በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ የካቲት 3/2017 ዓ.ም. ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸው ነበር።
አቶ ልደቱ ከክልከላው በኋላ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፤ በአሜሪካ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን አነጋግረው “ልዩ ፈቃድ” ካላገኙ መጓዝ እንደማይችሉ እንደተናገራቸው ገልፀዋል።
አቶ ልደቱ ወደ አገር እንዳይመለሱ ከተከለከሉ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ “በውጭ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን በቅርቡ በጸደቁ አዋጆች ለመቅጣት በሰፊው ዝግጅት እየተደረገ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር ደሳለኝ ከጠቀሷቸው አዋጆች መካከል የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ አንዱ ነው።
የምክር ቤት አባሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ወደ ኢትዮጵያ የሚበሩ ማናቸውም አየር መንገዶች የተጓዦችን ስም ዝርዝር ከ3 ቀን በፊት ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የማሳወቅ ግዴታ ጥሎባቸዋል” ብለዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ አክለውም ይህ ድንጋጌ “ወደ አገር እንዳይገቡ የተከለከሉ ሰዎችን በአገር ውስጥ ኤርፖርቶች አቆይቶ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ከማድረግ ባለፈ ከመነሻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይበሩ መከልከልን እንደ ቀዳሚ እርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን የሰጠ” መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ የጠቀሱት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር።
ለ21 ዓመት በሥራ ላይ የቆየውን ሕግ ያሻሻለው አዋጅ ካስተዋወቃቸው አዳዲስ ነገሮች መካከል አንደኛው የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ምዝገባ ሥርዓት ነው።
የአጓጓዥ ኃላፊነትን የሚዘረዝረው የአዋጁ ድንጋጌ፤ “ማንኛውም አጓጓዥ መንገደኛን ወደ ሀገር ለማስገባት ወይም ከሀገር ለማስወጣት ከማጓጓዙ ከሦስት ሰዓት በፊት የመንገደኛውን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ለአገልግሎቱ ማሳወቅ ወይም መላክ አለበት” ይላል።
ከኢትዮጵያ የሚወጡ መንገደኞችን ያሳፈረ ማንኛውም የአየር ትራንስፖርት አጓጓዥም በተመሳሳይ “የመንገደኞቹን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ከማጓጓዙ ከሦስት ሰዓት በፊት ወደ ሚሄድበት አገር ማሳወቅ አለበት” የሚል ድንጋጌ በአዋጁ ተካትቷል።
ከስምንት ወራት በፊት ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያው ከዚህ ድንጋጌ ጀርባ ያለው አመክንዮ የዓለም የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ያወጣው የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር አስተዳደር መመሪያ መሆኑን ገልጿል።
የድርጅቱ መመሪያ አገራት የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ምዝገባ ሥርዓት እንዲዘረጉ የሚያስገድድ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2017 የወጣው ይህ መመሪያ የመንገደኞች ቅድመ ጉዞ መረጃ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ዘዴ ሲሆን፣ በረራው ከመነሳቱ በፊት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ተሰብስበው ወደ ድንበር ቁጥጥር ኤጀንሲዎች እንደሚተላለፉ ያትታል።
በመመሪያው መሠረት የመንገደኞች ቅደመ ጉዞ መረጃ በሁለት የተለያዩ ምድቦች የሚከፈል ሲሆን፣ ለአየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ከራሳቸው አውቶማቲክ ሲስተም የሚገኝ ቀዳሚው ከበረራ ጋር የተያያዘ መረጃ ነው።
ሁለተኛው ምድብ በአሁኑ ጊዜ በማሽን ሊነበቡ በሚችሉ ፓስፖርቶች እና በሌሎች ኦፊሴላዊ የጉዞ ሰነዶች ላይ ከሚገኙት መረጃዎች ጋር የሚዛመድ የእያንዳንዱ ተሳፋሪ እና የአውሮፕላን በረራ አባል መረጃ ነው።
ይህ የዓለም ሲቪል አቪየሽን ድርጅት መመሪያ በአውሮፕላን ኦፕሬተሮች የሚሰበሰበው የእያንዳንዱ መንገደኛ ቅደመ ጉዞ መረጃ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚተላለፍ ያትታል።
የመንገደኞች ቅደመ ጉዞ መረጃ የተጓዦቹን ሙሉ ስም፣ የትውልድ ዘመን፣ ዜግነት እና ፆታን ማካታት አለበት። ይህ መረጃም ከበረራ ሦስት ቀናት በፊት መላክ እንዳለበት መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
የተጓዦችን መረጃ ቀድሞ አለመላክ የአውሮፕላን ጉዞ እንዲዘገይ ወይም በመዳረሻ አገራት ለቅጣት ሊዳርግ እደንደሚችል መመሪያው ያትታል።
ኢትዮጵያ የዓለም ሲቪል አቪየሽን ድርጅት ፈራሚ መሆኗን ያስታወሰው የአዋጅ ማሻሻያው፤ “አጓጓዥ መንገደኛን ወደ አገር ለማስገባት ወይም ከአገር ለማስወጣት ከማጓጓዙ በፊት የመንገደኛውን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ለአገልግሎቱ ከሦስት ሰዓት በፊት የማሳወቅ ወይም መላክ ግዴታ እንዲኖራቸው” መደረጉን አስረድቷል።
የአዋጅ ማሻሻያው “መረጃውን በመለዋወጥ የሚፈለጉ አደገኛ ወንጀለኞች በተለይም ሽብርተኞችን ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ሲል የሥርዓቱን ጥቅም አብራርቷል።
ከተጓዦች መረጃ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት የጸደቀው ይህ አዋጅ ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ስለሚታገዱ ሰዎችም አዲስ ድንጋጌን አካትቷል።
በድንጋጌው መሠረት የኢሚግሬሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር “በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት በብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽ እና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን ማንኛውንም ሰው ከአገር እንዳይወጣ ማገድ ይችላል።”
በ1995 የወጣው የቀድሞው አዋጅ ይህን ሥልጣን የሰጠው ለፍርድ ቤት ብቻ ነበር። ይህ አዋጅ “ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው” የሚል ድንጋጌ ነበረው። አዲሱ ማሻሻያ ግን ይህን ሥልጣን በተደራቢነት ለአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተርም ሰጥቷል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)