ቀደም ባለው ጥናት መሠረት እንኳ ከ300,000 በላይ ሰዎች በዓይን ጠባሳ ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን እንዳጡ በሚነገርላት ኢትዮጵያ የዓይን ብሌን ቀዶ ጥገና ሀኪሞች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ (የቀድሞው ብሔራዊ ደም ባንክ) አገልግሎት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጿል።
ለተቋሙ ፈተና የሆነበት ጉዳይ ምን እንደሆነ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበላቸው የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ፣ ” በኢትዮጵያ የዓይን ብሌን ቀዶ ጥገና የሚሰሩ ሀኪሞች 11 ብቻ ናቸው ” ብለዋል።
ምን ያህል ሀኪሞች መኖር ነበረባቸው ? ምን ያህል ሀኪሞች ያስፈልጋሉ ? ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ” በአገር ውስጥ ይህን ያህል ሀኪም ያስፈልጋል ” ተብሎ የተቀመጠ እስታንዳርድ እንደሌለ፣ ሆኖም እንደ አገር ካሉት 11 የዓይን ብሌን ቀዶ ጥገና ሀኪሞች መካከል አብዛኛዎቹ ያሉት አዲስ አበባ በመሆኑ በሌሎች አካባቢዎች ያሉት ሀኪሞችም አገልግሎቱም አነስተኛ አንደሆነ አስረድተዋል።
በገለጻው መሠረት በኢትዮጵያ ሕክምና እየተሰጠ ያለው ፦
– በአዲስ አበባ፣
– ሀዋሳ፣
– ጎንደር፣
– ጅማ፣
– መቐለ ብቻ ነው።
የሀኪሞች ስብጥርም አዲስ አበባ ወስጥ የተሻለ ቢሆንም፣ ጎንደር ሁለት በሌሎቹ ደግሞ በእያንዳንዳቸው ተቋማት አንድ ሀኪም ብቻ እንደሆነ፣ ቢያንስ በክልሎች ዋና ከተሞች የህክምና አገልግሎት የሚኖርበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ተገልጿል።
የሀኪሞችን ቁጥር ማብዛት ደግሞ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ሳይሆን ከሚኒስቴር ጋር በጋራ መስራትን፣ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መነጋገርን እንደሚጠይቅ፣ ተቋማትን የማስፋፋት ሥራውም ግንባታና በጀት እንደሚሻ ተመላክቷል።