የሶማሊላንድ የመረጃ፣ የባህል እና የብሔራዊ መመሪያ ሚኒስትር አሊ ሐሰን መሐመድ (አሊ ማርሃን) ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከቀናት በፊት ራሷን በነጻ አገርነት ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ቆንስላው ወደ ኤምባሲ ማደጉን አስመልክቶ የተናገሩትን አረጋግጠዋል።
“የኢትዮጵያ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማደጉን አስመልክቶ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው ዕለት ፕሬዝዳንቱ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል” ሲሉ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ሶማሊላንድ ነጻነቷን በማወጅ እንደ አገር የተመሠረተችበትን ዕለት ግንቦት 10/2016 ዓ.ም. 33ኛ ዓመት ስታከብር ሃርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸውን በሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያስረዳል።
የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት የሰጡትን መረጃ አስመልክቶ ቢቢሲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ የሆኑትን አቶ ነብዩ ተድላ የጠየቀ ሲሆን፣ ጉዳዩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሳምንታዊ መግለጫ ላይ ሊነሳ እንደሚችል ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት ይህንን በተመለከተ የሚሰጡት መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ የባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ሹመት ከሰጧቸው 10 ሰዎች መካከል በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ልዑክ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ደሊል ከድር ቡሽራ መካተታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግንቦት 7/2016 ዓ.ም. ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ደሊል ከድር በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ልዑክ ሆነው ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ ሲያገለግሉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በሶማሊላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ከፍ ማለቱን በተመለከተ ከሶማሊያ በኩል አስካሁን በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ሶማሊያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል በፈረሙት የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ በመወሰን በአገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ እና አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።
በተጨማሪም ከሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ከአራት ወራት በፊት የፈረሙት የባሕር በር የማግኛ የመግባባቢያ ስምምነት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም የሶማሊላንዱ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ሰፈር በኪራይ የምታገኝበት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥበት ስምምነት በሁለት ወራት ገደማ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከሳምንታት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም ከዶቼቬለ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል የጦር ሠፈር ልትከራይ የምትችላቸው ሦስት አማራጭ ቦታዎች ተለይተዋል ብለው ነበር።
ሚኒስትሩ በዚህ አጋጣሚም ሁለቱ አገራት የተፈራረሟቸው የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት በጥሩ ሂደት ላይ እንዳለ ገልጸው፣ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚፈጸሙበት ረገድ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ይህ ስምምነት በተገቢው ሂደት ላይ መሆኑን መግለጻቸውን ዋቢ በማድረግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ሁለቱ አገራት የተፈረረሙት የመግባባቢያ ስምምነት ለሦስት አስርት ዓመታት ያስቆጠረው ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ያጠናከረ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ከቢበሲ ሶማሊኛ የሶማሊያን የተቃውሞ አንስቶ ለቀረበላቸው ጥያቁ “የሶማሊያ መንግሥት በሶማሊላንድ ላይ ምንም አይነት ሥልጣን እንደሌለው እና የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በምንም መልኩ ሶማሊያን አይመለከትም” ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የሞቃዲሾ አስተዳደር ከመመሥረቱ በፊትም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር የቀደመ ጤናማ ግንኙነት ነበረው ሲሉም በዚሁ ቃለ መጠይቅ ወቅት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡- (BBC )