ኢትዮጵያ የተቀቀሉ የሥጋ ምርቶች እና ተረፈ ምርቶችን ለቻይና ገበያ ልታቀርብ መሆኑን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ሳህሉ ሙሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ለመላክ እየተዘጋጀች ያለችው የተቀቀለ የበግ፣ ፍየል፣ የዳልጋ ከብት እና የግመል ስጋን መሆኑ ዶ/ር ሳህሉ ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ “በዚህ ደረጃ ምርቱን ለሚፈልጉ አገራት ነው እየተሰራ ያለው ግን በአሁን ለጊዜው ዒላማ ያደረግነው የቻይናን ገበያ ነው” ብለዋል።
ዶ/ር ሳህሉ “በዋናናት ታርጌት [ዒላማ] የተደረገው ትልቁ ገበያ የሆነውን የቻይና ገበያ [ነው]” ሲሉ የኢትዮጵያ የተቀቀለ ስጋ ዋና መዳረሻን ጠቁመዋል። ዋና ዳይሬክተሩ “ለቻይና ገበያ ዒላማ አድርገን እንስራ እንጂ ውጤቱ ምርታችንን ለሚፈልጉ ሁሉም ገበያዎች ሁሉ የሚሆን ነው” ሲሉ አክለዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ ከቻይና መንግስት እና ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በተደረገ ንግግር “ከኢትዮጵያ የተቀቀለ የሥጋ ምርት እና ተረፈ ምርት እንደሚቀበሉ ይሁንታ ተሰጥቷል” ብለዋል።
ይህን ተከትሎ “እዚህ [ኢትዮጵያ] ያሉ የኤክስፖርት ስጋ ማቀነባበሪዎች ይሄንን ስጋ የመቀቀያ ቴክኖሎጂ በማምጣት በፋብሪካዎቻችው ውስጥ በመግጠም ዕድሉን ለመጠቀም እንቅስቃሴ እያደረጉ” መሆኑን ጠቁመዋል።
“[ለፋብሪካዎቹ] ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው” የሚሉት ዶ/ር ሳህሉ፤ “ይሄ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ በቀጥታ ምርትን በዚህ አግባብ በማቀነባበር ወደ ትልቁ ገበያ የመግባት ዕድል እየተከፈተ ነው የሚገኘው” ሲሉ አክለዋል።
ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የሥጋ አይነት በተመለከተ ሲያብራሩ “ከዋናው ቀዩ ስጋ ውጭ ያሉ ተረፈ ምርቶች፤ ቀንዱም ለአግልግሎት እንዲውል ተደርጎ ተቀነባብሮ ይላካል። ሌሎች የሆድ ዕቃዎችም በሙሉ በየፈርጃቸው ተቀነባብረው ወደ የሚፈለጉበት ገበያ እየተላኩ ነው” ብለዋል።
ዶ/ር ሳህሉ የተቀቀለ ሥጋ ለውጭ ገበያ የሚላክበትን ምክንያት፤ “አንዳንድ አገራት ወደ አገራቸው ለሚያስገቡት ምርት በጣም ጥብቅ የሆነ መስፈርት ነው የሚያስቀምጡት። ከዛ በመነሳት ነው ኢትዮጵያ ምርት ተቀቅሎ ለገበያ መግባት እንደሚችል ፈቃድ የተሰጠው” ሲሉ አብራርተዋል።
ይህ ጥብቅ የሆነ መስፈርት “አገራት የእንስሳት በሽታ ወደ አገራቸው እንዳይገባ የሚከላከሉበት ዘዴ ነው” ሲሉ ያክላሉ።
“መቀቀሉ በራሱ እሴት መጨመር ነው” የሚሉት ዶ/ር ሳህሉ፤ “ከጥሬ ምርትነት ተቀቅሎ ጥራት እና ደህንነቱ ተጠብቆ ነው ወደ መዳረሻ ገበያ የሚላከው ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም አንዱ እሴት ነው” ይላሉ።
የተቀቀለ ሥጋ መላኩ ዋጋ ላይ ስለሚኖረው ለውጥ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ “ዋጋ ላይ እንደየመዳረሻ ገበያዎቹ እና ተጠቃሚ ምርጫ ዋጋውም በዛው ልክ ይለያያል። ቁርጥ ዋጋ የለም። አንዳንድ ገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። አንዳንድ ገበያ ደግሞ መደበኛ ዋጋ የሚገኝበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ስጋ ለመቀቀል የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ በተመለከተ ዶ/ር ሳህሉ “ያን ያህል ከባድ አይደለም ትልልቅ አቅም ያላቸው የኤክስፖርት ማቀነባበሪያዎች ስላሉ ቴክኖሌጂውን ማስገባት እና መግጠም ብቻ ነው። ኢንቨስትመንት ይጠይቃል ዞሮ ዞሮ ግን ከቴክኖሎጂ አንጻር አዲስ ቴክኖሎጂም አይደለም ከባድም አይደለም” ብለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኢትዮጵያ በዓመት 200 ሺህ ቶን ስጋ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አላት። “ስጋ ወደ እነስሰሳት ሲቀየር በግምት ወደ 20 ሚሊዮን እስሳትን አርደው አቀዝቅዘው ወደ ገበያ መላክ የሚችል አቅም ፈጥረናል” ሲሉ አክለዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)