በሰሜን ምስራቅ ፓኪስታን ቸኮሌት ሰርቃለች በሚል ጥቃት በተፈፀመባት የ13 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛ ግድያ ተጠርጥረው ሁለት ጥንዶች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ኢቅራ የተባለችው ታዳጊ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ተደብድባ እና በርካታ አካላዊ ጉዳት አስተናግዳ ሆስፒታል መግባቷ ታውቋል።
የፖሊስ ቅድመ ምርመራ ታዳጊ ሰራተኛዋ ማሰቃየት እንደደረሰባት አሳይቷል።
ልጃቸው ወደ ሆስፒታል ስትወሰድ ከፖሊስ የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው የተናገሩት የኢቅራ አባት፤ ልጃቸው ራሷን ስታ ካዪት በኋላ በደቂቃዎች ልዩነት ሕይወቷ አልፏል።
የኢቅራ አባት “ሕይወቷ ሲያልፍ ውስጤ ስብርብር ሲል ተሰማኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግድያው በአገሪቱ ሰፊ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ለኢቅራ ፍትሕን የሚጠይቁ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን አግኝተዋል።
ከዚህ ባሻገርም የታዳጊዋ ግድያ በፓኪስታን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ እና የቤት ሰራተኞች አያያዝን በሚመለከት ክርክር አስነስቷል።
የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በሚመለከት ሕግ ከአገር አገር ቢለያይም በፑንጃብ ግዛት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በሕግ የቤት ሰራተኛ ሆነው መቀጠር አይችሉም።
ኢቅራ ከስምንት ዓመቷ ጀምሮ የቤት ሰራተኛ ሆና መስራት እንደጀመረች የተናገሩት አባቷ እዳቸውን ለመክፈል ስትል ስራ እንደጀመረች ተናግረዋል።
ለጥቂት አሰሪዎች ስትሰራ ከቆየች በኋላም ከሁለት ዓመት በፊት ስምንት ልጆች ላሏቸው ጥንዶች በወር 28 ዶላር እየተከፈላት ስትሰራ እንደነበር ታውቋል።
ፖሊስ ኢቅራ ከአሰሪዎቿ ቸኮሌት ሰርቃለች የሚል ክስ እንደቀረበባት ጠቁሞ ታዳጊዋ ከባድ ድብደባ እንደተፈፀመባት አስታውቋል።
ፖሊስ አክሎም ኢቅራ ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ድብደባ እንደተፈፀመባት ማስረጃ ማግኘቱን ገልጿል።
ለቢቢሲ የደረሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶዎች ታዳጊዋ እጅ እና እግሯ ላይ ስብራት እንዲሁም ጭንቅላቷ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባት ያሳያል።
የታዳጊዋን ሙሉ የጉዳት መጠን ለማወቅ የአስከሬን ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፤ ፖሊስ ለቢቢሲ የሕክምና ሪፖርት በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ተናግሯል።
“ልቤ የደም እንባ እያነባ ነው። ስንቶች በየቀኑ በእንደዚህ አይነት ተራ ስራ በየቤቱ ተመሳሳይ ጥቃት ያስተናግዳሉ? በማለት በቀድሞው ቲውተር የፃፉ አንድ የመብት ተሟጋች፤ “ደሃ እስከ መቼ ነው በዚህ መልኩ ልጆቹን ወደ መቃብር የሚልከው?” በማለትም ጠይቀዋል።
አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ደግሞ “ይህ ወንጀል አይደለም። ይህ ሃብታሞች ደሃዎችን እንዴት እንደሚይዙ የሚያሳይ ስርዓት ነፀብራቅ ነው” ብለዋል።
የኢቅራ አሰሪዎች እና ለቤተሰቡ የሚሰሩ የቁርዓን መምህር በግድያዋ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የቁርዓን መምህሩ ታዳጊዋን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ለሆስፒታሉ ሰራተኞች አባቷ ሕይወታቸው እንዳለፈ እና እናቷ እንደደሌሉ በመግለፅ ጥለዋት እንደሄዱ ተነግሯል።
የኢቅራ አባት “ለልጄ ሞት ተጠያቂ የሆኑት ሲቀጡ” ማየት እሻለሁ ብለዋል።
ግድያው ምንም እንኳ ሕዝባዊ ቁጣ ቢቀሰቅስም እንደዚያ አይነት ጉዳዮች በሕግ ለመቅጣት አስቸጋሪ እና በአብዛኛው ከፍርድ ቤት ውጭ በስምምነት የሚፈቱ ናቸው።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)