በግድያ የተጠናቀቀው ጥሎሽ Leave a comment

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው

ከሁለት ወራት በፊት ሕንድ ውስጥ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ።

ሦስት ሰዎች የሞቱበትና ሰባት ሰዎች የታሰሩበት ነበር።

በሕንድ ሰሜናዊ ግዛት ፕራይጋርጅ የተፈጠረው አጋጣሚ በርካቶችን አስደንግጧል።

ሺቫኒ ካስራውኒ ቀኑን ልትረሳው አትችልም።

“አምስት ሰዓት አካባቢ ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ ሰዎች ቤታችን መጡና ያለ ርህራሄ ይደበድቡን ጀመር” ትላለች።

ድብደባውን የፈጸሙት የወንድሟ አናሹ ሚስት የሆነችው አኒሽካ ቤተሰቦችና ዘመዶች ናቸው።

ድብደባው ከመፈጸሙ አንድ ሰዓት ቀድሞ እነ ሺቫኒ ቤት ውስጥ አኒሽካ ሞታ ተገኘች። በገመድ ታንቃ ሕይወቷ አልፎ ነበር የተገኘችው።

ፖሊስ አኒሽካ ራሷን እንዳጠፋች ገልጿል።

ቤተሰቦቿና ጎረቤቶቿ ግን አኒሽካ ለጥሎሽ ሲባል በሺቫኒ ቤተሰብ እንደተገደለች አምነዋል።

የሺቫኒ ቤተሰቦች የእንጨት ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን በጋራ ነው የሚኖሩት።

በታችኛው የቤታቸው ክፍል ሱቅና መጋዘን አላቸው። ከላይ ደግሞ መኖሪያ ቤታቸው ይገኛል።

በሁሉም ፎቅ ላይ መኝታ ክፍል አለ። አናሹ ከባለቤቱ አኒሽካ ጋር የሚኖረው የመጨረሻው ፎቅ ላይ ነበር።

ከተጋቡ አንድ ዓመት ሞልቷቸዋል።

በቤቱ የመጀመሪያ ፎቅ የአናሹ ቤተሰቦች፣ በሁለተኛው ፎቅ ደግሞ እህቱ ሺቫኒ ይኖራሉ።

“አኒሽካ ብዙውን ጊዜ ሁለት ሰዓት ላይ ለእራት ትመጣ ነበር። የዛን ቀን ሳትመጣ ቀረች። ተኝታ ይሆናል ብለን አሰብን” ትላለች ሺቫኒ።

ወንድሟ አራት ሰዓት ላይ ከሱቅ ሲመለስ አኒሽካን ለመጥራት ወደ ፎቁ ወጣ።

“ቢያንኳኳም፣ ቢደውልም መልስ አላገኘም። የበሩን መስታወት ሰብሮ ገባ። አኒሽካ ሞታ አገኛት። ሲጮህ ሁላችንም ወደ ላይ ወጣን።”

አናሹ እና አጎቱ የአኒሽካን መሞት ለፖሊስና ለቤተሰቦቿ አስታወቁ።

ከአንድ ሰዓት በኋላ የአኒሽካ ቤተሰቦችና ዘመዶች ቤቱን እንደከበቡት ፖሊስ ገልጿል። በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ከፍተኛ ድብድብ ተነሳ።

በሺቫኒ ስልክ በተቀረፀ ቪድዮ የሁለቱ ቤተሰቦች አባላት በዱላ ሲመታቱ ይታያል።

ፖሊሶች ነገሩን ለማብረድ ቢሞክሩም ሊሳካ አልቻለም።

የአኒሽካ አስክሬን ከቤት ከወጣ በኋላ ቤተሰቦቿ ቤቱን በእሳት አጋዩት።

ከቤቱ ሥር ያለው የእንጨት መጋዘን ብዙም ሳይቆይ ተቀጣጠለ። ሺቫኒ እና ቤተሰቦቿ መውጣት አልቻሉም።

ሺቫኒ እና አክስቷ የሁለተኛውን ፎቅ መስኮት ሰበሩ። ከጎን የነበረው ክፍል የአጎቷ ነበር። ራሳቸውን ማትረፍ ቢችሉም ቤተሰቦቿ ግን ከእሳቱ መውጣት አልቻሉም።

እሳቱን መቆጣጠር የተቻለው ከሦስት ሰዓት በኋላ ነው። የሺቫኒ እናትና አባት አስክሬን ተገኘ።

“እናቴ ደረጃው ላይ ቁጭ እንዳለች ነው አስክሬኗ የተገኘው” ትላለች ሺቫኒ እያለቀሰች።

ጥቃቱን የፈጸሙት 12 የአኒሽካ ቤተሰቦችና ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ ያልታወቁ ሰዎች እንደሆኑ ሺቫኒ ለፖሊስ ቃሏን ሰጥታለች።

የአኒሽካ አባት፣ አጎት እንዲሁም ልጆቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የአኒሽካ አባት የአናሹ ወላጆችና እህቶች አኒሽካን በጥሎሽ ምክንያት ያንገላቷት እንደነበርና እንደገደሏትም ለፖሊስ ገልጸዋል።

ሺቫኒ ግን ይህ ሐሰት ነው ትላለች።

ከአኒሽካ ቤተሰብ መኪናን ጨምሮ ሌሎችም ስጦታዎች በሠርጉ ወቅት ተቀብለዋል።

“ለልጃቸው የፈለጉትን ዓይነት ስጦታ ሰጥተዋል። ሌላ ምንም አልጠየቅናቸውም” ትላለች ሺቫኒ።

አናሹ ሚስቱ ከሞተችበት ቀን አንስቶ ቤቱ አልተመለሰም። ቤተሰቦቿ እንዳይገድሉት ፈርቷል።

በሕንድ ከ1961 ጀምሮ ጥሎሽ መስጠትም ሆነ መቀበል ሕገ ወጥ ተደርጓል።

ሆኖም ግን 90 በመቶ የሕንድ ሠርጎች በጥሎች ነው የሚከናወኑት።

ሚስቶች በጥሎሽ ምክንያት ጥቃት እንደሚደርስባቸው ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጓል።

ከ2017 እስከ 2022 ድረስ 35 ሺህ 493 ሴት ሙሽራዎች በጥሎሽ ምክንያት ተገድለዋል።

ሆኖም ግን ከጥሎሽ ጋር የተያያዘ ግድያ ተፈጽሟል በሚል የበቀል ጥቃት ሲፈጸም ተሰምቶ አያውቅም።

ሺቫኒ አሁን አጎቷ ጋር እየኖረች ነው። ቤታቸው እንዳልነበር ሆኖ ወድሟል።

“ፍትሕ እሻለሁ። ሕይወቴ፣ ቤተሰቤ፣ ቤቴ ተመሰቃቅሏል። ገለልተኛና ነጻ ምርመራ ይደረግ። ጥፋተኞች መቀጣት አለባቸው። ለምን ቤቱን አቃጠሉት? አሁን እንዴት አድርገን ነው ማስረጃ የምናገኘው?” ትላለች።

በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች ቤተሰቦቿን ከማዳን ይልቅ ቆመው ይመለከቱ እንደነበር ትናገራለች።

ፖሊስ ግን ክሱን ያጣጥላል። “ለምርመራ አስክሬን እያወጣን ነበር። ሁኔታውን ለማረጋጋት ነው እየሞከርን የነበረው” ብሏል ፖሊስ።

ከፍተኛ የፖሊስ አመራር እንዳሉት፣ ቤቱ ይቃጠላል ብሎ ያሰበ አልነበረም። አምስት ሰዎችን ከእሳት አደጋው ማዳን ችለዋል።

የአኒሽካ ቤተሰብ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ነው። ከአኒሽካ ሞት በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸው ታስረዋል።

የአኒሽካ አጎትና ልጆች ከታሰሩት መካከል ናቸው።

ጃዋሀር ላል ኬርዋኒ የአኒሽካ አያት ናቸው።

“ምን ልበላችሁ? ልጆቼ፣ የልጅ ልጆቼ ታስረዋል። አኒሽካን ገድለው ራሷን ያጠፋች እንዲመስል በገመድ ሰቀሏት” ይላሉ።

የአኒሽካ ሠርግ ቆንጆ እንደነበር ያስታውሳሉ።

“5 ሚሊዮን ሩፒስ ነው ያወጣነው። ለቤት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁላ ሰጥተናታል። ይህም 1.6 ሚሊዮን ሩፒስ የሚያወጣ መኪናን ይጨምራል” ይላሉ።

አኒሽካ ከወራት በፊት ልትጠይቃቸው ስትሄድ ትንኮሳ እየደረሰባት እንደሆነ እንደነገረቻቸው በመፀፀት ያስታውሳሉ።

“ታገሺ አልናት። ነገሮች እየተሻሻሉ ይሄዳሉ አልናት” ይላሉ አያትው።

የሺቫኒ ቤተሰቦች በአካባቢው የተከበሩ ናቸው። ደግና ተባባሪ ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጿቸዋል።

“መልካም ሰዎች ናቸው። ይሄ እንዴት እንደተፈጠረ አናውቅም። ፀብ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች አይደሉም። ማን ቤታቸውን እንዳቃጠለው አናውቅም። ግን ማንም ሰው ልጁ በገመድ ተሰቅላ ቢያይ በቁጣ ይንገበገባል” ሲል ጎረቤታቸው ይናገራል።

አኒሽካ “በጣም ሥነ ሥርዓት ያላት ተወዳጅ ልጅ ነበረች” ስትል ሌላ የሰፈሩ ሰው ትናገራለች።

የአኒሽካን ቤተሰብም የምትገልጸው “እንዲህ ያለ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸም የሚችሉ ዓይነት ሰዎች አይደሉም። አማቾቿ በእሳቱ መሞታቸው ያሳዝናል” በማለት ነው።

አክላም “አኒሽካ የሞተችው እንዴት ነው? ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሲያወራ አልሰማሁም” ስትል ትጠይቃለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡- (ቢቢሲ )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop