በጋምቤላ ክልል “በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት” በሽታ ህጻናትን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ…… Leave a comment

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ውስጥ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተ “የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት” በሽታ ምክንያት በአንድ ሳምንት ውስጥ ህጻናትን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በዞኑ ውስጥ የተከሰተውን በሽታ ለመቆጣጠር አስፈላጊው “ጥንቃቄ ካልተደረገ” ወደ ሌሎች አካባቢዎች “የመዛመት ስጋቱ ከፍተኛ” እንደሆነ ቢሮው ገልጻል።

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን በሽታው የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ሰኞ የካቲት 3/2016 ዓ.ም. እንደሆነ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አቤል አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ከኮሌራ በሽታ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች ያሉትን ይህንን በሽታ ምንነት ለማረጋገጥ ወደ ላብራቶሪ “ናሙና ልኮ፤ ውጤት እየተጠባበቀ” መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ቢሮው፤ የተከሰተውን በሽታ “ለጊዜው አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት” በሚል እየጠራው ያለው በላብራቶሪ ባለመረጋገጡ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዶ/ር አቤል እንደሚያስረዱት ይህ በሽታው መጀመሪያ የታየው ኑዌር ዞን ካሉት አምስት ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው አኮቦ ወረዳ ነው።

በአኮቦ ወረዳ የተከሰተው በሽታ በአንድ ሳምንት ወስጥ በዞኑ ውስጥ ወደ የሚገኙት ዋንቱዋ፣ ማኩዌይ እና ላሬ ወረዳዎች እንደተስፋፋ የጤና ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ዶ/ር አቤል፤ “በእነዚህ ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት [በሽታ] ተከስቷል። በዚህ በአጠቃላይ 136 ሰው ተይዟል” ሲሉ ካለፈው ሰኞ አንስቶ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር ጠቅሰዋል።

በበሽታው ከተያዙት ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ ህይወታቸው ማለፉን የጤና ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል። ከህይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል “እድሜያቸው በአስር እና አስራ ቤት” ያሉ ህጻናት እንደሚገኙበት የሚገልጹት ዶ/ር አቤል፤ “እስከ 60 ዓመት” የሚገኙ ሰዎችም መኖራቸውም አስረድተዋል።

ኃላፊው፤ “[በሽታው] በሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ በተቅማጥ እና ትውከት ስለሚያስወጣ፤ በሰዓታት ውስጥ ይገድላል” ሲሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸው ያለፈበትን ምክንያት ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ፤ በሽታው “መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ” የህክምና ቡድኖች እና ግብአቶችን ወደ አካባቢው ማሰማራቱንም አስረድተዋል። በዚህም በበሽታው ከተያዙት 136 ሰዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ 96 ያህሉ በተሰጣቸው ህክምና ማገገማቸውን ዶ/ር አቤል ተናግረዋል።

31 ሰዎች ደግሞ ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑን አክለዋል።

የጤና ቢሮ ኃላፊው፤ በሽታው በዞኑ ለመከሰቱ በምክንያትነት የሚጠቅሱት በአካባቢው ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የመጸዳጃ ቤቶች በተደራጀ ሁኔታ አለመኖር ነው።

“ከዚህ ባለፈ ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚጎራበት ስለሆነ፤ በደቡብ ሱዳን በኩል [ከአውሮፓውያኑ] 2024 ጀምሮ ከ21 ሺህ በላይ ኬዞች አሏቸው። ሞትም አለ።

በደቡብ ሱዳን ድንበር ከእነሱም ወደ እኛም የሚመላለሱ ሰዎች ስላሉ መንስኤው ከዚያ ጋርም ሊገናኝ ይችላል” ሰሉ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል ያሉትን ጉዳይ ጠቅሰዋል።

ደንበር አካባቢ የሚታየው የሰዎች ዝውውር በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይም የሚታይ መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር አቤል፤ ይህ እንቅስቃሴ በሽታው ወደ ሌሎች ወረዳዎች እንዲዛመት ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል።

በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሽታውን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል መተግበር ያለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች የማይተገበሩ ከሆነ፤ በሽታው የመዛመት ስጋት “ከፍተኛ” መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በሽታውን ለመቆጣጠር “የእንቅስቃሴ ገደብ” የመጣል ሀሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም “ለጊዜው ትኩረት የተደረገው” የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

“እንደ ምግብ ያሉ አብዛኛው ሰብአዊ ድጋፎች ስለሚመላለሱ ለጊዜው መንገድ አልዘጋንም” ብለዋል።

ዶ/ር አቤል እንደሚያስረዱት፤ የክልሉ ጤና ቢሮ በዞኑ የተከሰተው በሽታ ለመቆጣጠር 65 ሚሊዮን ብር “ተጨማሪ በጀት” ያስፈልገዋል።

ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚሆነው እንደ “ድንኳን፣ ጄሪካን የመሳሰሉ መገልገያዎችን” ለመሸፈን የሚውል እና በአይነት የሚቀርብ ነው።

በጥሬ ገንዘብ የሚያስፈልገው ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን የሚሆነው በጀት እንደሆነ የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ይህ ገንዘብ በግዢ ለሚቀርቡ መድኃኒቶች፣ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚጓዙ ባለሙያዎች ክፍያ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን እንደሚውል ተናግረዋል።

ጤና ቢሮው 65 ሚሊዮን ብር የተገመተውን በአይነት እና በጥሬ ገንዘብ የሚቀርብ ድጋፍ ለማግኘት ለአጋሮች፣ ለክልሉ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡን የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር አቤል ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop