እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ በምታካሂደው ወረራ ባደረባት ስጋት ምክንያት አሜሪካ ልትልከው የነበረው የቦምብ ጭነት ማቆሟን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ።
የቦምብ ጭነቱ ከፍተኛ ክብደት ያላቸው 2000 ፓውንድ (907 ኪሎ ግራም) እና 226 ኪሎግራም የሚመዝኑ ቦምቦችን ያካተተ መሆኑን ባለስልጣኑ በአሜሪካ የቢቢሲ የሚዲያ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
እስራኤል በራፋህ በምታካሂደው ወረራ ሲቪሎችን እንዴት መጠበቅ ትችላለች ለሚለው የአሜሪካ ስጋት መፍትሄ ማምጣት አልቻለችም ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
እስራኤል ይህንን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠችም።
የእስራኤል ጦር በምስራቃዊ ራፋህ የማያባራ ጥቃት ከትናንት በስቲያ ሌሊቱን ከፈጸመ በኋላ ጋዛን እና ግብጽን የሚያገናኛቸውን የድንበር ማቋረጫ ራፋህን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
ጦሩ እርዳታ ወደ ጋዛ በሚገባበት በኩል ታንኮቹን አሰልፎ ታይቷል።
በተለይ በራፋህ ከተማ አካባቢ የእስራኤል የቦምብ ጥቃት የከፋ ሲሆን በአንድ ሌሊት በተፈጸመው ጥቃት የአንድ ቤተሰብ ሰባት አባላት መገደላቸውን የአካባቢው የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ካስገባቻት በኋላ የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ብቸኛው የእርዳታ መግቢያ እንዲሁም ከጥቃቱ ለሚሸሹ ብቸኛ መውጫ ነበረች።
በዚህ ሳምንት የእስራኤል ጦር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከራፋህ ምስራቃዊ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
በዚህች ከተማ የሚኖሩት አብዛኛዎቹ እስራኤል በሰሜን ጋዛ እየፈጸመችው ከነበረው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃትን ሸሽተው የተጠለሉ ናቸው።
“የአሜሪካ አቋም እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በራፋህ ያሉ ሰዎች [ፍልስጤማውያን] የትም መሄጃ በሌላቸው ሁኔታ ከባድ የምድር ላይ ጥቃት እንዳትጀምር የሚል ነው” ሲሉ የዋይት ሃውስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
“በራፋህ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን መጠበቅ የሚቻልበት እና ከሌሎች የጋዛ ስፍራዎች በተለየ መልኩ በዚህች ከተማ ያቀዱትን ዘመቻ የሚያካሂዱበትን መንገድ ከእስራኤል ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል” ብለዋል።
“እነዚህ ውይይቶች እየተካሄዱ ቢሆኑም ስጋታችንን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አልቻሉም። የእስራኤል መሪዎች በራፋህ ያላቸውን ዘመቻ ለማካሄድ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ እኛም በራፋህ ጥቅም ላይ ሊውሉ ስለሚገባቸው የጦር መሳሪያዎች መገምገም ጀመርን። ይህ የተጀመረው ባለፈው ወር ነው” ብለዋል።
“ይህንን ግምገማ ተከትሎም ባለፈው ሳምንት ሊላክ የነበረ አንድ የጦር መሳሪያ ጭነት አቁመናል። ጭነቱ 2 ሺህ ፓውንድ እና 500 ፓውንድ የተሰኙት ቦምቦችን ይዟል። ትኩረታችን በተለይ 2 ሺህ ፓውንድ የሚመዝኑት ቦምቦችን ልክ በሌሎች የጋዛ ክፍሎች ላይ እንዳየነው ጥቅጥቅ ባለ የከተሜ አሰፋፈር ላይ መጠቀም የሚያስከትለው ተጽእኖ ላይ ነው። ይህንን ጭነት በምን ሂደት እንላከው የሚለው ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም” ሲሉም አስረድተዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )