ሙባረክ ጀማል 26 ዓመቱ ነው። ሻሸመኔ ከተማ በሚገኝ የግል ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን ጨርሶ የመውጫ ፈተና አላለፈም። ስለ ነገ ህይወቱ እየተብሰለሰለ ባለበት ጊዜ ነው “ታይላንድ ውስጥ በወር እስከ 1,500 የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ስራ አለ” የሚል ወሬ የሰማው።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ቤተሰቦቹ ቤት ቁጭ ባለበት በዶላር የሚያስከፍለው “የፕሮሞሽን ስራ” በሚያውቀው ሰው በኩል ሰተት ብሎ መጣ። ለአርሶ አደር ወላጆቹ የመጀመሪያ ልጅ ለሆነው ሙባረክ፤ ይህ እድል የሚታለፍ አልነበረም። ቤተሰቡንም ሆነ ታናናሾቹን መርዳት እንደሚችል አሰበ።
” ‘ስራው ምንድነው?’ ብዬ ብዙም አልጠየኩም ነበር” ይላል መለስ ብሎ ሲያስታውስ። ታይላንድ እንደሚወስደው የነገረው “አብዲ” የተባለ ታይላንድ የሚገኝ ደላላ ነገሮችን ያከናወነው በፍጥነት ነበር። በአምስት ቀናት ውስጥ ለጉዞ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተጠናቅቀዋል።
ሙባረክ፤ መስከረም 2016 ዓ.ም. ከምዕራብ አርሲዋ አዳባት የገጠር ቀበሌ ተነስቶ አዲስ አበባ ገባ። ቀጥሎ ታይላንድ ባንግኮክ ከተማ የሚበረውን አውሮፕላን ተሳፈረ። አብሮት ሌላ ኢትዮጵያዊ ተጓዥ ነበር።
ባንግኮክ ሲደርሱ እንደጠበቁት የተቀበላቸው ሰው አልነበረም፤ ቀጥታም ወደ ስራው ቦታ አልሄዱም። ደላላው በስልክ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መጀመሪያ ቻንግ ራይ ወደተባለችው የድንበር ከተማ ተጓዙ። ቀጥሎ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የታይላንድ ጎረቤት ወደ ሆነቸው ላኦስ ተሻገሩ።
ላኦስ ሲደርሱ መልስ የሚሰጥ ባያገኙም ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። ያመጣቸው ደላላ “የሚቀጥር ኩባንያ ባለማግኘቱ” ከአንድ ሳምንት የላኦስ ቆይታ በኋላ በድጋሚ ወደ ታይላንድ ተመልሰው ወደ ሌላ ከተማ ጉዞ ጀመሩ።
ይህኛው ጉዞ የታይላንድ እና ምያንማር ድንበር አቅራቢያ ወደ ምትገኘው ሜይ ሶት ከተማ የሚወስድ ነበር። ቀኑን ሙሉ ተጉዘው ምሽት ላይ ወደ ከተማዋ ሲገቡ እረፍት ለማድረግ እንኳ እድል አልተሰጣቸውም።
ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ የቻይና ዜግነት ያላቸው ሰዎች መጥተው “ፓትሮል” መሳይ ተሽከርካሪ ላይ ጭነው ወደማያቁት ቦታ ይወስዷቸው ጀመር። በዚህኛው ጉዞ ደላላው “አብዲ” አብሯቸው አልነበረም። እዛው ሜይ ሶት ከተማ ቀርቷል።
የምሽት ጉዞው ከተጀመረ ከአስር ደቂቃ በኋላ መኪናው ከዋናው መንገድ ወጥቶ ጫካ ውስጥ እንዲወርዱ ከተደረጉ በኋላ በሌላ መኪና ተጫኑ። ትንሽ ከተጓዙ በኋላም በድጋሚ መኪና ተቀየረ።
ሶስተኛው መኪና የቆመው ታይላንድ እና ምያንማርን የሚያዋስነው ሞይ ወንዝ ሲደርሱ ነው።
ቀጣዩ ጉዞ በጀልባ ነበር። ከጀልባው በኋላ ደግሞ ሌላ መኪና። በወታደሮች የሚጠበቅ ትልቅ ካምፕ ደጃፍ ላይ የደረሱት ሌሊት አምስት ሰዓት ገደማ ነው። ግራ መጋባት እና ፍርሃት የከበባቸው ስድስቱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፤ የተለያዩ ህንጻዎችን የያዘው ካምፕ ምን እንደሆነ አላወቁም ነበር።
ቢቢሲ በዚህ ልዩ ዘገባ ከተጎጂዎች በተጨማሪ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የታይላንድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን፣ ከካምፕ የሚወጡ ኢትዮጵያውያንን የሚያግዝ ድርጅት እንዲሁም ጉዳዩን የሚከታተሉ ተንታኝ አነጋግሯል።
እንደ ምያንማር፣ ካምቦዲያ እና ላኦስ ባሉት የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የተስፋፉት እነዚህ ካምፖች (compounds) በየዓመቱ “በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ የሚገኝባቸው” የኦንላይ ማጭበርበሪያ ናቸው።
ህገ ወጥ የሰዎች እና ህጻናት ዝውውር፣ የግዳጅ ወንጀለኝነት፣ የሰዎች ስቃይ፣ ህገ ወጥ ቁማር እንዲሁም በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል (money laundering) የእነዚህ ካምፖች መገለጫ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የመድኃኒት እና የወንጀል ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ዩናይትድ ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ የተሰኘው የአሜሪካ መንግሥት ቲንክ ታንክ የበርማ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ጄሰን ታወር እንደሚገልጹት የእነዚህ ካምፖች መነሻቸው የቻይና ሕገ ወጥ ቁማር ኩባንያዎች ናቸው።
የቻይና መንግስት በእነዚህ አቋማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ የወንጀል ቡድኖቹ አጎራባች ወደሆኑት ፊሊፒንስ፣ ካምቦዲያ እና ምያንማር በመሻገር ተመሳሳይ ተግባር መፈጸም መቀጠላቸውን ጄሰን ያስረዳሉ።
ጄሰን እንደሚገልጹት የወንጀል ቡድኖቹ ዋነኛ ዓላማ ቻይናውያን ዜጎችን በተለያዩ መንገዶች በማታለል ቁማር ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ገንዘብ መሰብሰብ ነበር። የቻይናን እርምጃ ተከትሎ ግን ፊታቸውን ወደ ሌሎች ሀገራት ዜጎች እና አዲስ የበይነ መረብ ማጭበርበር ዘዴዎችን ወደ መጠቀም አዞሩ።
ጄሰን፤ “[በዚህ ወቅት] የግዳጅ ሰራተኞችን መጠቀም ጀመሩ። ለዚህም መጀመሪያ ላይ ሰዎችን ማገት ያዙ። 2021 አካባቢ ካምቦዲያ ውስጥ የሰዎች የመታገት ታሪኮች ይሰሙ ነበር። [የግዳጅ ሰራተኛ የሚሆኑት] በመጀመሪያ ቻይናውያን ነበሩ፤ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፋፉት” ሲሉ የተስተዋለውን ለውጥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኮቪድ ምክንያት ታግደው የነበሩ በረራዎች በድጋሚ ሲጀመሩ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ሰዎች መመልመል መጀመራቸውን ያስረዳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በእነዚህ ካምፖች ውስጥ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በምያንማር እና ካምቦዲያ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፥
“በምያንማር ቢያንስ 120,000 ሰዎች የኦንላይን ማጭበርበር እንዲያከናውኑ በሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ታማኝ ምንጮች የሚያመላክቱ ሲሆን በካምቦዲያም በተመሳሳይ 100,000 ሰዎች በኦንላይን ማጭበርበር ውስጥ በግዳጅ እንደተሳተፉ ተመላክቷል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።
ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው በካምፖቹ ውስጥ ካሉ ተጎጂዎች መካከል ከ13 እስያ ሀገራት የመጡ ሰዎች ይገኙበታል። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም ተጎጂዎች ከመጡባቸው አካባቢዎች መከካል የተጠቀሱ ሲሆን በሪፖርቱ ላይ በቅድሚያ የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ነች። ኬንያ እና ታንዛኒያ በሪፖርቱ ላይ የተዘረዘሩ ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ናቸው።
ታይላንድ ቺያንግ ራይ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የህገ ወጥ የሰዎችን ዝውውርን ለመከላከል የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የምትመራው ናንሲ (በደህንነት ስጋት ምክንያት ስሟ የተቀየረ) እንደምትናገረው፤ ከእነዚህ ካምፖች ከሚወጡ አፍሪካውያን መካከል የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያ፣ የብሩንዲ፣ የሩዋንዳ እና የሱዳን ዜጎች ይገኙበታል።
ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ግን ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው “ኢትዮጵያውያን እና ዩጋንዳውያን” መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች። ናንሲ፤ ኢትዮጵያውያን ተጎጂዎች ለመብዛታቸው በምክንያትነት የምትጠቅሰው አንዱ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ወደ ታይላንድ መግባት መቻላቸውን ነው።
ምያንማር፣ ላኦስ እና ካምቦዲያ ወደሚገኙት ካምፖች የሚጓዙ ተጎጂዎች አብዛኛውን ጊዜ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ታይላንድ ነው። በቀጣናው ለሚታየው ህገ ወጥ ሰው ዝውውር መተላለፊያ ወደ ሆነችው ታይላንድ ከአዲስ አበባ “ቀጥታ በረራ መኖሩ” እና ኢትዮጵያውያን “የመዳረሻ ቪዛ” (on arrival visa) የሚያገኙ መሆናቸው ተጋላጭነታቸውን እንደጨመረው ታስረዳለች።
በሀገሪቱ የሚገኙት የተለያዩ ግጭቶችም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በብዛት ካምፖቹ ወስጥ ለመገኘታቸው ምክንያት እንደሆነ ታምናለች።
‘ጃው ኬ’ ካምፕ
“Humanity Research Consultancy Limited” የተሰኘው “ዘመናዊ ባርነትን” ለመዋጋት የሚሰራ የዩናይትድ ኪንግደም ተቋም ያደራጀው በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የማጭበርበሪያ ካምፖች ዝርዝር እንደሚያሳየው ምያንማር ውስጥ ይህ ተግባር የሚፈጸምባቸው ቢያንስ 154 ግቢዎች አሉ።
የካምፖቹ ዝርዝር እንደሚያሳየው ከሌሎች ሀገራት ይበልጥ ምያንማር ውስጥ ብዛት ያላቸው ካምፖች ይገኛሉ። የካምፖቹ ባለቤቶች ህንጻዎችን የማጭበርበር ድርጊት ለሚያከናውኑ የወንጀል ቡድኖች ያከራያሉ።
በምያንማር የሚገኙት ካምፖች የየራሳቸው መጠሪያ ስያሜ አላቸው።
ከምዕራብ አርሲ ዞን የተነሳው ሙባረክ የገባው “ጃው ኬ” የሚል ስያሜ ባለው፤ ታይላንድ እና ምያንማር በሚለየው “ሞይ” ወንዝ አጠገብ ወደሚገኘው ካምፕ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው “ጃው ኬ” የሚገኙ እና ከካምፑ የወጡ ተጎጂዎች ግቢው ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ከ700 እስከ አንድ ሺህ ያደርሱታል። ካምፑ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች የሚሰሩት ኢትዮጵያውያኑ ማደሪያ እና መመገቢያቸው በዚያው ግቢ ውስጥ ነው።
ኢትዮጵያውያን እና ከሌሎች ሀገራት የመጡ እና በግዳጅ የማጭበርበር ስራ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች የሚኖሩት በኮንቴይነሮች ተደራርበው በተሰሩ ክፍሎች ውስጥ ነው። ተደራራቢ አልጋዎችን የሚይዙት ክፍሎቹ ከ12 እስከ 15 ሰዎች ይኖሩባቸዋል።
ብዙውን ጊዜ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖሩት ለተመሳሳይ ኩባንያ የሚሰሩ እና ከአንድ ሀገር የመጡ ሰዎች ናቸው። የወንዶች እና የሴቶች መኖሪያዎች የተለያዩ ናቸው።
ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ገደማ ወደ ካምፑ የደረሱት እነ ሙባረክ ሻንጣቸውን አስቀምጠው ቀጥታ የተወሰዱት ማጭበርበሩ በሚከናወንበት ህንጻ ላይ ወደሚገኘው የሚያሰራቸው ኩባንያ ቢሮ ነበር። ኮምፒውተር ላይ መጻፍ መቻላቸውን ከተፈተኑ በኋላ በማግስቱ ስራ እንደሚጀምሩ እንደተነገራቸው ሙባረክ ይናገራል። በዚህ ሰዓትም ስራው ምን እንደሆነ አልተነገራቸውም።
“ወደ ግቢው የገባን ምሽት ስለደነገጥን ‘ስራውን ምን ይሆናል’ ብለን አላወራንም። የተነጋገርነው በንጋታው ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለን ነው። አንዱ ‘ስራው scamming ነው’ አለ። [ሌሎቹ] ‘scamming ምንድነው?’ ብለው ጉግል አደረጉ። አንዱ ልጅ ‘ማጭበርበር ነው’ አለ። እኔ ጉግል አላደረግኩም፤ እነርሱ እንደነገሩኝ ተቀበልኩ” ሲል ትክክለኛው ስራ መጀመሪያ የተነገረው እንዳልሆነ የተረዳበትን አጋጣሚ ያስታውሳል።
ሙባረክ ወደ ግቢው ከገባበት ማግስት ጀምሮ ያሉትን 15 ቀናት ያሳለፈው ስልጠና ላይ ነው። ስልጠናው “ደንበኞችን እንዴት ማነጋገር እንደሚችሉ” ለማሳየት ቢባልም ጉዳዩ እንዴት አጭበርብረው ብር እንደሚቀበሉ የሚያስተምር ነበር።
በአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ወስጥ መደበኛው “የስራ ሰዓት” 12 ሰዓት ነው።
ስልክ እና ፓስፖርቱን የተቀማው ሙባረክ ከዚህ ካምፕ መውጣት የሚችልበት እድል አልነበረውም። በተፈጸመበት ድብደባ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በድጋፍ የሚራመድ ሰው የተመለከተው ወደ ካምፑ በገባ በሳምንቱ ነበር።
“ፒግ ቡቸሪንግ ስካም”
በደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በሚገኙት ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች የሰዎችን ገንዘብ ለመውሰድ ቢያንስ 10 አይነት የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ የተባበሩት መንግስታት የመድኃኒት እና የወንጀል ቢሮ መረጃ ያሳያል። በአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ውስጥ የሚፈጸመው እና የተለመደው የማጭበርበር ዘዴ ግን “ፒግ ቡቸሪንግ” የተሰኘው ነው።
“ፒግ ቡቸሪንግ” ከብትን አደልቦ፤ ስጋው መፋፋቱ ሲረጋገጥ ማረድን የመሰለ ዘዴ ነው። የዩናይት ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ የበርማ ፕሮግራም ዳይሬከተሩ ጄሰን ታወር፤ ይህ ዘዴ “የተጎጂዎችን ስነ-ልቡና በመቆጣጠር ያላቸውን በሙሉ ተሟጥጦ የሚወሰድበት” እንደሆነ ይናገራሉ።
ለሙባረክ የተሰጠውም ስልጠና “አሊሻ” የተባለችን ሴት በመምሰል በቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ፓኪስታን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን “አዕምሮ መቆጣጠር” ላይ ያተኮረ ነበር።
የሙባረክ ስራ በየቀኑ የሚመጡለትን ከአስር በላይ የስልክ ቁጥሮች እየተቀበለ ግለሰቦቹን በተለያዩ የዋትስአፕ አካውንቶች ማውራት ነው። ከመጀመሪያው ቀን እስከ መጨረሻው ከግለሰቦቹ ጋር የሚኖረው ንግግር ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ መመሪያ (chat frame) በኩባንያው ይዘጋጃል።
“አሊሻ” የተባለችው ገጸ ባህሪ የምትሳለው የተሳካላት፣ ብዙ ሀገራት እየተዘዋወረች የምትዝናና የንግድ ሰው ተደርጋ ነው።
“በመጀመሪያው ቀን ስለ አሊሻ የኑሮ ስታይል፣ የኑሮ ደረጃ [ትገልጻለህ]። ‘ዱባይ፣ ፓሪስ ለጉብኝት ሄጃለው’ ብለህ ታወራለህ። በኦርደር የተዘጋጁ ፎቶዎች አሉ። የሆቴል፣ የሻወር፣ የጉብኝት ላይ፣ የራቁት ፎቶዎች አሉ። ባይጠይቁም የራቁት ፎቶ ይላክላቸዋል፤ ጭንቅላታቸውን ትቆጣጠራለህ” ሲል ያስረዳል።
“አሊሻ” የተባለች ቆንጆ ሴት እያናገረ እንደሆነ የሚያስበው ግለሰብ፤ በቪድዮ ወይም በድምፅ ማውራት ቢፈልግ ለዚሁ ተግባር የተዘጋጁ “ሞዴሎች” ተቀብለው ያነጋግሩታል። “ሞዴሎቹ” የሚያነጋግሩት ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ እና ቅንጡ ቤት በሚመስል ክፍል ውስጥ ነው።
ሌሎች ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ለዚሁ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች ጭምር እንዳላቸው ሌላ ካምፕ ውስጥ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሙባረክን በሚያሰራው ኩባንያ መመሪያ መሰረት ግለሰቡን የማውራት እና የማሳመን ሂደት በአራት ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ አለበት። በአራተኛው ቀን ላይ ግለሰቡ ገንዘብ ማጭበርበር ወደሚጀመርበት ሂደት ይሸጋገራል። ቀጣዩም ሂደት ቀናትን የሚወስድ ነው።
የተሳካላት የንግድ ሰው ሆና የምትቀርበው “አሊሻ”፤ ግለሰቡ የእርሷ አይነት ስራ ላይ ተሰማርቶ ገቢ እንዲያገኝ እንደምትፈልግ ትገልጻለች። የኦንላይን ስራው የሚከናወነው የግዙፉን የመገበያያ ኩባንያ “አማዞን” ድረ ገፅን በሚመስል በማጭበርበሪያ ኩባንያው በተዘጋጀ ሀሰተኛ ድረ ገፅ ላይ ነው።
የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ አነስተኛ ገንዘብ ወደ ድረ ገጹ እንዲያስገባ የሚጠየቀው ግለሰቡ፤ እምነት ለመፍጠር ሲባል ያስገባው ብር ላይ ተጨማሪ “ኮሚሽኖችን” እንዲያገኝ ይደረጋል። በኩባንያ መመሪያ መሰረት ግለሰቡ ገንዘቡን ከትርፍ ጋር የሚያወጣው ደረጃ (stage) አንድ እና ሁለት ላይ ነው።
ሙባረክ፤ “ደረጃ ሶስት ላይ ሁሉም ነገር ወጥመድ ነው። ሶስተኛ ስቴጅ ላይ ምንም የሚፈቀድለት ገንዘብ ማውጣት የለም። ተሳስተህ ፈቀደህለት ገንዘብ ካወጣ እዛው ፊት ለፊት በኤሌክትሪክ ቶርች ያደርጉሃል” ሲል ገንዘብ መውሰዱ በዚህ ደረጃ ላይ እንደሚጀመር ያስረዳል።
ግለሰቡ በዚህ ደረጃ ላይ የሚጠየቀው ገንዘብ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሲሆን በድረ ገጹ ላይ “በኮሚሽን” መልኩ የሚታየው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ ነው። ይሁንና ስራውን አጠናቅቆ ገንዘቡን ለማውጣት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በተደጋጋሚ ገንዘብ እንዲያስገባ ይጠየቃል። ከፍተኛ ሆኖ የሚታየውን ኮሚሽን ለማግኘት ጉጉት ውስጥ የሚገባው ግለሰቡ በየሰበቡ የሚጠየቀውን ገንዘብ ያስገባል።
ቤት፣ መኪና … ግለሰቡ ያለውን በሙሉ ሸጦ ገንዘቡን እስከሚያስገባ ድረስ ይህ ሂደት ይቀጥላል። ማስገባት የሚችለው ገንዘብ በሙሉ መሟጠጡ ሲያልቅ ወደ ድረ ገጹ ወደ ሚገኘው አካውንት መግባት ይከለከላል፣ አሊሻም ከዋትስአፕ ላይ ትጠፋለች።
እስር እና ስቃይ
“ህጋዊ ስራ እናገኛለን” ብለው ከመጡ በኋላ ራሳቸውን በእነዚህ ካምፖች ውስጥ የሚያገኙ ተጎጂዎች አብዛኛውን ጊዜ የሰዎችን ህይወት የሚያመሳቅል የገንዘብ ማጭበርበር ስራ ለመስራት ፈቃደኛ አይሆኑም። ይህንን የሚረዱት የወንጀል ቡድን መሪዎች፤ የግዳጅ ሰራተኞቹን “ባህሪ የሚቀይሩ” ተግባራትን እንደሚፈጽሙ የዩናይትድ ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ የበርማ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጄሰን ታወር ይናገራሉ።
“[ባህሪያቸውን ለመቀየር] ሽልማቶችን ይጠቀማሉ። አደንዛዥ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። ማጭበርበሩን እንዲፈጽሙ ለማድረግ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎችን የሚያገኙበትን ዕድል ያመቻቻሉ። በዚህም ‘እምቢ’ ካሉ ስቃይ ይፈጸምባቸዋል” ይላሉ።
ካምፖቹ ውስጥ በግዳጅ የሚገኙ ሰዎችን ለማስወጣት እና ከወጡም በኋላ እርዳታ እንዲያገኙ የምትሰራው ናንሲ፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተጎጂዎቹ ላይ የሚደርሰው አካላዊ ጉዳት መጨመሩን ማስተዋሏን ታስረዳለች። የናንሲ ድርጅት ድጋፍ ያደረገላቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ስቃይ መካከል መገረፍ፣ በኤሌክትሪክ ‘ሾክ’ መደረግ፣ እጃቸው ታስሮ መንጠልጠል እና ጨለማ ክፍል ውስጥ መታሰር ይገኙበታል።
“በቅርቡ፤ አንጎላቸው ላይ በተደጋጋሚ በኤሌክትሪክ ሾክ ስለተደረጉ የአዕምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አጋጥመውናል። ማን እንደሆኑ፣ ስማቸውን፣ ከየት እንደመጡ አያውቁም” የምትለው ናንሲ፤ “ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ወንድ እና ሴቶች” መኖራቸውንም ገልጻለች።
ቢቢሲ ካምፖች ውስጥ ከነበሩ እና ካሉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከቤተሰቦች ያገኛቸው በርካታ ፎቶዎች በድብደባ ሰውነታቸው የበለዘ ወንድ እና ሴቶችን ያሳያሉ። በኤሌክትሪክ ሾክ በመደረጉ እግሩ “ውሃ የቋጠረ” ሰው ፎቶም ቢቢሲ ተመልከቷል።
ለአለቆች አለመታዘዝ፣ ጥያቄ ማንሳት እና ኩባንያው በሚያስቀምጠው እቅድ ልክ ገንዘብ ማጭበርበር አለመቻል እነዚህን ቅጣቶች ከሚያስከትሉ “ጥፋቶች” መካከል ናቸው።
የእነ ሙባረክ ኩባንያ በግዳጅ ሠራተኞቹ ላይ የጣለው ወርሃዊ ገቢ አምስት ሺህ ዶላር ነው።
ሙባረክ፤ የመጀመሪያው ወር እቅዱን ባለማሳካቱ የደረሰበት ቅጣት ከመደበኛው 12 ስራ ሰዓት ተጨማሪ እንዲሰራ መደረግ ነበር። በሁለተኛውም ወር ላይ የተባለውን ያህል ገንዘብ ገቢ ማድረግ አልቻለም። የዚህኛው ወር ቅጣት በየቀኑ ከስራ ሰዓት በኋላ ለአንድ ሰዓት ግቢው ውስጥ መሮጥ ነበር።
ከዚህ በኋላ የነበሩት ቅጣቶች እየከበዱ መምጣታቸውን ሙባረክ ያስታውሳል።
“በየቀኑ አንድ ለመጭበርበር በጥሩ ሂደት ላይ ያለ ደንበኛ መኖር አለበት። ከሌለ ትገረፋለህ። ፊት ለፊት አውጥተው ይገርፉሃል፣ ቁጭ ብድግ ያሰሩሃል። የምትቀመጥበትን ወንበር እንኳ ሳታስገባ ከሄድክ ትቀጣለህ። ከሀይማኖቴ ጋር ስለሚጋጭብኝ ከበደኝ። በፊትም እየሰራሁ የነበረው እነሱን ፈርቼ ነው” ይላል።
ሙባረክ ለተከታታይ ወራት የሚጠበቅበትን አምስት ሺህ ዶላር ማስገባት አልቻለም። በአንዱ ወር ደግሞ ይባሱኑ የሚጭበረበሩት ሰዎች እምነት ለመፍጠር የሚሰጣቸውን አነስተኛ ኮሚሽን ይዘው ጠፉ።
ይህን ጊዜ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሰባት ሺህ ዶላር ከፍሎ ከካምፑ እንዲወጣ ነገሩት። ይህን ያህል ገንዘብ ማግኘት እንዳማይችል ተናግሮ በልመና እና ድርድር ሶስት ሺህ ዶላር ለመክፈል ተስማማ።
ቤተሰቦቹን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ በማድረግ ካምፕ ውስጥ ካሉት ልጆች 2,500 ዶላር አሰባሰበ። ለኩባንያው አለቆች የቀረውን 500 ዶላር መክፈል እንደማይችል እና ቤተሰቦቹን እንደማያገኝ ነገራቸው።
ይህ አይነቱ ነገር ከኩባንያው አለቆች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ሁለት ሆነው አንድ ክፍል ውስጥ አስገብተው “በሽቦ አለንጋ” ይደበድቡት ጀመር።
“የሽቦ አለንጋ አለ። በዚያ አንዴ ሲመታኝ ጭንቅላቴን ቆረጠኝ። ለመከላከል እጅህን ስታነሳ በኤሌክትሪክ ሾከር ሾክ ያደርጉሃል። ከጆሮዬ በታች በኩል ለሁለት ሆነው ሲመቱኝ ራሴን ስቼ ወደቅኩ” ሲል የደረሰበትን ያስታውሳል።
ራሱን በመሳቱ ቅጣቱ አልቀለለትም። የግዳጅ ሠራተኞች ወደ ሚታሰሩበት “ዳርክ ሩም” የተባለው ክፍል ወደሚገኝበት አካበቢ ተወስዶ አግድም በቆመ ብረት ላይ ታሰረ።
እዚህ ማሰቃያ ስፍራ የሚመጡ የግዳጅ ሠራተኞች የሚጠበቁት እና ቅጣት የሚደርስባቸው በታጣቂዎች ነው። ቀን አስር ሰዓት ገደማ እጁ በቁመቱ ልክ ተወጥሮ የታሰረው ሙባረክ፤ ሌሊቱን በዚህ መልኩ አሳለፈ። ታስሮም ቢሆን እንቅልፍ እንዲወስደው አይፈቀድለትም።
“በሀይማኖታችን ስቃይ ላይ ስትሆን በሀሳብህ (imagination) ትሰግዳለህ። ማታ አራት ሰዓት እኔም እንደዛ እሰግዳለሁ ብዬ አይኔን ጨፍኜ ወደ ፀሎት ገባሁ። [ጠባቂው] አይኔን ስጨፍን እንቅልፍ የያዘኝ መስሎት እየሮጠ መጥቶ ኤሌክትሪክ ሾከሩን አንገቴ ላይ አደረገ። ‘እየተኛሁ አይደለም’ ብዬ ነቅቼ ነገርኩት። ‘እንዳይደገም’ ብሎኝ ሄደ”
በማግስቱ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ የእስር አይነቱ ተቀየረለት። ሁለት እጆቹ ወደላይ በአንድ ላይ ታስረው የእግሮቹ ጣቶች ብቻ መሬት እንዲነካ ተደርጎ ታሰረ። እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንዲህ ቆይቶ ደግሞ እስሩ ተቀየረ።
የእስር አይነቶቹ ብቻ እየተቀያየሩ ያለ ምግብ ሶስት ቀናትን አሳለፈ። በእነዚህ ቀናት የሚጸዳዳውም ራሱ ላይ ነበር።
ሶስተኛው ቀን ላይ የኩባንያው አለቆች መጥተው ወስደው ቀሪውን 500 ዶላር ለማስላክ ቤተሰብ ጋር እንዲደውል ካደረጉት በኋላ መልሶ ታሰረ።
በአራተኛው ቀን ጀርባውን ዞሮ ከታሰረ በኋላ ለሁለት ጀርባው እስከሚደማ ድረስ ተገረፈ። ከቤተሰብ የሚያስልከው ተጨማሪ ገንዘብም ከ500 ወደ ሁለት ሺህ ዶላር አደገ። ለቤተሰብ ደውሎ ይህንኑ ተናገረ። አምስተኛውንም ቀን በእስር ካሳለፈ በኋላ ከቤተሰብ ብሩን ሲቀበሉ ከእስር ተፈታ።
አርሶ አደሮቹ የሙባረክ ወላጆች እርሱን ለማስፈታት በአጠቃላይ 600 ሺህ ብር ገደማ ወጪ እንዳደረጉ ይናገራል። ግማሹ ገንዘብ የተገኘው የቤተሰቡ ከብቶች እና እህሎች ተሽጠው ነው። ቀሪው ግማሽ ደግሞ በብድር እና መዋጮ።
ደላላ “ከሩቅ አይመጣም”
ሙባረክ ላይ የደረሰው ቅጣት ሁሉም ኩባንያዎች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስ አይደለም። በተለያየ መንገድ ወደ ካምፑ ከመጡ በኋላ ከቻይናውያን አለቆች ጋር ተሳስማምተው፣ የበላይ ተቆጣጣሪም ሆነው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች ይናገራሉ።
ሙባረክ፤ በነበረበት ኩባንያ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ተቆጣጣሪ የነበረው ሌላ የሀገራቸው ልጅ እንደነበር ያስታውሳል። “[ኢትዮጵያዊው] ቲም ሊደር የምትሰራውን ይከታተላል። እንዴት ቻት እንደምናደርግ ያነባል፤ ፍጥነታችን ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ይከታተላል። ከተናደደብህ፣ ከእርሱ ጋር መስማማት ካልቻልክ አሳልፎ ይሰጥሃል” ሲል በኩባንያው ውስጥ ያላቸው ሚና ይገልጻል።
ኩባንያዎቹ ውስጥ ሆነው ሌሎች ሰዎች ከኢትዮጵያ የሚያስመጡ መኖራቸውም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በግቢዎቹ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይገልጻሉ።
ከ2021 ወዲህ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ሰዎች መመልመል የጀመሩት የማጭበርበር ኩባንያዎች፤ ሰዎችን ማስመጣት የጀመሩት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያሰሯጯቸው ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎች ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የምልመላ ዘዴ መቀየሩን ከካምፑ የሚወጡ ሰዎችን የምትረዳው ናንሲ ትናገራለች። በአሁኑ ወቅት “አብዛኛዎቹ ሰዎች እየተቀጠሩ ያሉት በራሳቸው ሀገር ሰዎች” መሆኑን ታስረዳለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ካምፖቹ ውስጥ የነበሩ እና ያሉ ተጎጂዎች “ስራ ታገኛላችሁ” ተብለው የሄዱት በኢትዮጵያውያን “ደላሎች” አግባቢነት ነው። ሁሉም ግለሰቦች ታይላንድ ውስጥ ስራ ስለመኖሩ መረጃ የደረሳቸው በሚያውቁት ሰው በኩል ነው።
ከአምስቱ መካከል ሁለቱን ያነጋገሯቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ደላላዎች ሲሆኑ ባንግኮክ ከተማ ከደረሱ በኋላ ተቀብለው ወደ ምያንማር ያሻገሯቸው ቻይናውያን የኩባንያዎቹ ሰዎች ናቸው። ሶስቱ ደግሞ ሲያነጋግሩ የነበረው ታይላንድ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደላላዎችን ሲሆን ታይላንድ ውስጥ ከተቀበሏቸው በኋላ ለቻይናውያው አስተላልፈዋቸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች፣ በታይላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መቀመጫቸው ታይላንድ የሆኑት እነዚህ ደላሎች “ካምፖቹ ውስጥ ተመሳሳይ ስራ ሲሰሩ የነበሩ” መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ናንሲ፤ “[ከካምፑ ከሚወጡ ሰዎች መካከል] የትኛው ተጎጂ እንደሆነ፣ የትኛው እንዳልሆነ መለየት ከባድ ነው። ከካምፖቹ የሚወጡ ተጎጂዎች እንዳሉ ብናውቅም፤ አንዳንዶቹ ሰዎችን ለመቅጠር ሲባል እንዲወጡ እንደሚፈቀድላቸው እናውቃለን” ትላለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ታይላንድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ኢትዮጵያውያንም ከካምፑ የወጡ ሰዎች ታይላንድ ውስጥ ተቀምጠው ሰዎችን እንደሚያስመጡ ማስተዋላቸውን ገልጸዋል። ሁለቱም የታይላንድ ነዋሪዎች ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ በሚገኙ ደላሎች “በተፈጠረባቸው ስጋት” ስማቸው እንዲጠቀስ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ላለፉት 18 ዓመታት ባንግኮክ ውስጥ የኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ በዚህ መንገድ ተታልለው ወደ ታይላንድ የመጡ ሰዎችን በተደጋጋሚ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረጋቸው ምክንያት ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“[መልዕክት የሚልኩት] በማይታወቅ ቁጥር ነው። ግን ከዚያ መሆኑን የሚያሳየው ‘የሰው ስራ እያበላሻችሁ ነው፣ እንገላችኋለን’ [ይላሉ]። የእኔ ልጆች የሚኖሩት ኢትዮጵያ ነው። ‘ልጆችህን እንጠፋለን’ እንደዚህ አይነት ዛቻዎች ነው የሚመጡት” ሲሉ የሚደርሷቸውን ዛቻዎች ገልጸዋል።
ታይላንድ ውስጥ ለስድስት ዓመታት የኖረ ሌላ ኢትዮጵያዊ በበኩሉ ሰዎችን በማስመጣት እና ካምፖች ውስጥ በማስገባት ላይ የተሰማሩ “ቢያንስ አስር” ወንድ እና ሴት ኢትዮጵያውያንን እንደሚያውቅ ይናገራል። የእነዚህ ግለሰቦችን ባህሪ የሚገልጸው “ድብቅ እና ጨካኝ” ብሎ ነው።
ኢትዮጵያውያንን ከምያንማር ካምፖች የማስወጣት ፈተና
ምያንማር ከሚገኙት ካምፖች ለመውጣት የሚጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ “በሺዎች የሚቆጠሩ” ኢትዮጵያውያን አሁንም በውስብስቡ የደቡብ ምስራቅ እስያ የወንጀል መረብ ተጠልፈው ተይዘዋል። የእነዚህ ወጣቶች ቤተሰቦች ከኢትዮጵያ መንግስት መፍትሔ እየጠበቁ ነው።
የቤተሰቦቹን ኮሚቴ የሚሰበስቡት ወ/ሮ አበበች ሲመል እንደሚናገሩት እስካሁን ድረስ ስማቸው እና ያሉበት ቦታ የተረጋገጡ ከ250 በላይ ወጣቶች በኮሚቴው ተመዝግበዋል። ወላጆቹ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲመላለሱ ቢቆዩም እስካሁን ድረስ ተጨባጭ መፍትሔ አላገኙም።
በምያንማር የሚገኙ ኢትዮጵያውያ ጉዳይ የተያዘው ጃፓን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው። በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዳባ ደበሌ፤ ከግንቦት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በምንያማር የኢትዮጵያ አምባሳደርም ሆነዋል።
ኤምባሲው ኢትዮጵያውያኑን ለማስወጣት እያከናወነ ያለውን ተግባር በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረገው ቢቢሲ፤ ጥያቄዎች በኢሜይል እንዲላኩ በአምባሳደር ዳባ ተጠይቆ ይህንኑ ቢያደርግም ምላሽ አላገኘም። በታይላንድ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራዎች ደርቦ የያዘው በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲም በተመሳሳይ ምላሽ አልሰጠም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በሰጣቸው መግለጫዎች ዜጎቻቸው በተመሳሳይ መልኩ ከተያዙባቸው 18 ሀገራት ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያኑን ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። ቢቢሲ ከሚኒስቴሩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።
ከካምፖቹ የወጡ ተጎጂዎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚረዳውን ድርጅት የምትመራው ናንሲ፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵውያንን ለመመለስ በተደረጉ ጥረቶች የኢትዮጵያ መንግስትን ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ትናገራለች። ታይላንድ ውስጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለመኖሩ የሀገሪቱን መንግስት የሚያገኙት ባንግኮክ ውስጥ ባለው የኬንያ ኤምባሲ በኩል መሆኑን ታስረዳለች።
“በህንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጉዳዩ ላይ የተነሳ ይመስላል። በቀጥታ እንድናገኛቸው አይፈልጉም። ኤምባሲው የተጎጂዎችን ዜግነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ እንዲፅፍልን ስንፈልግ ብዙውን ጊዜም በቶሎ ምላሽ አይሰጥም” ስትል ወቀሳዋን ታቀርባለች።
በካምፖቹ ውስጥ የነበሩ እና ያሉ ወጣቶች በበኩላቸው ኬንያ እና ዩጋንዳውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎች “በሀገራቸው መንግሥት ጥረት” እንዲወጡ ሲደረጉ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን “ይህ አይነቱ እርምጃ” አለመኖሩን ያነሳሉ።
ከካምፖቹ ከወጡ ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኛዎቹ ነጻነታቸውን ያገኙት በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ከፍለው ነው። በምያንማር ካምፕ ወስጥ ስድስት ወራትን ያሳለፈው ሙባረክም ገንዘቡን ከከፈለ በኋላ የኩባንያው አለቆች እንዲወጣ አድርገውታል።
እርሱን ጨምሮ አራት ሰዎችን ከካምፕ አስወጥተው ወደ ታይላንድ መልሰው ሜይ ሶት ከተማ ላይ ጥለዋቸው እንደሄዱ ይናገራል። ታይላንድ ውስጥ በኢሚግሬሽን እስር ቤት እና ማቆያዎች ውስጥ አንድ ወር ያሳለፈው ሙባረክ፤ ሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ገብቷል።
ታስሮ በቆየባቸው አምስት ቀናት እጆቹ እና ትክሻው ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ብዙ ጉልበት የሚጠይቁ ስራዎችን ማከናወን እንደማይችል ያስረዳል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ወዲህ ምንም አይነት ስራ ላይ አልተሰማራም።
“ቤተሰቦቼ አስበው ‘ይህንን አድርግ’ ካላሉኝ በስተቀር አሁን የማስበው ነገር የለም። ወጪ አውጥተው ነው የላኩኝ፤ ከዚያም የመለሱኝ ገንዘብ ከፍለው ስለሆነ ‘ይህንን አድርጉልኝ’ ማለት ይከብደኛል” ሲል ቀጣይ የህይወት እርምጃዉን አለመለየቱን ያስረዳል።
ሙባረክ “ባርነት” ሲል በሚያስታውሰው የካምፕ ቆይታውን የደረሱበት አካላዊ እና ስነ ልቡናዊ ጉዳቶች ጨርሰው አልጠፉም። “ካምፑ ውስጥ የደረሰብኝን ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ። ‘ቤተቦቼ ለእኔ ብለው እዳ ውስጥ ገቡ’ ብለህ አንዳንዴ ታስባለህ። ግን ደግሞ ‘አላህምዱሊላሂ በህይወት መውጣቴ በራሱ በቂ ነው’ ብዬ አስባለሁ”በማለት ይናገራል።
ታይላንድ ውስጥ ስራ እንደሚያስቀጥረው አሳምኖ ለኩባንያው ባለቤቶች የሸጠው ደላላው አብዲ በአንጻሩ ተጠያቂ አልሆነም። ቲክቶክ ላይ እየዘፈነ (lip sync) በሚለቅቃቸው ቪድዮዎች ይመለከተዋል። አሁን ላይ ወደ ዱባይ መሻገሩን እንደሰማም ያነሳል።
“ተገኝቶ ወደ ህግ ቢያቀርቡት ደስ ይለኛል” ይላል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)