡን ሕይወት ለይቶ ማየት አስፈላጊ መሆኑን እና “ይህ ራሱ ፍልስፍና” መሆኑን ያብራራሉ።
ይህ ፍልስፍና በአሁኑ ወቅት፣ በትምህርት ተቋማት ብቻ የተወሰነ መሆኑን የሚያነሱት ፕሮፌሰር በቀለ “የሰው መረዳት በጨመረ ቁጥር ወደ ሕብረተሰቡ ዘልቆ ሰዎች የሚኖሩት ይሆናል” እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
ፕሮፌሰር በቀለ በ1973 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ ጊዜ ጀምሮ፣ ለ46 ዓመታት ያህል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና ትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ለመሆን ተወዳድረው፣ የመጨረሻዎቹ ሦስት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ገብተውም ነበር።
በአፍሪካ ፍልስፍና ላይ በመሥራት የሚታወቁት ፕሮፌሰር በቀለ፣ የኦሮሞ ፍልስፍና ላይ የሠሯቸውን የጥናት ወረቀቶች ጨምሮ ብዙ ጥናቶችን ለህትመት አብቅተዋል።