አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ አቋረጠች……. Leave a comment

አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ ማቋረጧን የዋይት ሐውስ ባለስልጣናት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ አረጋገጡ።

አንድ የዋይት ሐውስ ባለስልጣን “ፕሬዝዳንቱ ሙሉ ትኩረታቸው ሰላም ላይ ነው። አጋሮቻችንም እዚህ ግብ ላይ እንዲያተኩሩ እንፈልጋለን። የምናደርገውን እርዳታ ለጊዜው አቁመን ለመፍትሄው የሚኖረውን አበርክቶ መለስ ብለን ለመፈተሽ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ብሉም በርግ በበኩሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጡ ማንኛውንም የወታደራዊ ድጋፎች ሙሉ በሙሉ ለጊዜው ማቋረጣቸውን አረጋግጧል።

እንደ ብሉም በርግ ዘገባ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ዩክሬን ያልደረሱ ወታደራዊ መሳርያዎች፣ፖላንድ ወደሚገኘው ወታደራዊ ግምጃ ቤት እየተጓጓዘ የሚገኙ መሳርያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ እንዲቆሙ ሆነዋል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባወጡት መግለጫ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአሁኑ ጊዜ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት እድል ያላቸው በዓለም ላይ ብቸኛው መሪ ናቸው” ብለዋል።

“ሩሲያውያንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት እንፈልጋለን። ሰላም ይቻል እንደሆነ ማጣራት እንፈልጋለን።” ብለዋል በመግለጫቸው ላይ።

በጉዳዩ ላይ ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ፔንታጎን እስካሁን ድረስ አስተያየታቸውን አልሰጡም።

ብሉምበርግ እና ፎክስ ኒውስ የወታደራዊ እርዳታው እገዳ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ለዋሺንግተን “ለሰላም ዝግጁ” መሆናቸውን እስኪያሳዩ ድረስ እንደሚቀጥል ባለስልጣናትን ጠቅሰው ዘግበዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለኪየቭ የሚሰጠውን የደህንነት መረጃም ለመቀነስ መወሰኑን ሲኤን ኤን ዘግቧል።

ይህ ዜና የተሰማው ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳነት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዋሺንግተን ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ነው።

ውይይቱ በሁለቱ መሪዎች መካከል የጋለ ክርክር የተደረገበት እና ኃይለ ቃል የተቀላቀለበት ነበር።

ዲሞክራቱ እና የወታደራዊ አገልግሎት ኮሚቴ ውስጥ አባል የሆኑት ታሚ ደክወርዝ የዋይት ሐውስን ውሳኔ “አሳፋሪ እና ዩክሬንን የነጠለ” ሲሉ ተችተዋል።

በማሕበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይም “ውሳኔው አገራችንን ደህንነቷ የተጠበቀ አያደርገውም” ብለዋል።

አክለውም “ፑቲንን እና ጠላቶቻችንን የልብ ልብ ሲሰጥ የዲሞክራሲ አጋሮቻችንን ጋር ያለንን ወዳጅነት ያዳክማል” ብለዋል።

ሌላኛው ዲሞክራት ፒተር ዌልች ደግሞ “ፑቲክ የጦር ወንጀለኛ ነው። ትራምፕ ደካማ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ይህ የዜሌንስኪ ጉብኝት በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነትን ለማቆም እና የማዕድን ስምምነትን ለመፈራረም ያለመ ነበር።

በኃይለ ቃል የተሞላው ጋዜጣዊ መግለጫ ከተካሄደ በኋላ ውይይቱ ሳይጠናቀቅ እንዲሁም በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት ከትራምፕ ጋር የዜና መግለጫ መስጠት ቢኖርባቸውም ዜሌንስኪ ከዋይት ሃውስ እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

ለሳምንት ያህል ሲሞገስ የነበረው የማዕድን ስምምነቱም ሳይፈረም ቀርቷል። “ለሰላም ዝግጁ ስትሆን ተመልሰህ ና” ሲሉም ትራምፕ የዜሌንስኪ መኪና ለቆ ከመውጣቱ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።

በዋይት ሃውስ የነበረው የመጀመሪያው ግማሽ ሰዓት ውይይት ሰላማዊ ነበር። ሆኖም ቫንስ “ለሰላም እንዲሁም ለብልጽግና መንገዱ በዲፕሎማሲ መፍታት ነው” ካሉ በኋላ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ እያደረጉት ያሉት ይህንኑ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጣልቃ በመግባት ሩሲያ ወረራ ከመፈጸሟ ከሶስት ዓመታት በፊት ያልተሳካ የተኩስ አቁም ስምምነትን በማጣቀስ “ማንም አላስቆመውም” ሲሉም የሩሲያ አቻቸውን ቭላድሚር ፑቲንን ወቅሰዋል።

“ጄዲ ምን ዓይነት ዲፕሎማሲ ነው የምታወራው? ምን ማለትህ ነው?” ሲሉም ዘለንስኪ ጠየቀዋል።

የሁለቱ ባለስልጣናት ንግግር ውጥረት እንደተሞላበት ባሳየው በዚህ ቅጽበትም ቫንስ “የአገርህን ውድመት የሚያስቆመው ዲፕሎማሲ አይነት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

በመቀጠልም ቫይስ ፕሬዚዳንቱ “አክብሮት የጎደለው” በሚል ዜሌንስኪን ዘልፈዋቸዋል።

ከዚህ የተካረረ ውይይት በኋላ አውሮፓውያን በእንግሊዝ ተሰብስበው መክረዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እና አገሪቷን ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል አራት ነጥቦችን የያዘ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።

ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች አገራት በጥምረቱ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ስታርመር፣ ዩክሬንን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት አሜሪካ እንድትቀላቀል እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

ስታርመር የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ በአብዛኛው ከአውሮፓ የሆኑ 18 መሪዎች በተሳተፉበት ጉባኤ ” በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለነው” ብለዋል።

በዋሽንግተን ከፍተኛ ዘለፋን ያስተናገዱት ዜሌንስኪ በበኩላቸው “ዩክሬን ጠንካራ ድጋፍ እንዳላት ተሰምቷታል፤ ጉባኤውም ለረዥም ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአውሮፓ አንድነት አሳይቷል።” ሲሉ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop