የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አገራቸው ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በተካሄደው የሳዑዲ አረቢያ የሰላም ንግግር ላይ እንድትገኝ አለመጋበዟ የሚያስገርም ነው ማለታቸውን ተከትሎ ትራምፕ ጠንከር ያለ ወቀሳ አቀረቡ።
ትራምፕ የዩክሬን ምላሽ ያልጠበቁት እንደሆነ ገልጸው ለጦርነቱ ጅማሮ ዩክሬንን ተጠያቂ አድርገው አገሪቱ “ስምምነት ላይ መድረስ ትችል ነበር” ብለዋል።
የዩክሬን ጦርነት የተቀሰቀሰው ከሶስት ዓመታት በፊት ሩሲያ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ነው።
ትራምፕ ይህንን ያሉት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አገራቸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሰላም አስከባሪዎች በዩክሬን መስፈርን በፍጹም እንደማትቀበለው መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።
ሩሲያ እና አሜሪካ ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ቡድኖችን ለማቋቋም መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ በአሜሪካ እንደተከዱ ለሚሰማቸው ዩክሬናውያን የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ በቢቢሲ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “በሰላም ንግግሩ ባለመሳተፋቸው እንደተበሳጩ ሰምቻለሁ።
ከዚያ በፈት ለሶስት ዓመታት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ይህንን ማድረግ ይችሉ ነበር። ይህ በቀላሉ ሊፈታ ይችል ነበር” ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
“[ጦርነቱን] መጀመር አልነበረባችሁም ። ስምምነት ላይ መድረስ ትችሉ” ነበር ብለዋል።
“ለዩክሬን ስምምነት ላይ መድረስ እችል ነበር” ሲሉም አክለዋል።
“ይህም ከሞላ ጎደል ሁሉም መሬት ያስገኝላቸው ነበር። የትኛውም ሰው አይገደልም ነበር እንዲሁም የትኛውም ከተማ አይፈርስም ነበር” ሲሉ ነው ትራምፕ የተናገሩት።
በሳዑዲ አረቢያ የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለስልጣናት የሰላም ንግግር ካደረጉ በኋላ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ጉዳዩ “ከፍተኛ መተማመን እንዳሳደረባቸው” ገልጸዋል።
“በጣም መልካም ነበሩ። ሩሲያ በጉዳዩ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ትፈልጋለች። ይህ ጭካኔ እንዲቆም ይፈልጋሉ” ብለዋል።
“ጦርነቱን የማስቆም ኃይል ያላቸው ይመስለኛል” ሲሉ ትራምፕ አስረድተዋል።
የአውሮፓ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ሊልኩ ስለሚችሉበት ሁኔታ የተጠየቁት ትራምፕ ” ይህንን ማድረግ ከፈለጉ ጥሩ ነው። የምደግፈው ጉዳይ ነው” ብለዋል።
የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለስልጣናት በሪያድ ያካሄዱት የሰላም ንግግር የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የመጀመሪያው ነው።
በዚህ የሰላም ንግግር ላይ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ እንዲሁም የሩሲያ ፕሬዚዳንት ረዳት ዩሪ ኡሻኮብ እ ና የሩሰያ የሉዓላዊ ሃብት ፈንድ ኪሪል ዲሚትሪቭ ተገኝተዋል።
ከሰላም ንግግሩ በኋላ ላቭሮቭ እንደተናገሩት ሩሲያ በየትኛውም የሰላም ስምምነት የኔቶ አገራት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዩክሬን መስፈራቸውን እንደማትቀበል ነው።
አሜሪካ እና ሩሲያ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል አምባሳደሮችን መሾም ጨምሮ “አጋርነታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንደሚመለስ” ገልጸዋል።
ሩቢዮ በበኩላቸው ጦርነቱን ለማስቆም ሩሲያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቁርጠኛነቷን እንዳመኑበት አስረድተዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)